የዐባሪው ትልም
ይህ ክፍል፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ወይም “በእግዚአብሔር ስም” ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ “ስሙን የሚጠራ ይድናል”፣ “በስሙ ተሰብሰቡ”፣ “በስሙ አጋንንትን አውጡ” ወዘተ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ቀሳውስትና ተከታዮች፣ በዚህ አግባብ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ስም” የሚለውን ዐሳብ የሚጠቀመው የተጸውዖን ስም ለማመልከት ይመስላቸዋል[1]፡፡ ከዚህ የተነሣ፣ “የጥምቀት ቀመር በኢየሱስ ስም” መሆን አለበት ይላሉ፡፡ እንዲያውም በተጸውዖ ስምና በማዕረግ ስም መኻል ልዩነት መኖር አለበት ባዮች ናቸው፡፡ በነገረ መለኮቱ ክፍል፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በተጸውዖ ስምና በማዕረግ ስም መኻል አንዳችም ልዩነት እንዳላደረጉ በግልጽ ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የድርጅቱ አስተማሪዎችና ተከታዮች፣ ስምን በተመለከተ መስመር ስተው የወጡበትን ወሳኝ ፅንሰ ዐሳብ ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
ሀ. መግቢያ
ብዙ ወንጀል ያለበትን ሰው፣ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፣ “በስሜ እንጀራ ብላ” ብለው ከእስር እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ ግለሰቡ መንደር ለመንደር እየዞረ፣ “በእምዬ ምኒልክ፤ የዕለት እንጀራዬን ስጡኝ” ይላል፡፡ በአለማመኑ የተገረሙ ሰዎች፣ “የአምላክ ስም ጠርቶ መጽሐፍ መትቶ ልመናና መሓላ የተለመደ ነው፡፡ አንተ ግን በምን አግባብ፣ ‘በምኒልክ ስም’ እያለ ትለምናለህ” ቢሉት፣ “‘በስሜ እንጀራ ብላ’ ያለኝ ምኒልክ ነው” አለ ይባላል፡፡
ይህ ሰው በምኒልክ ስም መለመኑ በጐ ዐስቦ ሊሆን ይችላል (ማለትም በእኔ በጐ ሥራ ሳይሆን፣ በምኒልክ ቸርነት ነው ነጻ የወጣሁት ብሎ እያለ ይሆናል)፡፡ ወይም በተንኰል (“በስሜ ምግብ ብላ” እንዴት እባላለሁ) ብሎ ምኒልክን በምፀት መተቸቱ ሊሆን ይችላል፡፡ የግለሰቡ ዐሳብ ምን እንደ ሆነ ገድሉ ላይ የተጻፈ ነገር የለም፡፡ ምኒልክ ግን፣ “በስሜ እንጀራ ብላ” ያሉት በስሜ ነዳይ ሆነህ ለምን በሚል መንፈስ እንዳልሆነ፣ በቊርጥ መናገር ይቻላል፡፡ ግለሰቡ ግን ወይ ከፍቅር ወይ ከጥላቻ ጒዳዩን አዛብቶ አቅርቦታል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጸለይ አለብን የሚሉና መጸለይ የለባችሁም የተባሉ ሰዎች፣ ትልቅ ውዝግብ ፈጥረው ነበር፡፡ የክርክሩ መነሻ የኖርዝ ካሮላይና ስቴት ስለነበርች፣ በርእሰ ጒዳዩ ዙሪያ ዐስተያየት እንዲሰጡ የተጋበዙ የዱክ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮት መምህራን፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጸለይ ማለት፣ በጸሎት መጨረሻ ላይ ‘በኢየሱስ ስም’ ማለት አይደለም” የሚል ዐስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡
“የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቈላ. 3÷17) የሚለው ሐረግ እንዴት ይብራራል? ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “አብ በወልድ እንዲከብር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ እኔ አደርገዋለሁ” (ዮሐንስ 14÷13-14) ብሎ ባስተማረበት ዐውድ፣ የእነዚህ ምሁራን አስተያየት እንዴት ይተነተናል? በርግጥ፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” መጸለይ ማለት ምን ማለት ነው?
“የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” መምህራን፣ አምላክ ለዘመናት ደብቆ ያስቀመጠው ስም፣ “ኢየሱስ” ነው፡፡ በዚህ ስም ብቻ ድነት ይገኛል፡፡ “‘ኢየሱስ’ የሚለውን ስም ጠርቼ፣ ከዘላለም ሕይወት ልጐድል አልችልም” ወዘተ ሲሉ ይደመጣል፡፡ በርግጥ ግን፣ “የአምላክን ስም ዕወቁ”፣ የአምላክ ስም፣ “ጋሻችሁ ነው”፣ “ስሙን ቀድሱ”፣ “ስሙን የሚጠራ ይድናል”፣ “በስሙ ተሰብሰቡ”፣ “በስሙ አጋንንትን አውጡ” ወዘተ ማለት ምን ማለት ነው? “ስም” የሚለው ዐሳብ፣ በተጸውዖ ስም ላይ ትኲረት ያደረገ ነው ወይስ ከዚያ ያለፈ ትርጓሜና ፋይዳ አለው? በሚለው ዐቢይ ጒዳይ ላይ እንነጋገራለን፡፡ በተለይ፣ “ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አስተምህሮ አንጻር፣ ይህ ጥናት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ስም” ሲል ምን ማለቱ ነው እንዲሁም ምን ማለቱ አይደለም የሚለውን ጒዳይ እንመረምራለን፡፡
ለ. ስም እንዴት ይቀደሳል?
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ባስተማረው ጸሎት፣ በዕለት ጸሎታችሁ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ስም “ቀድሱ” ተብለናል፡፡ “ይትቀደስ ስምከ” (ስምህ ይቀደስ)፡፡ ቢሆን እግዚአብሔር ይቀድሰናል እንጂ፣ እኛ በምን አግባብ ልዑልን እንቀድሳለን? ደግሞ “ስም” እንዴት ይቀደሳል?
“የይሖዋ ምስክሮች”፣ ስሙን መቀደስ ማለት፣ ያህዌ (ይሖዋ) የሚለውን የአምላክ ተጸውዖ ስም ማወቅና መጥራት ነው ይሉናል፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባቀረበው ክህነታዊ ጸሎቱ (ዮሐንስ 17) “ስምህን አስታወቅኋቸው፤ አስታውቃችውማለሁ” (ቊጥር 26) ብሏል፡፡ የሚገርመው ግን፣ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ፣ በዐዲስ ኪዳን ውስጥ አንዳችም ጊዜ እንኳ፣ የአምላክን የተጸውዖ ስም ሲጠቀሙ አንመለከትም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሓፍያን እጅግ ብዙ ጊዜ፣ ብሉያትን ጠቅሰው ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት እንኳ፣ የብሉይ ኪዳኑን የአምላክ የተጸውዖ ስም፣ በቀጥታ ጠቅሰው ሲጽፉ አንመለከትም፡፡ ከዚህ የምንማረው ቊም ነገር፣ ስሙን መቀደስ ማለት፣ የተጸውዖ ስሙን ከመጥራት ጋር የተያያዘ አይደለም ማለት ነው፡፡
የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት ተርጒሞ ባሳተመው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም ላይ እንኳ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱን የጠራው፣ 1 ጊዜ፣ “አባ” ብሎ፣ 4 ጊዜ፣ “አምላኬ ሆይ” ብሎ፣ 21 ጊዜ፣ “አባት ሆይ” ብሎ፣ 1 ጊዜ፣ “ቅዱስ አባት ሆይ” ብሎ፣ 2 ጊዜ፣ “የሰማይና የምድር ጌታ” ብሎ፣ 1 ጊዜ፣ “ቅዱስ ጌታ” ብሎ፣ 1 ጊዜ፣ “እውነተኛ አምላክ” ብሎ ነው፡፡ ኢየሱስ፣ ያህዌ (ይሖዋ) የሚለውን ወይም ደግሞ ሌሎች የአምላክ የብሉይ ኪዳን የተጸውዖ ስሞችን፣ አንድ ጊዜ እንኳ ሲጠራ አንመለከትም (ማቴ. 6÷9:13፤ማቴ. 11÷25-30፤ ማቴ. 26÷39፤ ማቴ 27÷46፤ ማር. 14÷35-36፤ 15÷34፤ ሉቃ. 10÷21-22፤ 22÷34:41:42፤ ዮሐ. 11÷41-42፤ 12÷27-28፤ 17÷1-26)፡፡
ኢየሱስ የአምላክን ስም ለደቀ መዛሙርቱ ያስታወቀው፣ የአምላክን የተጸውዖ ስም እንድ ጊዜ እንኳ ሳይጠራ ነው፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየን፣ “ስሙን መቀደስ” ወይም፣ “ስምህን አስታወቅኋቸው” የሚለው ፅንሰ ዐሳብ፣ ከተጸውዖ ስም ጋር፣ ንክኪ (ተያያዥነት) እንደሌለው ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሙሴ፣ “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ (ኤልሻዳይ) ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር (ያህዌ) አልታወቀላቸውም ነበር” (ዘፀ. 6÷3) ይላል፡፡ እዚህ ምንባብ ላይ፣ አንድ መሠረታዊ ነጥብ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም:— ርእሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ) “ያህዌ” የሚለውን የተጸውዖ ስም እንደሚያውቁ፣ ይገለገሉበትም እንደ ነበር፣ በርካታ ክፍሎችን ጠቅሶ መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ:— በዘፍጥረት 22 ላይ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ሊሠዋ እንደ ሄደ እናነባለን፡፡ በዚያ ቦታ ላይ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አብርሃምን እንደ ጠራው (ቊ. 11)፣ “አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ እንደ ሰየመው” (ቊ. 14) እናነባለን፡፡ ይህ ታሪክ ከመፈጸሙ በፊት ደግሞ፣ እግዚአብሔር አብርሃምን፣ “ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔ ነኝ አለው፡፡ አቤቱ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ሆይ፣ እንድወርሳት በምን ዐውቃለሁ አለ” (ዘፍጥረት 15÷7-8)፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች እንኳ፣ በግልጽ የምንማረው ሐቅ፣ “ያህዌ የሚለው ስሜ አልታወቀላቸውም ነበር” የሚለው ጒዳይ፣ ከተጸውዖ ስም ጋር አንዳችም ተያያዥነት እንደሌለው ነው፡፡ የተጸውዖ ስሙን እየጠሩ “ስሜ አልታወቀላቸውም” ከተባለ፣ ጒዳዩ የመጠሪያ ስሙን ከማወቅና ካለማወቅ ጋር የተያያዘ አይደለም ማለት ነው፡፡
ዘፀአት 6÷3 የምንማረው፣ ርእሳን አበው የአምላክን መግቦትና ኪዳናዊ ታማኝነት በግልጽ አይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሙሴም ሆነ ከግብፅ የወጣው ሕዝብ ያየው የአምላክ የትድግና ተኣምር፣ እጅግ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ አምለክ ሁሉን ቻይ እንደ ሆነ ለርእሳን አበው አላሳየም እያልሁ አይደለም፡፡ ሙሴና ከሙሴ ጋር የነበረው ሕዝብ ያየው ክንድ ግን ይልቃል ለማለት ነው፡፡ በግብፅ ሕዝብ ላይ እጅግ በርካታ መቅሠፍቶች ሲወርዱ ከማየት ባሻገር፣ ባህር ተከፍሎ በደረቅ ምድር የተሻገረ ሕዝብ ነው፡፡
ዘፀአት 6÷3 በተመለከተ ብሉያትን የሚያጠኑ ምሁራን የተለያየ አስተያየት ቢኖራቸውም እንኳ፣ ለርእሳን አበው፣ “ስሜ አልታወቀላቸውም ነበር” ከሚለው ዐሳብ በግልጽ የምንማረው ሐቅ፣ ስም የሚለው ጒዳይ፣ ከተጸውዖ ስም ጋር ግንኙነት እንደ ሌለው፣ የተለያየ ነባቤ ቃል የሚከተሉ ነባብያነ መለኮት፣ በአጽንዖት የሚስማሙበት ሐቅ ነው፡፡
“በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” መጸለይ ማለት ወይም፣ “የክርስቶስን ስም መጥራት” ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ችግር፣ “በይሖዋ ምስክሮች” እና “በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምዕመናን ዘንድም ትክክለኛ መረዳት እንደ ሌለ መታዘብ ይቻላል፡፡ ለአባይ ነባዮች ድጋፍ የሚሰጥ አንድ ዕውቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ፣ “ለአባይ ነባያት ለምን ድጋፍ ታደርግላቸዋለህ?” ሲባል፣ “ተኣምራቶቹ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠርቶ እውን የሚሆኑ ስለሆኑ፣ እነዚህ ተኣምራት በሌላ የባዕድ መናፍስት (በርኲሳን መናፍስት) እውን የሆኑ ናቸው ማለት አይቻልም” የሚል አስተያየት ሰጥቶአል፡፡ ለዚህ ሰው የኢየሱስን ስም መጥራት ማለት የተጸውዖ ስሙን ከመጥራት ጋር አያይዞ ነው፡፡ እንግዲያው፣ “የአምላክን ስም መጥራት (ስሙን ማክበር፣ ማወደስ፣ ማግነን፣ ለስሙ መስገድ ወዘተረፈ) ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለውን ጒዳይ ለመመርመር ሙከራ እናደርጋለን፡፡
- “ስሜንም ዐውቋልና እጋርደዋለሁ” (መዝ. 91÷14)፡፡ “ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ” (መዝ. 9÷10) “ስምህ ይቀደስ” (ማቴ. 6÷9) ማለት ትርጒሙ ምንድን ነው?
- ኢየሱስ፣ “አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው” (ዮሐ. 12÷28) ሲል ምን ማለቱ ነው? አብ ስሙን የሚያከብረው እንዴት ነው?
- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው” (ኢሳ. 42÷8) የሚለው ምንባብ፣ ስለ እግዚአብሔር የተጸውዖ ስም እየተናገረ ነውን?
- ኢየሱስ፣ “ስምህን አስታወቅኋቸው፤ አስታውቃቸውማለሁ” (ዮሐ. 17÷26) ሲል ምን ማለቱ ነው? በርግጥ ኢየሱስ የአምላክን የተጸውዖ ስም ነግሮን ያውቃልን?
- “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” (ምሳ.18÷10) “ወደ ተጸውዖ ስም ይሮጣል እንዴ?” ተምሳሌታዊ ገለጻ ነው ወይስ ቊማዊ ትርጒም አለው?
- “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በአምላኩ ስም ይሄዳል፤ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሐር ስም ለዘላለም እንሄዳለን” (ሚክ. 4÷5)፤ “በአምላክ ስም መሄድ” ማለት ምን ማለት ነው?
- “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል” (ሐሥ. 15÷14)፤ “ለስሙ የሚሆን ወገን” ማለት ምን ማለት ነው?
ሐ. ሰዋስው
በዐማርኛ ሰዋስው ሕያዋንም ሆኑ ግዑዛን የሚጠሩበት መጠሪያ ሁሉ፣ “ስም” ይባላል፡፡ እንደ ታላቁ የዐማርኛ ሰዋስው ምሁር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ስም አምስት ምድቦች አሉት፡፡ እነርሱም:— (1) የተጸውዖ ስም፣ (2) የወል ስም፣ (3) የጥቅል ስም፣ (4) የቈሳቊስ ስምና (5) የነገር ስም ናቸው[2]፡፡
የተጸውዖ ስም ማለት፣ ሰው ወይም አምላክ የሚጠራበት፣ የግሉ የሆነና እርሱ ብቻ ተለይቶ የሚጠራበት መጠሪያ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ:— ምኒልክ፣ የሺእመቤት፣ ጐንደር፣ ኤርትራ፡፡ በተጸውዖ ስም ላይ እየተደረቡ የሚገቡ ስሞች ደግሞ፣ የማዕርግ (የአክብሮት) ስም ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ:— ዐፄ፣ እቴጌ፣ ጳጳስ፣ ዶክተር፣ ራስ፣ ፊት አውራሪ፣ መጋቢ፣ ጭቃ ሹም፡፡
የወል (የጋራ ወይም የጋርዮሽ) ስም ማለት ባሕርይው አንድ ሆኖ፣ የጀማ መጠሪያ የሆነው ሁሉ ነው፡፡ ለምሳሌ:— ሰው፣ አገር፣ ተራራ፣ ወንዝ፣ መጽሐፍ፣ በግ፣ አንበሳ፡፡ የጥቅል ስም ደግሞ ብዙ የወል ስም ወደ አንድ ወገን ተጠቅልሎ የሚጠራበት የማኅበር ወይም የነገድ ስም ነው፡፡ ለምሳሌ:— ፍጥረት፣ መንጋ፡፡ ሰዋስው በወል ስምና በጥቅል ስም መኻል፣ ጥሩ ዳር ድንበር ያበጀ አይመስልም፡፡ ጥናታችን ነገረ መለኮት እንጂ ሰዋስው ስላልሆነ፣ ጒዳዩን በዝርዝር አንመለከትም፡፡
የቈሳቊስ ስም፣ “ለሰው አገልግሎት የሚገባ የቤት ዕቃ ነው”[3] ብለውናል፡፡ ይኸውም:— ልብስ፣ ዐልጋ፣ ወንበር፣ ጫማ፡፡ የነገር ስም ደግሞ፣ “በዐይን የማይታይ፣ በእጅ የማይዳሰስ፣ ባሕርይንና ሥራን የሚያመለክት ቃል ሁሉ የነገር ስም ወይም የግብር ስም ይባላል”[4]፡፡ ለምሳሌ:— ንጽሕና፣ ጤና፣ ኀጢአት፣ ጽድቅ፣ ወዳጅነት፣ ብርሃን፣ ጨለማ፡፡
የአምላክ የተጸውጾ ስሞች፣ የማዕረግ፣ የወልና የጥቅል ስሞች ሆነው ግልጋሎት ላይ ውለዋል፡፡ ያህዌ (יהוה)፣ አዶናይ (אֲדֹנָי)፣ ኤል (אֵל)፣ ኤሎሂም (אֱלֹהִים)፣ ኤል ሻዳይ (אֵל שַׁדַּי)፣ ያህዌ ጸባዖት (יְהֹוָ֥ה צְבָאֽוֹת)፡፡ በዕብራይስጥ አዶናይ የሚለው ስም፣ በዐማርኛችን “ጌታ” ማለት ስለሆነ፣ የወል ስም ነው፡፡ በግሪክ ደግሞ፣ “ቴዎስ” (እግዚአብሔር) እና “ኩሪዮስ” (ጌታ) የሚሉት ስሞች የወል ስም ናቸው፡፡
ብሉያትም ሆኑ ዐዲሳት በተጸውዖ ስምና በማዕረግ ስም መካከል አንዳችም ልዩነት አላበጁም፡፡ በዚህ ረገድ የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል:—
- “ቀናተኛ” የሚለው ስም የእግዚአብሔር “ስም” እንደ ሆነ ተገልጾአል (ዘፀአት 34÷14)፡፡
- “ድንቅ መካር”፣ “ኀያል አምላክ”፣ “የዘላለም አባት”፣ “የሰላም አለቃ”፣ የሚሉት ቅጽሎች የመሲሑ “ስም” ናቸው ተብሏል (ኢሳይያስ 9÷6)፡፡
- “ቅዱስ” የሚለው ቅጽል የእግዚአብሔር “ስም” እንደ ሆነ ተነግሮናል (ኢሳይያስ 57÷15)፡፡
- “አዳኝ” የሚለው “ስም” ነው (ኢሳይያስ 63÷16)፡፡
- “ክርስቶስ” “ስም” ነው (ማቴዎስ 24÷5 ከ1ጴጥሮስ 4÷14 ጋር ያነጻጽሯል)፡፡
- “የእግዚአብሔር ቃል” “ስም” ነው (ራእይ 19÷13)፡፡
- “የነገሥታት ንጉሥ”፣ “የጌቶች ጌታ” ስም ነው (ራእይ 19÷13)፡፡
“አምላክ”፣ “ጌታ” እና “እግዚአብሔር” በሚሉት ስሞች ላይ “የእኛ” (“የእኛ አምላክ”)፣ “የእስራኤል” (“የእስራኤል አምላክ”) ወዘተ የሚሉት ቅጽሎች ተቀጽለውበት የሚገኝ ስለሆነ፣ ቃሉ የማዕረግ ስምን ማሳየቱ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ይህ ዐይነቱ የማዕረግ ስም የተጸውዖ ስም ሆኖ ሲያገለግል እንመለከታለን፡፡ በዕብራይስጥ “መሲሕ” (ማሻኽ)፣ በግሪክ “ክርስቶስ” የሚለው ቃል፣ የማዕረግ ስምን በሚያሳይ መልኩ ጥቅም ላይ ውሎአል (ለምሳሌ:— ማቴዎስ 16÷16፤ ሉቃስ 24÷46፤ ዮሐንስ 1÷41)፡፡ በአንጻሩ ደግሞ “ክርስቶስ” የሚለው ይኸው ቃል፣ የተጸውዖ ስምን በሚያመለክት መልኩ በአብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ አገልግሎአል (“ኢየሱስ ክርስቶስ” እንዲሉ)፡፡ ከዚህ የምንማረው ትልቁ ቊም ነገር፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በተጸውዖ ስምና በማዕረግ ስም መካከል አንዳችም የትርጒም/የፅንሰ ዐሳብ ልዩነት ያለማድረጋቸውን ነው፡፡
“የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” መምህራን በተጸውዖ ስምና በማዕረግ ስም መካከል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ልዩነት በማኖራቸው ምክንያት፣ ማቴዎስ 28÷19 ላይ የምናገኘውን፣ “አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ” የሚለውን የጥምቀት ቀመር፣ ሰዎችን በማጥመቅ ሂደት ውስጥ ተፈጻሚ ልናደርገው አንችልም ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ፣ “አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ” የሚሉት ቃላት የተጸውዖ ስም ሳይሆኑ፣ የማዕረግ ስም ናቸው፤ በማዕረግ ስም ማጥመቅ በትክክል እግዚአብሔርን አያመለክትም (በግእዝ ቋንቋ፣ “አብ” ስንል፣ “አባት” ማለታችን፣ “ወልድ” ስንል፣ “ልጅ” ማለታችን ነውና፡፡ ብዙ አባቶች ብዙ ልጆች ባሉበት ምድር በዚህ ዐይነት መልኩ ጥምቀትን ማካሄድ ስሕተት ነው) ባዮች ናቸው[5]፡፡
በብሉይ ኪዳንም ሆነ በዐዲስ ኪዳን፣ በተጸውዖ ስምና በማዕረግ (በወል) ስም መካከል አንዳችም የይዘት ልዩነት እንደ ሌለ ከላይ ተመልክተናል፤ ይህ አንደኛውና መሠረታዊው ነጥብ ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ፣ በማቴዎስ 28÷19 ጌታ፣ “በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” አጥምቁ ብሎናል፡፡ እነርሱ እንደሚሉት በማዕረግ ስምና በተጸውዖ ስም መካከል የይዘት ልዩነት ቢኖር ኖሮ፣ ጌታ በማዕረግ ስም አጥምቁ የሚል ትእዛዝ አይሰጠንም ነበር፡፡
በአጠቃላይ በማዕረግ ስምና በተጸውዖ ስም መካከል ያለው ልዩነት የሰዋስው ስያሜ ልዩነት እንጂ፣ የፅንሰ ዐሳብ (የትርጒም) ልዩነት እንዳልሆነ በግልጽ መረዳት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቃችን ወይም ማጥመቃችን፣ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ሥር ማደራችንን የሚያሳይ ነው፡፡
ስለዚህ ሰይጣንን፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ብቻ ሳይሆን፣ “በወልድ ስም”፣ “ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ስም”፣ “በአዳኙ ስም”፣ “በክርስቶስ ስም” ወዘተ ብለን በመቃወም ማብረራችን አግባብ ነው፡፡ እነዚህ ስሞች ሁሉ የሚያመለክቱት ያው አንዱን ክርስቶስ፣ አንዱን ጌታ ነውና፡፡
እነዚህ ሁሉ ስሞች የኢየሱስ ስሞች እንደ ሆኑ የነገሩን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ይጠራባቸው ዘንድ እርሱን ስለሚመጥኑት፣ ባሕርዩንም ስለሚያመለክቱ ነው፡፡ “መቶ አለቃ” የሆነን ወታደር፣ “ሃምሳ አለቃ” ወይም፣ “ሻለቃ” ወይም ደግሞ፣ “ኮሎኔል” ብሎ መጥራት ስሕተት ነው፡፡ ሃምሳ አለቃ የሚለው ማዕረግ የግለሰቡን ሥልጣን የሚያሳንስ ሲሆን፣ ሻለቃ ወይም ኮሎኔል ብሎ መጥራት ከግለሰቡ ሥልጣን በላይ ስለሆነ ስሕተት ነው፡፡ ኢየሱስ በተለያዩ ስሞች የተጠራው፣ ስሞቹ እርሱን ስለሚመጥኑት ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ፣ አንዱን የጌታ ስም ከሌላው ስም ማበላለጥ ትክክል አይደለም፡፡
ዳዊት ጐልያድን:—
- “ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ” (1ሳሙኤል 17¸45)፡፡
ሲለው፣ ዳዊት የውክልና ጦርነት እንደሚዋጋ የሚያሳይ እንጂ፣ ወንጭፉን ባስወነጨፈ ጊዜ ሁሉ፣ የአምላክን ስም መጥራቱን የሚያመለክት አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ መልእክት ይህ ሆኖ ሳለ፣ የያህዌን ስም (የኤልሻዳይን ወዘተ ስም) ጠርቶ ወንጭፉን ቢያስወነጭፍ ደግሞ አንዳችም ስሕተት ያለበትም፤ ሊኖርበትም አይችልም፡፡ ስለዚህ የክርስቶስን ስም እየጠራን አጋንንትን ማስወጣት እንችላለን፤ ነገር ግን የጌታን ስም ጥሩ የሚለውን ቃል የተጸውዖ ስምን ከመጥራት ጋር ልናያይዘው አንችልም፡፡
በዚህ ክፍል ዳዊት፣ “በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ” ሲል፣ ስሜ እግዚአብሔር ተብሎ ወይም እኔና እግዚአብሔር አንድ አካል ሆነን እመጣብሃለሁ ማለቱ ሳይሆን፣ በተገዳደርኸው በእግዚአብሔር ሥልጣን እመጣብሃለሁ ማለቱ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ኢየሱስ፣ “በአባቴ ስም መጣሁ” ሲል፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” መምህራን እንደሚያስተምሩት የአብና የወልድ ስም አንድ ነው ወይም አብና ወልድ አንድ አካል ናቸው ለማለት ተፈልጎ ሳይሆን፣ በአባቴ ሥልጣን ወይም አባቴን ወክዬ መጥቻለሁ ማለቱ ነው፡፡
በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ስም የሚለው ቃል 156 ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሁሉ በእነዚህም መጻሕፍት ስም ባሕርይን፣ ግብርንና ሥልጣንን የሚያመለክት ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ በሌላ አነጋገር “በ__ስም” ማለት “በ__ሥልጣን” ማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በስሜ አጋንንትን” አውጡ ሲለን[6]፣ የዚህ ዓለም ገዢበሆነው በዲያብሎስና በጭፍሮቹ ፊት ክርስቶስን ወክላችሁ ቅረቡ ማለት ነው—ከላይ ባየነው ክፍል ዳዊት፣ ያህዌን ወክሎ በጎልያድ ፊት እንደ ቀረበው ማለት ነው፡፡ “የኢየሱስን ስም” መጥራት ብቻ በራሱ ተኣምር የሚያደርግ ቢሆን ኖሮ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ያልተቀበሉ አይሁድ፣ የኢየሱስን ስም በመጥራት አጋንንትን ለማውጣት ያደረጉት ሙከራ አይከሽፍም ነበር፡፡ እንዲያውም ይህን ለማድረግ ሙከራ ባደረጉት ሰዎች ላይ ርኲስ መንፈስ ያደረበት ሰው ክፉኛ እንዳጠቃቸው ከዚህም የተነሣ፣ ከነበሩበትን ቤት ዕርቃናቸውን እንደፈረጠጡ እንመለከታለን፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ፣ “ኢየሱስ” የሚለውን የተጸውዖ ስም መጥራት ሳይሆን፣ በዚህ ስም የሚጠራውን ታላቅ ጌታ በእምነት ወክሎ የመቅረቡ ጕዳይ፣ ዋነኛ ነገር እንደ ሆነ የሚያሳስብ ነው፡፡
- “እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ ‘ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዛችኋለሁ!’ እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኲሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤ የአይሁዳዊው የካህናት አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር፡፡ ርኲስ መንፈሱም፣ ‘ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?’ አላቸው፡፡ ከዚያም ርኲስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቊታቸውን ሸሹ” (ሐዋርያት ሥራ 19÷13-16)፡፡
ይህ ታሪክ በኢየሱስ ስም ማለት የተጸውዖ ስሙን እንደ ቀመር መጥራት እንዳልሆነ አስተማሪ ነው፡፡
መ. ስምን መቀደስ ለስሙ ባለቤት ዕውቅናና ክብር መስጠት ነው
በሚከተሉት ምንባባት ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ከእግዚአብሔር ባሕርይና ግብር ጋር በተለዋዋጭነት እንዴት እንደ ቀረበ ልብ ይሏል:—
- “አቤቱ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ” (መዝሙር 18÷49)፡፡
- “ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው” (መዝሙር 68÷4)፡፡
- “ይህን ፍጥረትህን ዐስብ፤ ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፣ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ” (መዝሙር 74÷18)፡፡
- “አቤቱ አምላኬ ሆይ፤ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፤ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ” (መዝሙር 86÷12)፡፡
- “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራለሁ፤ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ” (መዝሙር 22÷22)፡፡
- “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጉባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ” (ዕብራውያን 2÷12)፡፡
በእነዚህ ምንባባት የእግዚአብሔር ስም ከእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ግብርና ሥልጣን ጋር መሳ ለመሳ ተነጻጽሮ ቀርቧል፡፡ መዝሙረኛው፣ “ለስሙ ዘምሩ” ወይም “ለስምህ እዘምራለሁ” ወይም ደግሞ “ስምህን አከብራለሁ” ሲል፣ ከእግዚአብሔር በተለየ መልክ ለስምህ ብቻ ማሕሌተ እግዚአብሔር እቆማለሁ እያለ አይደለም፡፡ “ሰነፍ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ስም አስቈጣ” ማለት፣ ራሱን እግዚአብሔርን አስቈጣ ወይም እግዚአብሔርን አዋረደ ማለት እንጂ፣ ከእግዚአብሔር በተለየ መልኩ ስሙ ብቻውን ይቈጣል፣ ይዋረዳል ወይም ይከብራል ማለት አይደለም፡፡
ሠ. የአምላክ የተጸውዖ ስሞች የአምላክን ባሕርይና ግብር አመልካች ናቸው
ዕብራውያን አንዴ ከተጻፉ፣ በምንም መልክ መጥፋት፣ መደለዝና መሰረዝ የለባቸውም የሚባሉ የእግዚአብሔር የተጸውዖ ስሞች የሚከተሉ ናቸው:— ያህዌ (יהוה)፣ አዶናይ (אֲדֹנָי)፣ ኤል (אֵל)፣ ኤሎሂም (אֱלֹהִים)፣ ኤል ሻዳይ (אֵל שַׁדַּי)፣ ሻዳይ (שַׁדַּי)፣ ያህዌ ጸባዖት (יְהֹוָ֥ה צְבָאֽוֹת)፣ ጸባዖት (צְבָאֽוֹת)፡፡
“ያህዌ” ማለት፣ “እኔ እኔ ነኝ” ወይም “እኔ ነኝ” ማለት ነው፡፡ “አዶናይ”፣ “አለቃዬ” ወይም፣ “ጌታዬ” ማለት ነው፡፡ “ኤል”፣ “አምላክ” ወይም “መለኮት” ማለት ነው፡፡ ኤሎሂም የብዙ ቊጥርን አመልካች የወገን ግጽል ሲሆን፣ “አምላክ መሆን” ወይም “አምላክነት” እንደ ማለት ነው፡፡ “ኤል ሻዳይ” ማለት፣ “ሁሉን የሚችል አምላክ” ማለት ነው፡፡ “ያህዌ ጸባዖት”፣ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ እነዚህ ስሞች የአምላክን ባሕርይ (ለምሳሌ:— ሁሉን ቻይ) እንዲሁም ግብር (ምሳሌ:— እረኛዬ) አመልካች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ የአምላክ ስምን ማወቅ ማለት፣ ይህን የአምላክ ባሕርይ እንዲሁም ግብር ማወቅ ማለት ነው፡፡
ከእነዚህ ስሞች ጋር እየተጫፈሩ (እየተዛረፉ) የሚነገሩ፣ የአምላክን ግብርና ባሕርይ የሚያሳዩ በርካታ ስሞች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እነሆ:— “ያህዌ ሮሂ” አምላክ እረኛዬ ነው (መዝ. 23÷ 1)፡፡ “ያህዌ ይርኤ” አምላክ መጋቢዬ ነው ወይም ያዘጋጅልኛል (ዘፀ. 15÷25-26)፡፡ “ያህዌ ንሲ” እግዚአብሔር ዐላማዬ ነው (ዘፀ. 17÷11-12)፡፡ “ያህዌ ማኳዶሽ” የሚቀድስ እግዚአብሔር፣ (ዘሌ. 11÷44)፤ “ያህዌ ሻሎም” የሰላም አምላክ (መሳ. 17÷6)፡፡ “ያህዌ ጽድቅኑ” እግዚአብሔር ጽድቄ ነው (ኤር. 23÷5-6)፡፡ “ያህዌ ሻማኽ” እግዚአብሔር ይታያል ወይም እግዚአብሔር እዚያ ነው (ሕዝ. 48÷35)፡፡
አቢግያ ስለባሏ ናባል ለንጉሥ ዳዊት እንዲህ አለች:—
- “በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፤ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፤ ስንፍናም አድሮበታል” (1ሳሙ. 25÷25)፡፡
በዕብራይስጥ፣ “ናባላኻ” ማለት “ጅል”፣ “ተላላ” ማለት እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ ግለሰቡም እንደ ስሙ ግብሩና ጠባዩ ጅል ነው፡፡ በዕብራይስጥ ሰይጣን (שָׂטָן) ማለት፣ “ፈታኝ” ወይም “ባላንጣ” (ጠላት) ነው፡፡ ስያሜው ግብሩን አመልካች ነው፡፡
የእግዚአብሔር ስሞች የእግዚአብሔርን ባሕርይ ያሳያሉ ሲባል ግን፣ ሁሉን የአምላክ ባሕርይ፣ ሁሉን የአምላክ ግብር በአንድ ቀንብቦ የሚይዝ የአምላክ የተጸውዖ ስም አለ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ:— “ኤልሻዳይ” (אֵל שַׁדַּי)[7] የሚለውን የዕብራይስጥ ስም፣ አብዛኞቹ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒሞች፣ “ሁሉን ቻይ አምላክ ” (God Almighty) ብለው በቊሙ ተርጒመውታል፡፡ ኤል (אֵל) “አምላክ” እንዲሁም፣ “ሻዳይ” (שַׁדַּי) “ከሃሊ” ወይም “ቻይ” ከሚሉት ሁለት ቃላት በአንድ የተጫፈረ ነው፡፡ እግዚአብሔር፣ “ሁሉን ቻይ አምላክ” መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ “ሁሉን ቻይ ብቻ ነው” ማለት ግን ትክክል አይደለም፡፡ የአምላክን ልዕልና የሚገልጹ ሌሎች እጅግ በርካታ የፍጽምና ባሕርያት አሉና፡፡
ኤሎሂም (אֱלֹהִים) ወይም ኤሎዋሃ (אֱלֹוהַּ) የሚለው የወል ስም፣ “አምላክ” ወይም “ጌታ” የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፣ ከሌሎች የአምላክ ስሞች ጋር ተጫፍሮ ሲቀርብ፣ በተገናኝ ትርጓሜው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ወይም ሥራ ያውጃል፤ ለምሳሌ ኤልኤልዮን (אֵל עֶלְיוֹן) “ልዑል (ምጡቅ) እግዚአብሔር” ማለት ነው (ዘፍጥረት 14÷18:19:20:22)፡፡ ኤልኦላም (אֵ֥ל עוֹלָֽם) “ዘላለማዊ አምላክ” ማለት ነው፡፡ ኤልሮሂ (אֵ֣ל רֳאִ֑י) “የሚያይ/የሚመለከት እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሥሉጥ ላዕለ ኵሉ ነው፤ ዘላለማዊ ጌታ ነው፤ ችግረኞችን ከነችግራቸው አብጠርጥሮ የሚመለከት አምላክ ነው፡፡ ለናሙናነት በቈነጠርኋቸው በእነዚህ ስሞች ውስጥ የምናስተውለው ቊም ነገር ስም ባሕርይን፣ ግብርንና ሥልጣንን አመላካች ሰንደቅ እንዲሁም ዐላማ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ነው ብሉያት እግዚአብሔር የተጠራባቸው ስሞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ባሕርይና ሥራ ያትታሉ ያልነው፡፡
ረ. የአምላክን የተጸውዖ ስም ማንም አያውቅም
ከየትኛውም ስም ይልቅ፣ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር የተጸውዖ ስም፣ እንደ ሆነ በብዙ ምሁራን የሚታመነው “ያህዌ” (יהוה) የሚለው ስም ነው፡፡ ይህ ስም በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 6,828 ጊዜ የምናገኘው ሲሆን፣ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ብቻ እንኳ 700 ጊዜ ያህል ተደጋግሞ ጥቅም ላይ ውሏል[8]፡፡
እኛ ባለንበት የታሪክ ዘመን፣ የዚህ የአምላክ ስም ትክክለኛ ንበት የቱ እንደ ሆነ (እንዴት እንደሚነበብ) የሚያውቅ አንድም ሰው ወይም የሃይማኖት ተቋም የለም፡፡ ይህ ስም በአንዳች ግለሰብ ወይም የሃይማኖት ተቋም ያልታወቀበትን ዐቢይ ምክንያት ላብራራ፡፡ እነሆ:—
ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ፣ የጥንት ዕብራውያን ያህዌ (יהוה—YHWH) የሚለውን የእግዚአብሔርን የተጸውዖ ስም መጥራት ስለሚፈሩ፣ ያህዌ በሚለው ስም ፈንታ አዶናይ (אֲדֹנָי—Adonai) የሚለውን የወል ስም (አዶናይ ማለት “ጌታ” ማለት ነው)፣ ያህዌ በሚለው ስም ምትክ ተክተው ይጽፉ እንዲሁም ይናገሩ ነበር፡፡ ይህን የአምላክ ስም መጥራት እንዲፈሩ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት፣ “የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” የሚለው፣ ከዐሥርቱ ትእዛዛት መኻል ሦስተኛውን ሕግ በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ነው፡፡ ይኸውም ተሳስተን ባልሆነ መንገድ ስሙን ጠርተነው ከሆነ፣ ቅሥፈት ያጋጥመናል የሚል ፍርሓት፡፡
ይህ ብቻ አልነበረም፣ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ያባዙ የነበሩት ጸሓፍት (እንዳሁኑ የማተሚያ መሣሪያ በወቅቱ ስላልነበር) ያህዌ የሚለው የአምላክ ስም በሚገኝበት ቦታ ሁሉ፣ እጃቸውን በሣሙና ሙልጭ አድርገው ይታጠቡ እንዲሁም ብዕራቸውን በንጹሕ ውሃ ያለቀልቁ ነበር፡፡ ይህ ማለት ደግሞ፣ አንድ ጸሓፊ ብሉያትን ገልብጦ እስኪጨርስ ድረስ ወደ ሰባት ሺሕ ጊዜ ያህል እጁንና ብዕሩን በዚህ መልክ ያጸዳ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ድካም የአምላክን ስም በከንቱ ላለመጥራት እንዲሁም ለስሙ የሚገባውን ትልቅ ክብር ለመግለጽ ነው፡፡ስለዚህ የአምላክህ የእግዚአብሔር ስም በከንቱ አትጥራ የሚለውን ሕግ ላለማፍረስ በሚያደርጉት ትንቅንቅ/ጥንቃቄ፣ ያህዌ የሚለውን የተጸውዖ ስም ከመጠቀም ይልቅ፣ አዶናይ የሚለውን የወል ስም ተክተው መጠቀም ጀመሩ፡፡ በዚህም መንገድ ያህዌ የሚለውን ስም ከሃይማኖት ሥርዐታቸው ውስጥ አስወጡ፡፡
የጥንት ዕብራውያን ድምፅ ተቀባይ ፊደላትን (consonants) ብቻ በመጻፍ፣ በሚያነቡበት ጊዜ ብቻ ድምፅ ሰጪ ፊደላትን (vowels) እያስገቡ ጽሑፋቸውን ያነቡ ነበር፡፡ በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ፣ የዕብራይስጥ ቋንቋ እያደገ ስለመጣ፣ ድምፅ ተቀባይ ፊደላትን ከድምፅ ሰጪ ፊደላት ጋር አሰባጥሮ መጻፍ ተጀመረ፡፡ ማሶራውያን (Masoretes) የሚባሉት የዕብራይስጥ ቋንቋ ሊቃውንት፣ ለዕብራይስጥ ፊደላት አናባቢ ምልክቶችን በመፍጠር፣ እነዚህን ምልክቶች ከተናባቢ ሆህያት ጋር አቀናጅተው መጻፍ ሲጀምሩ፣ ያህዌ ለሚለው ስም ግን አናባቢ ሳያበጁለት ቀሩ—ምክንያቱም ያህዌ የሚለው ስም ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ “አዶናይ” (אֲדֹנָי)የሚለውን ስም ተክቶ የመናገር ጠንካራ ልማድ ነበረና፣ በዚህ ምክንያት ለዚህ ስም አናባቢ ማበጀት አላስፈለጋቸውም[9]፡፡ “ልማድ ሲሰለጥን ቀኖና ይሆናል” ይሏል ይኸው ነው፡፡ ይህ አናባቢ ያልተበጀለት ያህዌ የሚለው ስም ድምፅ ተቀባይ ፊደላት— יהוה—YHWH ቴትራግራሞቶን በመባል ይታወቃል፡፡
ነገር ግን አይሁዶች ያህዌ የሚለውን ስም እግዚአብሔርን ከመፍራትና ስሙን ከማክበር የተነሣ ስለማይጠሩት፣ ቋንቋው ሲያድግ የቀድሞውን ትክክለኛ አነባበብ ዐዲሱ ትውልድ ሳያውቀው ቀረ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ዕብራውያን አዶናይ (אֲדֹנָי—Adonai) በሚለው የአምላክ ስም ላይ የሚገኙትን ድምፅ ሰጪ ሆህያት ማለትም “a, o, a” ያህዌ በሚለው ድምፅ ተቀባይ ፊደላት (ቴትራግራማቶን) ውስጥ በመጨመር፣ YaHoWaH ወይም YaHWaH ተብሎ እንዲነበብ አደረጉ፡፡ ይህ እንግዲህ የማሶራውያኑ ፈጠራ እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡
በዚህ ቦታ ልናስተውለው የሚገባን ትልቁ ቊም ነገር፣ ቴትራግራማቶንን ምንም ብለን ማንበብ ያለመቻላችንን ነው፡፡ ምክንያቱም የድምፅ ተቀባይ ፊደላት ቅንጅት ብቻ ስለሆነ፤ ለማንበብ ደግሞ ድምፅ ሰጪ ፊደላት የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ ሐቅ የተነሣም ነው፣ ያህዌ የሚለው ስም ሰው ሠራሽ ስም ነው ሚባለው[10]፡፡ ነገር ግን ያህዌ የሚለው ስያሜ ቴትራግራማቶን ሊነበብበት ከሚችልባቸው እጅግ በርካታ አማራጮች መኻል አንዱ መሆኑን ልብ ይሏል[11]፡፡
ልብ እንበል በእነዚህ ምንባባት፣ የአምላክ ስም ያህዌ ነው፤ ይህን ስም ለድነታችሁ ዋስትና ነውና ቋጥራችሁ ያዙት አልተባልንም፤ ወይም ወደዚያ የሚያንደረድር አንዳችም ጠቋሚ ዐሳብ አልቀረበም፡፡ በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ፣ ኢየሱስ የትኛውንም የብሉይ ኪዳን ስመ አምላክ በመጥራት ለደቀ መዛሙርቱ አይናገር እንጂ፣ ኢየሱስ በሕይወቱም ሆነ በሞቱ አባቱን በሚገባ መንገድ ተርኰታል (ዮሐንስ 1÷18)፡፡ እኛም፣ “ከአባቱ ዘንድ የመጣውንም የአንድያ ልጅን ክብር አይተናል” (ዮሐንስ 1÷14)፡፡
ከእነዚህ መረጃዎች በግልጽ የምንረዳው ቊም ነገር፣ የአምላክን የተጸውዖ ስም አላወቅንም ማለት፣ ስሞቹ የሚወክሉትን አምላክ አናውቅም ማለት አይደለም፡፡ የተጸውዖ ስሞች ንበት ጠፋብን ማለት፣ አምላክ ተሰወረብን ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ለስምህ እሰግዳለሁ ስንል፣ ለተጸውዖ ስምህ አደገድጋለሁ ማለታችን አይደለም፡፡ ነገር ግን የተጸውዖ ስሙ ባለቤት የህልውናዬ ዐልፋና ዖሜጋ ነው ማለታችን እንጂ፡፡ ያህዌ የሚለው ስም ትርጓሜው፣ የእግዚአብሔርን ታዳጊነትና በድነት ውስጥ ያለውን ሉዓላዊ ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ያህዌ ማለት በሁሉ ላይ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው ታዳጊ አምላክ ማለት ነው፡፡ ቴትራግራማቶን እንዴት እንደሚነበብ አይታወቅ እንጂ፣ ይህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ታዳጊና ልዑል አምላክ እንደ ሆነ የዐዲስ ኪዳን ምንባባትም በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔርን ማንነትና የድነት መንገድ እጅግ በተፍታታ መንገድ ገልጸውልናልና፡፡
ሰ. የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም የዕብራይስጥ የተጸውዖ ስሞችን አልተጠቀመም
ከዚህም ይልቅ አስደናቂ የሆነው ክሥተት፣ የቴትራግራማቶን ንበት በትክክል በሚታወቅበት ዘመን፣ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ የተተረጐመው የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም (ከ300 ዓ.ቅ.ክ[12] እስክ 200 ዓ.ቅ.ክ ባለው ጊዜ)፣ ያህዌ የሚለውንም ሆነ ሌሎችን የአምላክ የተጸውዖ ስሞች አንዳችም ጊዜ እንኳ አልተጠቀመም፡፡ የአምላክን የተጸውዖ ስሞች ሁሉ፣ በጽርዕ (በግሪክ ቋንቋ) “ቴዎስ” (θεὸς ማለትም እግዚአብሔር) እንዲሁም “ኩሪዮስ” (κύριός ማለትም ጌታ) በሚለው የግሪክ ቃል ብቻ ወስኖአቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ከብሉይ ኪዳኑ የዕብራይስጥ ቅጅ ይልቅ፣ ለሰብዓ ሊቃናት ትርጒም ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጡ ልብ ይሏል፡፡
ሸ. የዐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን የዕብራይስጥ ስም አልተጠቀሙም
የዐዲስ ኪዳን ጸሓፍት በጽሑፎቻቸው ውስጥ አንድም ጊዜ፣ የአምላክን የተጸውዖ ስም በጽሑፋቸው ውስጥ አልተጠቀሙም፡፡ የዐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን እጅግ በርካታ ጊዜ ብሉያትን ጠቅሰውና አጣቅሰው ሲጽፉ[13]፣ አንድ ጊዜ እንኳ የአምላክን የዕብራይስጥ ስም በጽሑፋቸው ውስጥ ሲጠቅሱ አንመለከትም፡፡ ይህን የአምላክ ስም በዐዲስ ኪዳን በኵረ ጽሑፋት ውስጥ አንድም ጊዜ እንኳ ያለመጥቀሳቸው ነው[14]፡፡ በዚህ ቦታ ልንጠይቀው የሚገባን መሠረታዊ ጥያቄ፣ የዐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ምን ነክቷቸው ነው ይህን ስም በጽሑፋቸው ውስጥ ሳይጠቅሱ ያለፉት—ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳ ይህን ስም መጥቀስ እንዴት አልቻሉም? ይህ ብቻ አይደለም፣ እግዚአብሔር የተጠራባቸው የብሉይ ኪዳን የተጸውዖ ስሞች በርካታ ቢሆኑም፣ አንዱም ስም በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎ አይገኝም፡፡
ቀ. ቴዎስና ኩሪዮስ ከክርስትና በፊት ለጣዖት ይውሉ የነበሩ ስያሜዎች ናቸው
በዐዲስ ኪዳን ግሪክ ቋንቋ፣ በአምላክ የወል ስምነት ተደጋግመው የተጠቀሱት ስሞች “ቴዎስ” (θεὸς—እግዚአብሔር) እንዲሁም “ኩሪዮስ” (κύριός—ጌታ) የሚሉት ስሞች ናቸው፡፡ ከዘመነ ክርስትና በፊት፣ እነዚህ ስሞች የግሪክ ጣዖታትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ስሞች መሆናቸውን የመስኩ ምሁራን በግልጽ ያስረዳሉ፡፡
በኦሮምኛ “ጎፍታ/ዋቀዮ”፣ በጒራጊኛ “ጐይታ”፣ በሲዳምኛና በጌዴዎኛ “መገኖ”፣ በትግርኛ “አምላኽ”፣ በወላይትኛ “ጦሳ”፣ በዐማርኛ “እግዚአብሔር” ወዘተ የሚሉት ስሞች፣ የወል ስም መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለባዕድ አምልኮም ሆነ ለመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ያላንዳች ጥያቄና ማመንታት ተጠቅመንባቸዋል፤ እየተጠቀምንባቸውም እንገኛለን[15]፡፡
በ. ዐዲስ ኪዳን ለኢየሱስ ትልቅ ክብር ሰጥቶአል
ልክ ነው ዐዲስ ኪዳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ እንዲያውም ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ስም ያለውና ጒልበት ሁሉ የሚንበረከክለት ስም፣ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደ ሆነ ይናገራል (ፊልጵስዩስ 2÷9-11፤ ኤፌሶን 1÷21)፡፡ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረው ጸሎት ላይ፣ “ስምህ ይቀደስ በሉ” ወይም “ስሙን ቀድሱ” ተብለን ነበር (ማቴዎስ 6÷9)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሚያብራራልን በሚከተለው መልክ ነው፡፡
- በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተሰብሰቡ (ማቴዎስ 18÷20፤ 1ቆሮንቶስ 5÷4)፡፡
- በጌታ ስም አጋንንትን አውጡ (ሉቃስ 10÷17፤ ሐዋርያት ሥራ 16÷18)፡፡
- በኢየሱስ ስም ንስሓና የኀጢአት ይቅርታ እንዲሁም ድነትን ስበኩ፣ (ሉቃስ 24÷47፤ ሐዋርያት ሥራ 4÷12፤ ዮሐንስ 1÷12፤ ሐዋርያት ሥራ 10÷43፤ 1ዮሐንስ 3÷23፤ 5÷13)፡፡
- ጸሎታችሁን በኢየሱስ ስም አድርሱ (ዮሐንስ 14÷13-14፤ 15÷16፤ 16÷23-24)፡፡
- መንፈስ ቅዱስ የሚላክላችሁ በኢየሱስ ስም ነው (ዮሐንስ 14÷26)፡፡
- በኢየሱስ ስም ሕሙማንን ፈውሱ፤ ሽባውን ተርትሩ (ሐዋርያት ሥራ 3÷16፤ 4÷7-10:30)፡፡
- በሰማይም ሆነ በምድር አቻ የሌው ስም የኢየሱስ ስም ነው (ኤፌሶን 1÷21፤ ፊልጵስዩስ 2÷9-11)[16]፡፡
“ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለው የዐማርኛ ስያሜ ከግሪክ አቻው በቀጥታ የተወረሰ ነው፡፡ “ኢየሱስ” (በዕብራይስጥ የሹዋ יֵשׁוּעַ በግሪክ የሱስ Ἰησοῦς) ማለት “እግዚአብሔር ያድናል” ማለት ሲሆን፣ “ክርስቶስ” (በዕብራይስጥ ማሺያኽ מָשִׁיחַ፣ በግሪክ ክርስቶስ χριστός) ማለት ደግሞ የተቀባ ማለት ነው፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሰዎች በብዛት ይጠሩበት የነበረ ስም ነበር፡፡ “ኢየሱስ” ለሚለው የግሪክኛና የዐማርኛ ስያሜ የዕብራይስጥ አቻው፣ የሹዋ ወይም ኢያሱ የሚለው የተጸውዖ ስም ነው—በድምፀትም በትርጒምም፡፡ ጌታ በተወለደበት በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከየትኛውም የዕብራይስጥ ስም ይልቅ ኢየሱስ የሚለው ስም የብዙ ሰዎች መጠሪያ እንደ ነበር ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ምሁሩ ፕሮፌሰር ጌሪ ሃበርማስ፣ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ከዘጠና ዘጠኝ ስሞች መኻል ሃያ ሁለቱ ኢየሱስ የሚለው ስም እንደ ሆነ በማስረጃ ይሞግታል፡፡ ይህ ማለት ከአምስት ሰዎች መኻል አንዱ፣ ስሙ ኢየሱስ ወይም የሹዋ ነው ማለት ነው[17]፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ “የሐዋርያት” ቤተ ክርስቲያን መምህራን ኢየሱስ የሚለው ስም አምላክ ለዘመናት ደብቆ ያኖረው ስም ነው የሚለው ትምህርታቸው ፉርሽ ነው፡፡
በፊልጵስዩስ መልእክት ላይ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመስቀል ሞቱና ሞትንም ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ:—
- “እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (2÷9-11) የሚል ቃል እናነባለን፡፡
በዚህ ቦታ ኢየሱስ የሚለው ስም፣ ጌታ ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት ይጠራበት የነበረው ስም ነው፡፡ ይህ ምንባብ እየተናገረ ያለው ኢየሱስ ስለሚለው የተጸውዖ ስም ሳይሆን፣ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ከፍተኛ ክብር እንደ ተጐናጸፈ የሚያሳይ ነው (ኤፌሶን 1÷21፤ ዕብራውያን 1÷4-5)፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ የሚለው ስም ቀድሞውኑ ይጠራበት የነበረ ስም ነውና፡፡ ንጉሥ ዳዊት፣ “አቤቱ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ” (መዝሙር 18÷49) እንዲሁም “ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው” (መዝሙር 68÷4) ሲል፣ አምላክ ለሚጠራበት የተጸውዖ ስም እዘምራለሁ ማለቱ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ጒልበት ሁሉ የሚንበረከክለት ስም የኢየሱስ ስም ነው ማለት የተጸውዖ ስሙ፣ ከኢየሱስ በተለየ መልኩ ስግደት ይቀርብለታል ማለት አይደለም፡፡
ከላይ በስፋት ለመመልከት እንደ ሞከርነው ስም፣ የስሙ ባለቤት ያለውን ባሕርይ፣ ግብርና ሥልጣን የሚያመለክት ስያሜ ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ስም ተሰብሰቡ ማለት በምትሰበሰቡበት ጊዜ በኢየሱስ ስም በሉ ማለት ሳይሆን፣ በእርሱ ሥልጣን (ዕውቅና) ሥር ስብሰባችሁን አካሂዱ ማለት ነው (ማቴዎስ 18÷20፤ 1ቆሮንቶስ 5÷4)፡፡
ድነትን ወይም ንስሓና የኀጢአት ይቅርታን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስበኩ ማለት፣ ኢየሱስ ለሰዎች ድነት ያደረገውን ገድል ተርኩ ወይም ሞትና ትንሣኤውን ስበኩ ማለት ነው (ሉቃስ 24÷47፤ ሐዋርያት ሥራ 4÷12፤ ዮሐንስ 1÷12፤ ሐዋርያት ሥራ 10÷43፤ 1ዮሐንስ 3÷23፤ 5÷13)፡፡ በዐጭሩ ስም የስሙ ባለቤት ካለው ባሕርይ፣ ግብርና ሥልጣን የተለየ ፋይዳ ያለው አይደለም፡፡
እንግዲያው እውነቱ ይህ ከሆነ፣ በጸሎታችን ማጠናቀቂያ ላይ፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ብለን ጸሎታችንን ማሳረግ የለብንም ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” መጸለይ ማለት፣ እንደ ክርስቶስ አስተምህሮና እንደ እርሱ ፈቃድ በመጸለይ የእርሱን ክብር መሻት እንደ ሆነ ከላይ ለማየት ሞክረናል፤ “ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል” (1ዮሐንስ 5÷14)፡፡ ስለዚህ አንድን ጸሎት ክርስቲያናዊ ጸሎት የሚያሰኘው በጸሎቱ መቋጫ ላይ፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ማለታችን ሳይሆን፣ ከጸሎቱ ጅማሬ እስከ ጸሎቱ ፍጻሜ የክርስቶስን ዐሳብ የሚወክልና የእርሱን ክብር የሚሻ ጸሎት መሆኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ጸልዩ ሲለን፣ ቀዳማይ መልእክቱ ይኸው ነው፡፡ ይዘቱ እርሱን የሚያስከብር ከሆነ፣ በጸሎቱ ማጠናቀቂያ ላይ፣ “በኢየሱስ ስም” ማለታችን አንዳችም ክፋት የለውም—ለእርሱ ያለንን አክብሮት የሚያሳይ እስከ ሆነ ድረስ አግባብ ነው፡፡
ተ. ማጠቃለያ
የጎጃሙን በላይ ዘለቀ በተመለከተ ሲነገር የሰማሁት አንድ ወግ አለ፡፡ በላይ ዘለቀ ከድል በኋላ ለተዋጊዎቻቸው ሥልጣን መስጠት ነበረባቸው፡፡ ቀኝ አዝማች፣ ግራ አዝማች፣ ቀኝ ጌታ፣ ደጃዝማች፣ ፊት አውራሪ፣ አዛዥ፣ ባለምባራስ…እያሉ ጦረኛውን ሁሉ ሲሾሙ ዋሉ፡፡ “ራስ” የሚል ትልቅ ማዕረግ የተከናነበ ተመስገን ፈንታ የተባለ ሰው፣ ጠጋ ብሎ፣ “እኔን ራስ አልኸኝ፤ ታዲያ ለአንተ ምን ተረፈልህ?” ቢላቸው፡፡ “ተው እባክህ፤ እኔ እናቴ ገና በጧቱ፣ ‘በላይ’ ብላኛለች፤ የሁሉ በላይ ነኝ” አሉ ይባላል፡፡
የተጸውዖ ስም ታላቅነት የሚወሰነው፣ የስሙ ባለቤት ማን ነው በሚለው ማመሳከሪያ ነው፡፡ የእስክንድርያው ሊቃነ ጳጳሳት አርዮስ ጥሩ ምግባር ቢፈጽም ኖሮ፣ አርዮስ የሚለው ስም የጥሩ ሰው ስያሜ ይሆን ነበር፡፡ ኀይሌ ገብረ ሥላሴ የሚለው ስም ዝነኛ የሆነው፣ የስሙ ባለቤት መልካም ምግባር ፈጽሞ በመገኘቱ ነው፡፡ የተጸውዖ ስምን የስሙ መጠሪያ ከሆነው ሰው አንጻር መመልከት የተለመደ ተፈጥሮአዊ አካሄድ ነው፡፡ የአምላክ የተጸውዖ ስሞች በትብብር የአምላክን ባሕርይና ግብር ለማሳየት ሙከራ ቢያደርጉም፣ አምላካችን እግዚአብሔር ግን፣ ከሰብአውያን ግምትና ተሞክሮ እጅግ የላቀ ነው፡፡ “የያህዌን ስም ከፍ ማድረግ” ማለት፣ እግዚአብሔርን በኑሮአችንና በአገልግሎታችን የበላይ ማድረግ ማለት እንጂ፣ አምላክን በተጸውዖ ስሙ መጥራት ማለት አይደለም፡፡
“በክርስቶስ ስም መጸለይ” ማለት በጸሎት ማጠናቀቂያ ላይ “በኢየሱስ ስም” ማለት ሳይሆን፣ እንደ ክርስቶስ ዐሳብና ፈቃድ ጸሎትን ማድረስ ማለት ነው፡፡ በክርስቶስ ስም መሰብሰብ፣ ለክርስቶስ ስም መስገድ ወዘተረፈ ማለት፣ በእርሱ ሥልጣን ሥር መዋቀር፣ በእርሱ ማዕከልነት መደራጀት፣ በእርሱ ጥላ ሥር መጠለል፣ በመጠጊያነቱ ውስጥ ማደር፣ ለእርሱ አምልኮተ ስግደት ማቅረብ፣ እንደ ቃሉ መኖር ወዘተ ማለት ነው፡፡ እንግዲያው የእግዚአብሔርን ስም የምንቀድሰው፣ ኑሮአችንንና ዐስተሳሰባችንን በእርሱ ዐሳብና ፈቃድ ውስጥ በመክተት እንጂ፣ በአንድ ክሥተት መጨረሻ ላይ የተጸውዖ ስሙን በመጥራት ወይም ባለመጥራት አይደለም፡፡ “ያህዌ” ወይም “ኢየሱስ” የሚለው ስም የአምላክ መጠሪያ እንጂ፣ አንዳችም ምትሐታዊ ቀመር የለበትም፡፡ አምላክን ትምክህት፣ ታላቅነቱን ተገን ማድረግ እንጂ፣ የተጸውዖ ስሙን ማወቅ ቊም ነገር የለውም፡፡
የጥምቀት ቀመር፣ “በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ነው ወይስ “በኢየሱስ ስም” የሚለው ጒዳይ የተጸውዖ ወይም የማዕረግ ስም ክርክር ከሆነ፣ መስመር ስተናል፡፡ ምትሐታዊ ቀመር አድርገነዋልና፡፡ በርግጥ በመጀመሪያው ክፍል ላይ በስፋት እንደ ቀረበው አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት ከሆኑ፣ በማቴዎስ 28÷19 መሠረት መጠመቃችን አግባብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የአብ ሥጋ ከሆነ ግን በኢየሱስ ስም መጠመቅም የለብንም፡፡ በሥጋ ስም የምንጠመቅበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ ሥጋ ለባሽን ክንዱ የሚያደርግ ርጒም ነውና (ኤርምያስ 17÷5)፡፡
[1] ስም በሚለው ጒዳይ ላይ በተወሰነ መጠንም ቢሆን በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ፣ ግልጽ የሆነ መረዳት ያለ አይመስልም፡፡ ይህ ዐባሪ ይህን የአመለካከት ስሕተት ያርማል ብለን እናስባለን፡፡
[2] እንግሊዝኛውም እንዲሁ ነው:— Proper Nouns, Common Nouns, Concrete Nouns, Abstract Nouns, Countable Nouns, Uncountable Nouns, Collective Nouns, Compound Nouns, Possessive Nouns, Gerunds (verbs ending in “ing” that acts as nouns).
[3] ብላታ መርስዔ ኀዘን፤ ገጽ 25፡፡
[4] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 26፡፡
[5] ተክለ ማርያም ገዛኸኝ፤ ዐዲስ ልደት፤ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል (ዐዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ) ገጽ 117፡፡
[6] መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ” (ማርቆስ 16÷17) የሚለውን ክፍል፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጋንንትን ያወጣሉ” ብለን ልናነበው አይገባም፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ የሆኑ ስሞችን ሁሉ እርሱን የሚመጥኑት ከሆነ፣ እነዚህን ስሞች ሁሉ በመጥራት አጋንንትን ብናወጣ ተሳስታችኋል ልንባል አንችልም፡፡
[7] ኤልሻዳይ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ወደ 48 ጊዜ ያህል የሚገኝ ሲሆን፣ ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጋሎት ላይ የዋለው በዘፍጥረት 17÷1 ላይ ነው፡፡ (እንዲሁም የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል:— ዘፍ. 35÷11፤ ዘፀ. 6÷2-3፤ ዘኈ. 24÷4:16)፡፡
[8] ያህዌ በሚለው የአምላክ ስም ላይ እንዲሁም ይህ ጽሑፍ በሚያነሣው ጭብጥ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ ተስፋዬ ሮበሌ፤ አርዮሳውያን፤ የይሖዋ ምስክሮች አስተምህሮ በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን፤ (ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበር፤ ሎጋንቪል፣ ጆርጂያ፤ 2016 ዓ.ም) ይመለከቷል፡፡
[9] ይህ ለዕብራይስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለአብዛኞቹ ጥንታውያን ቋንቋዎች እውነት የሆነ ክሥተት ይመስላል፡፡ ለምሳሌ:— የግእዝ ቋንቋ አናባቢ ሆህያት የተቀመሩለት ከጊዜ በኋላ እንደ ሆነ መረጃዎች ይጠቁሟሉ፡፡ ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል፣ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም በግእዝ ቋንቋ” በሚል ርእስ አዘጋጅተው ያሳተሙት መጽሐፍ ይህን ጒዳይ በተመለከተ እንዲህ ይላል፣ “በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ) ጊዜና ከአብርሃ ወአጽብሐ ዘመን ወዲህ ነው፣ እንጂ ከዚያ በፊት ፊደላቱ ቢኖሩም አናባቢ ምልክቶች ሳይኖሩአቸው የነበረው ግእዙ ፊደል ብቻ በመሆኑ ፊደሎቹ ስላስቸገሯቸው ለካዕብ፣ ለሣልስ፣ ለራብዕ፣ ለሐምስ፣ ለሳድስና ለሳብዕ የሚሆኑ የፊደላቱን ድምፆች የሚለዋወጡ አናባቢ ምልክቶችን ጨምረው እያንዳንዱ ፊደል ሰባት ዐይነቶች እንዲሆኑ አዘጋጅተው ለአጻጻፍና ለድምፅ አሰጣጥ እንዲመች አድርገውልናል” (ገጽ 5)፡፡
[10] “የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር” በመባል የሚታወቀው “የይሖዋ ምስክሮች” ድርጅት፣ ሰው ድነት የሚያገኘው ይህን የአምላክ ስም በመጥራት እንደ ሆነ እንዲሁም በምድር ላይ ይህን ስም ለፍጥረት ሁሉ በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው ይኸው ድርጅት እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ይህ የአምላክ ስም ትክክለኛ አነባበብ እንደማይታወቅ፣ አሁን ያሉት አማራጭ አነባበቦች (“ጆሆቫ” ወይም “ያህዌ” የሚሉት ስያሜዎች) ሰው ሠራሽ እንደ ሆኑ ገልጾአል፡፡ በዚህ ረገድ ድርጅቱ ዕያተመ ከሚያወጣቸው ጽሑፎች መኻል የሚከተሉትን ሁለት መጻሕፍት ይመለከቷል—Aid to Bible Understanding ገጽ 884-885፡፡ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር፤ ገጽ 195፡፡ ትክክለኛውን የአምላክ ስም ማወቅ ለድነት እጅግ ወሳኝ ጒዳይ ነው እንዲሁም የአምላክን ስም ለፍጥረት ሁሉ የምናሳውቅ ብቸኛ የምድር ወኪል ነን እየተባለ፣ በአንጻሩ ደግሞ የአምላክ ስም ትክክለኛ ንበት አይታወቅም ማለት ትልቅ ተቃርኖ ነው፡፡ እንግዲያው የድርጅቱ ተከታዮች ሊጠየቁ ከሚገባቸው ጥያቄዎች መኻል አንዱ፣ “እንዴት የማይታወቅ ስም ዕወቁ እንባላለን፤ እንዴትስ ሰው ሠራሽ የሆነ ስም ድነት ለማግኘታችን ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል?” የሚለው ነው፡፡
[11] በቴትራግራማቶን ላይ የቀረበው ትንታኔ በአብዛኛው የተወሰደው ጸሓፊው፣ አርዮሳውያን በሚል ርእስ ካዘጋጀው መጽሐፍ ነው፡፡
[12] “ዓ.ቅ.ክ” የሚለው ምኅጻረ ቃል፣ ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ወይም ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለት እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡
[13] የብሉይ ኪዳን 295 ክፍሎች በ352 ዐዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ ተጣቅሰው የሚገኙ ሲሆን፣ እንደዚህ ስሌት 4.4 ከመቶ የዐዲስ ኪዳን ምንባባት ብሉያት ናቸው ወይም 22.5 የዐዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ አንድ የብሉይ ኪዳን ምንባብ ይገኛል እንደማለት ነው፡፡ ለበለጠ መረጃ:— Roger Nicole, Revelation and the Bible, ed. Carl. F.H. Henry (Grand Rapids: Baker, 1958), ገጽ 137-151 ይመለከቷል፡፡
[14] “የይሖዋ ምስክሮች” 237 ጊዜ ያህዌ የሚለውን ስም በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የጨመሩ ቢሆንም፣ ለዚህ አድራጐታቸው ግን አንዳችም አጥጋቢ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም፡፡ እንዲያውም በዐዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ ይህን ቃል መጠቀማቸው ሰዎች፣ “ኢየሱስ አምላክ አይደለም” ወደሚለው አስተምህሮአቸው እንዲሳቡ አድርጓል፡፡
[15] በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ፣ “አላህ” የሚለውን የዐረብኛ የወል ስም፣ “እግዚአብሔር” በሚለው የዐማርኛ የወል ስም ተክተን እንጠቀም ወይስ አንጠቀም የሚል የሁለት ወገን ክርክር ቀርቦ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ በእኔ አተያይ ይህ ሙግት ሊፈታ የሚችለው፣ በዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ክርክሩ በቀረበበትም ወቅት የሰጠሁት አስተያየት ይህንኑ አካሄድ የተከተለ ነበር፡፡
[16] ይህ ክፍል በቀጥታ የተወሰደው ተስፋዬ ሮበሌ፤ አርዮሳውያን፤ የይሖዋ ምስክሮች አስተምህሮ በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን፤ ላይ ነው፡፡
[17] በሚከተለው ድረ ገጽ ላይ ይህን መረጃ የወሰድነው ወርኀ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ላይ ነው፡፡
www.garyhabermas.com/articles/The_Lost_Tomb_of_Jesus/losttombofjesus_response.htm

