በርግጥ ነገረ መለኮት አንገብጋቢ ነውን? 

ሀ. ትልም

የዚህ ምዕራፍ ቀዳማይ ዐላማ ሦስት ነው፡፡ ይኸውም:—

  • የምሥራቹን ወንጌል በማብሠር (ማለትም በወንጌል ሥርጭትና ደቀ መዛሙርት በማፍራት) ሂደት ውስጥ፣ የሥነ ጽሑፍ ሚናንን ትልቅነት በጒልኅ ማሳየት፣
  • በሥነ ጽሑፍ ረገድ በቤተ ክርስቲያን የሚታየውን  ክፍተት፣ ለማነጻጸሪያ ከተመረጠ ናሙና ጋር ማገናዘብ (ማነጻጸር) የክፍተቱን ጥልቀትና ስፋት በውል ማስተዋል፣ 
  • ለማገናዘቢያነት የተመረጠው ናሙና ጠንከራ ጐኖች ናቸው የሚባሉትን ተሞክሮዎችና አሠራሮች፣ ቤተ ክርስቲያን ልትጠቀምባቸው እንዴት እንደምትችል፣  ጠቋሚ ዐሳቦችን ፈንጠቅ ማድረግ ነው፡፡  

ለ. በርግጥ ነገረ መለኮት አንገብጋቢ ነውን?  

በክርስትና ሃይማኖት እና በመናፍቃን እንቅስቃሴ መኻል ያለውን ገደል የማሰው (ልዩነቱን ያበጀው)፣ ነገረ መለኮት (የክርስትና መሠረተ እምነት) ነው፡፡ ክርስትና አንዱን አስተምህሮ ያምናል፤ መናፍቃን ተቃራኒውን ትምህርት ይከተላሉ፡፡ ልዩነቱ፣ “ዐበይት” ተበለው በሚጠሩ አንጋፋ ትምህርቶች ላይ መሆኑ፣ ችግሩን ይበልጥ አግዝፎታል፡፡   

እውነተኛን መንፋሳዊነት፣ ሐሳዊ ከሆነው መናፍስታዊ አሠራር የሚለይልን ትምህርት ነው (2ጢሞ. 3÷16-17፤ ሮሜ 6÷17-18፤ 1ጢሞ. 1÷5:10፤ ቈላ. 2÷22-23፤ 1ዮሐ. 4÷13)፡፡እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁና ዐሳባችሁ ውደዱ” የሚለውን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው፣ ዐሳባችንን ለእውነት (ለትክክለኛው ትምህርት) ሌሎ በማሳደር ብቻ ነው (ማቴ. 22÷37፤ ሮሜ 12÷2)፡፡  

የአስተምህሮ ቀዳማይ ዐላማ፣ በአስተምህሮው ጥላ ውስጥ በመሰብሰብ አንድነትን መፍጠር ቢሆንም (1ቆሮ. 1÷10፤ ሮሜ 16÷17፤ 2ዮሐ. 9-11)፣ ዐበይት ትምህርቶች ሲማሱና ሲጣሱ ግን፣ መከፋፈልና መለያየት እውን ይሆናል፡፡ እውነት ነባራዊ ፋይዳ ስላላት፣ ሰዎች በአስተምህሮ ምክንያት መለያየታቸው፣ የነበረና የሚኖር ክሥተት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የተለያየ ዐስተሳሰብ እንዲሁም የተለያየ ምግባር አላቸውና፡፡ ይህ የማይካድ ሐቅ ቢሆንም፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እውነትን በመጫማት (የሙጥኝ በማለት) ሐሰትን ወግድ ማለት ይጠበቅባቸዋል (ኤፌ 4÷12-13)፡፡ በእውነት የምትጠቅመውን ያህል፣ እንዳትበረዝ እንዳትከለስ መጠበቅ፣ አፍቃሬ እውነት የሆኑ ሰዎች ሁሉ ኀላፊነት ነው፡፡

“ዐበይት ክርስቲያናዊ ትምህርት (ደርዛዌ ነገረ መለኮት) ዋነኛ ጒዳይ ለምን ሆነ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ እነዚህ ትምህርቶች የድነት ቅድመ ሁኔታ መሆናቸውን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በማያሻማ መንገድ መግለጹ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንንና ያንን እመን ማለታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይህንና ያንን የማታምን ከሆነ፣ ከዘላለም ሕይወት ትጐድላለህ፤ ዘላለማዊ አበሳ (ፍዳ) ያገኝሃል፤ የእውነት ሁሉ ባለቤት ከሆነው ከአምላክ ትለያለህ ወዘተ ይሉናል፡፡ ይህ ደግሞ፣ ዐበይት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች፣ የሰብአውያንን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ የሚለውን ቋሚ ንግግር የሚያጐላምስ ሐቅ ነው፡፡    

ቅዱሳት መጻሕፍት አንዳንድ ትምህርቶች ከሌሎች ትምህርቶች ይልቅ፣ ገቢራዊ ፋይዳቸው እንደሚበረታ ያስተምራሉ፡፡ ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባባትን ለአብነት ያህል እንመልከት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 23÷23 ላይ፣ ኢየሱስ ጸሓፍትንና ፈሪሳውያንን፣ ከዐበይት ትምህርቶች ይልቅ፣ በንዑሳን (በደቂቃን) ትምህርቶች ላይ ትኲረት በማድረጋቸው ነቅፎአቸዋል:—  

  • “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ ከአዝሙድና ከእንስላል፣ ከከሙንም ዐሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን፣ ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተው ወዮላችሁ፡፡ ሌላውን ሳትተዉ፣ ይህን ልታደረጉ ይገባችሁ ነበር”፡፡

ጸሓፍትና ፈሪሳውያን፣ ለዐሥራታቸው እጅግ ጠንቃቃ መሆናቸው፣ የሚበረታታ ሠናይ ግብር ነው፡፡ ይህ ጠንቃቃነት ግን፣ “በሕግ ባለው ዋና ነገር” ላይ ይበልጥ ሊገንን (ሊደምቅ) ሲገባው፣ ጭራሹኑ ተግባራዊ ያለመሆኑ፣ ክርስቶስ እንዲነቅፈው ምክንያት ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው ክፍሉ፣ “ሌላን ሳትተዉ፣ ይህን ልታደረጉ ይገባችሁ ነበር” የሚለው፡፡

በሮሜ 14÷1-10 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ሥርዐተ አምልኮ ሊካሄድበት የሚገባው ቀን የትኛው ነው?”፣ በሚለው ጒዳይ ላይ የተወዛገቡ ሰዎችን እንዲሁም፣ “ሥጋ ወይስ አትክልት ብቻ እንመገብ?” በሚለው ነጥብ የተለያዩትን ሰዎች የዳኘው፣ አንዱን አመለካከት በመደገፍ፣ ሌላውን አቋም በመንቀፍ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ይህ ጒዳይ የልዩነት ምክንያት መሆን በጭራሽ አይገባውም በማለት እንጂ፡፡           

  • “በእምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው፣ አከራካሪ በሆኑ ጒዳዮች ላይ በአቋሙ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት፡፡ የአንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ያልጠነከረው ሌላው ሰው ግን፣ አትክልት ብቻ ይበላል፡፡ ማንኛውንም የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላውም፣ የሚበላውን አይኰንን፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና፡፡ ሌላውን በሚያገለግል ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው፤ ጌታ ሊያቆመው ስለሚችልም ይቆማል”፡፡
  • “አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ፣ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኲል እንደ ሆኑ ያስባል፡፡ እያንደንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን፡፡ አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና፡፡ የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ እግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል፡፡ ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና፡፡   ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፡፡ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን”፡፡

ይህ ምንባብ፣ ክርስቲያኖች ወንድማማች እንዲሆኑ እንዲሁም አንዱን ሰው ሕያው፣ ሌላውን ሰው ደግሞ ሙታን የሚያደርገው፣ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንደ ሆነ ይገልጻል፡፡ ይህ ዐበይት አስተምህሮ ነው፡፡ የቀንና የምግብ ጒዳይ ግን ኢምንት (ንዑስ) በመሆኑ፣ ክርስቲያኖች  ገቢራዊ ፋይዳቸው ደቃቅ በሆኑ ትምህርቶች፣ ወንድማማችነታቸው ሊበረዝና ሊከልስ አይገባም:—

  • “ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቷል፤ በሕይወትም ተነሥቷል፡፡ ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ?”  

ሀ. ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ትምህርቶች 

ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ፣ “እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደ ሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና”  (ዮሐ. 8÷24) ብሏል፡፡ ይህ ማለት፣ “ኢየሱስ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ፣ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችንን ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ክርስትና፣ “ክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ነው” ሲል፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ደግሞ፣ “ኢየሱስ የአምላክ የመጀመሪያ ፍጡር ነው፤ ሊቀ መልአክ ሚካኤል ነው” ይላሉ[1]፡፡ እንግዲያው ኢየሱስ ማን ነው ብለን እንመን? ይህ ተቃራኒ ዐዋጅ ስለሆነ፣ አንዱ ከሌላው ጋር ሊታረቅ በጭራሽ አይችልም፡፡ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” በመባል የሚታወቀው የሃይማኖት ድርጅት ሲሻው፣ “ኢየሰሱስ አብ ነው” ሲል ሲሻው ደግሞ፣ “ኢየሱስ፣ አብ የተጠቀለለበት (የተሸፈነበት) ሥጋ ነው” ይላል[2]፡፡ ቋሚ የሆነው ክርስትና ትምህርት ደግሞ፣ ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ስለሆነ፣ “አብ የተጠቀለለበት ሥጋ ነው” የሚለው ትምህርት፣ በትልቅ አጽንዖት ኑፋቄ ይላል፡፡ ከዚህ የምንማረው ቊም ነገር፣ በነባሩ የክርስትና ትምህርትና በመናቃን መካከል ያለው ልዩነት፣ የሰዎችን ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ትምህርቶች ላይ ያለ፣ የአስተምህሮ ልዩነት መሆኑን ነው፡፡ በትምህርቶቹ መኻል ያለው ልዩነት የቅራኔ ልዩነት በመሆኑ፣ ሊታረቁ (ሊስማሙ) በጭራሽ አይችሉም፡፡ አንዱ ትክክል ከሆነ፣ ሌላው ስሕተት መሆኑ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥነ አመክንዮ ተቃራኒ ዐዋጆች፣ በአንድ ጊዜና በተመሳሳይ ትርጒማቸው፣ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ በጭራሽ አይችሉም ይላልና፡፡

ክርስቲያኖች፣ “ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው፣ በሞተበት ቊሳዊ አካል ነው” ስንል፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ደግሞ፣ “የክርስቶስ ቊሳዊ አካል ከሞቱ በኋላ፣ ወደ ጋዝነት ተቀይሯል” ወይም፣ “ለአምላክ ፍቅር መታሰቢያነት አምላክ ራሱ በሆነ ስፍራ ደብቆት” ይሆናል ይሉናል፡፡ ይህ እርስ በርስ (አንዱ ከሌላው ጋር) የሚጻረር ትምህርት ነው፡፡ በሥነ አመክንዮ ሁለቱ ዐዋጆች ትክክል ላይሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ከሁለቱ አንዱ ዐዋጅ ፍጽም ስሕተት መሆኑ የግድ ነው፡፡ ሁለት ተቃራኒ ዐዋጆች ትክክል የሚሆኑበት አንዳችም ምክንዮአዊ ሕግ የለም፡፡  

ቅዱሳት መጻሕፍት በማያሻማ መንገድ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ በአካለ ሥጋ ከሙታን መነሣቱን፤ እንዲሁም ይህን ሐቅ ማመንም ሆነ ያለማመን፣ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችንን እንደሚወስነው ያስተምራሉ:—

  • “እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን ዐዲስ ልደት፣ እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን”፡፡
  • “ኢየሱስ ጌታ ነው ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ”፡፡
  • “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው፡፡ እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው”፡፡

 (1ጴጥ. 1÷3-4፤ሮሜ 10÷9፤ 1ቆሮ. 15÷17-18)

ክርስቲያኖች እነዚህንና እነዚህን መሰል ምንባባት መሠረት አድርገን ዘላለማዊ ድነት፣ “በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዞታዊ ሥራ በማመን የሚገኝ ነው” ስንል፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ደግሞ፣ “ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር ጋር መተባበር” እንዲሁም፣ “ከድርጅቱ ጋር ጠንክሮ በመሥራት፣ ከአርማጌዶን ጦርነት መትረፍ ይቻላል” ይላሉ፡፡ በአንጻሩ፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” የሚባለው ሃይማኖታዊ ድርጅት፣ “ድነት፣ የኢየሱስ ሥጋ ከሰማይ እንደ መጣ በማመን፣ በመጠመቅና ልሳን በመናገር እንደሚገኝ” ይገልጻል፡፡ ከእነዚህ ዐዋጆች መኻል አንዱ ትክክል ከሆነ፣ ሌሎቹ በጭራሽ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እርስ በርስ የሚቃራን ዐዋጅ ትክክል ሊሆን በጭራሽ አይችልምና፡፡

ከዚህ የምንማረው ሐቅ፣ በክርስትናና በመናፍቃዊ ድርጅቶች መኻል ያለው ልዩነት፣ በጭራሽ እርስ በርስ ሊታረቅ የማይችል ከሆኑ ባሻገር፣ ልዩነቶቹ የሰዎችን ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ትምህርቶች ላይ መሆኑ፣ እነዚህ ሃይማኖቶች እጅግ ተጻራሪ ሃይማኖት እንዲሆኑ አድርጓል፡፡  

አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ “የእኛ ቤተ ክርስቲያን ዶክትሪን የላትም” ወይም “ዶክትሪን ሊለያየን አይገባም” ሲሉ ይደመጣል፡፡ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ የችግሩ ምክንያት፣ “ዶክትሪን” የሚለውን ቃል በትክክል ካለማወቅ ወይም፣ “ዶክትሪን” የሚያመጣውን ትልቅ ልዩነት በትክክል ካለመገንዘብ የሚመጣ ስሕተት ነው፡፡ “ዶክትሪን” የሚለው ቃል ከላቲን የተገኘ ቃል ሲሆን፣ መሠረታዊ የሆነ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍና ወዘተ ትምህርት ለማመልከት ግልጋሎት ላይ ይውላል፡፡ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ “ዶትሪን” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ፣ “ዶግማ” የሚለውን የግሪክ ቃል ለተመሳሳይ ዐላማ ትጠቀማለች[3]፡፡

ያም ሆነ ይህ፣ “ዶክትሪን” መሠረተ እምነትን አመልካች እስከ ሆነ ድረስ፣ “ዶክትሪን የለኝም” የምትል ቤተ ክርስቲያን ልትኖር አትችልም፡፡ አለች እንኳ ቢባል፣ “የእኛ ቤተ ክርስቲያን ዶክትሪን የላትም” የሚለው አነጋገር ራሱ ዶክትሪን ነው፡፡ ዶክትሪን የሌላት ቤተ ክርስቲያን፣ ዐበይትም ሆነ ደቂቅ የሚባል ትምህርት የሌላት፣ ልቅ የሆነች፣ እርስ በርስ የተምታታ አቋምና ትምህርት  የሚንጸባረቅባት፣ ቅይጥ ትምህርት የምታስተናግድ፣ ቀውጢ ስብስብ ነች ማለት ነው፡፡ ጥሩ ዶክትሪን ባይሆንም እንኳ፣ “ተቃራኒ ዐስተሳሰብ መያዝ ትክክል ነው” ማለትም ዶክትሪ ነው፡፡ በዐጭሩ የትኛውም ሃይማኖት ወይም ርእዮተ ዓለም፣ ያለ ዶክትሪን ጸንቶ ሊቆም አይችልም፡፡    

ጽንፈኛው እስላማዊ ድርጅት[4]፣ እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን ቀመር፣ ወርኀ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም፣ “የመስቀሉ ተከታዮች” እንዲሁም “ክርስትናን አንክድም ብለዋል” በሚል፣ ሠላሳ ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራውያንን ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ፣ በአደባባይ እንደ እንስሳ ዐርዷቸዋል[5]፡፡ እነዚህ ሰዎች መሞትን የመረጡት፣ ክርስትናን አንክድም፤ የእስልምናን መሠረተ እምነትም አንቀበልም በማለታቸው ነው፡፡ መሠረተ እምነት (ዶክትሪን) የልዩነት ምክንያት ካልሆነ፣ እነዚህ ሰዎች መሞት አልነበረባቸውም፡፡ ክቡር የሆነውን የሕይወት ዋጋ ያስከፈለው ዶክትሪን ነው፡፡ “ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ” የሚለው አባባል[6] ትልቅ ትርጒም ይዞ የሚመጣው፣ “እውነት ነባራዊ ነች” የሚል ዶክትሪን፣ ሲኖር ብቻ ነው፡፡  

“ወንጌል የድነት መሠረት ነው” ስንል፣ ድነት የሚገኝበት ትክክለኛ የሆነው ስብከተ ወንጌል ምን እንደ ሆነና፣ እንዴት ሰዎች ሊቀበሉት እንደሚችሉ በወል የማናውቅ ከሆነ፣ ከድነት ጋር ልንገናኝ አንችልም (ገላ. 1÷6-9፤ 1ጢሞ. 4÷16)፡፡ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችን የሚወሰነው፣ ትክክለኛውን ትምህርት ገንዘብ በማድረጋችን ወይም ባለማድረጋችን ነውና፡፡  

ለ. ዐበይት፣ መኻል ሰፋሪና ደቂቃን ትምህርቶች

ከእነዚህ ምንባባት በግልጽ የምንማረው ሐቅ፣ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ፋይዳቸው፣ ተዋረዳዊ በሆነ መንገድ መደራጀቱን ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ ሁሉም ክርስቲያናዊ ትምህርቶች፣ እኲል ፋይዳ አላቸው፣ በእኲል ደረጃ አንገብጋቢ (ዐበይት) ናቸው ማለት   አይቻልም፡፡ አንዳንድ ትምህርቶች፣ ለድነታችን እጅግ ወሳኝ ጒዳይ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ለክርስቲያናዊ ሕይወት (ኑሮ) ጠቃሚ ቢሆኑም፣ የድነት ቅድመ ሁኔታ ባለመሆናቸው፣ ዐበይት በሚለው መስፈርት ሥር ልናስቀምጣቸው አንችልም፡፡

እኔ፣ “ዐበይት” የሚለውን ጒዳይ የተመለከትሁት ከድነት አንጻር ብቻ (ከድነት ጋር በቀጥታ የሚገናኙ አስተምህሮዎች) ነው[7]፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ፣ ይህን የማታምኑ ከሆነ፣ ድነት አታገኙም (ከዘላለም ሕይወት ትጐድላላችሁ) የሚላቸውን ትምህርቶች፣ “ዐበይት” በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቻቸዋለሁ[8]፡፡

አንዳንድ ትምህርቶች ደግሞ፣ ለድነት አንገብጋቢ ጒዳይ ባይሆኑም እንኳ፣ ለኑፋቄ የሚዳርጉ፣ ክርስትና ለድነት ተስፋ የሰጣቸውን ትምህርቶች እንድንቃረን ወይም እንድንክድ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ፣ እጅግ ትልቅ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ትምህርቶች  ናቸው፡፡ እኔ እነዚህን ትምህርቶች፣ “መኻል ሰፋሪ ትምህርቶች” በሚል ማዕቀፍ ውስጥ አካትቼአቸዋለሁ፡፡  

“መኻል ሰፋሪ”[9] የሚለው ማዕቀፍ ባሕርዩ ምን እንደ ሆነ የተወሰነ ገለጻ ማኖር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ:— አንድ ሰው ድነት ለማግኘት፣ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሕጸጽ አልባ የሆኑ፣ የአምላክ አፊዎተ ቃል ናቸው” የሚለውን ማመን ላይገደድ ይችላል፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች እኛ ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተሟላ መልኲ በእጃቸው አለመኖሩን ልብ ይሏል፡፡ ምናልባት አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች፣ ይህን ያህል ቊጥር ያላቸው የዐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት መኖራቸውን ላያውቁ ይችላሉ፡፡   

አማኒው ማኅበረሰብ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃልነቱን እንደሚቀበል ታሳቢ ቢደረግም፣ “የዐዲስና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ካላመናችሁ፣ ድነት አታገኙም” የሚል ዐሳብ የያዘ ወይም ይህን ዐሳብ ታሳቢ ያደረገ (ይህ ዐይነት አንድምታ ያለው) ምንባብ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም[10]፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ሰው፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ሕጸጽ አልባ የሆኑ፣ የአምላክ አፊዎተ ቃል ናቸው ብሎ የማያምን ከሆነ፣ እምነቱን በምን ላይ ሊመሠርት (የእምነቱ መልኅቅ ምን ሊሆን) ይችላል? በምን ሊመራ፣ በምን ሊተዳደር ይችላል? ለድነት ወሳኝ ናቸው ያልናቸውን ዐበይት አስተምህሮዎች፣ ለድነት ወሳኝ (ዐበይት) ናቸው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል ምን መሠረት ያገኛል?  ምክንያቱም እነዚህን ትምህርቶች ወሳኝ (ዐበይት) ያላቸው፣ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነውና[11]፡፡  

ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚስማሙባቸውን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች[12]  ያወጧቸው የሃይማኖት መግለጫዎችን ተከትልን ከሄድን[13]፣ ዝርዝሩ እኔ ካቀረብሁትም ይልቅ ሰፊ ይሆናል[14]፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ዐበይት የሚሏቸውን ትምህርቶች የዘረዘሩት፣ የቀደምት ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መግለጫዎች ተከትለው ነው፡፡

አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ፣ የሃይማኖት መግለጫዎቹ ታሳቢ ያደረጓቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባባት በመጥቀስ፣ ከጉባኤዎቹ ጋር ተመሳሳይ ዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ለዚህ አብነት ሆነው ሊቀርቡ ከሚችሉ ምሁራን መኻል፣ ዐቃቤ እምነቱ ኖርመን ጋይዝለር (Norman L. Geisler) አንዱ ናቸው[15]፡፡ ፕሮፌሰር ጋይዝለር በዚህ አንጻር ዐበይት ያሏቸው ትምህርቶች ዐሥራ አራት ሲሆኑ፣ ወደዚህ ድምዳሜ እንዴት እንደ ደረሱ የገለጹት፣ በዚህ መልክ ነው[16]፡፡

ወንጌል፣ “ድነት ለማግኘት የእግዚአብሔር ኀይል” እንደ ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምራሉ (1ቆሮ. 15÷1-8፤ ሮሜ 1÷16)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 3ሀ[17] ባለው ክፍል፣ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከገለጸ በኋላ፣ የድነት ወንጌል የሚለውን የዘረዘረው በሦስት ደርዝ አደራጅቶ ነው (ሮሜ 1÷17)፡፡ ይኸውም:— መጽደቅ (ከምዕራፍ 3ለ[18] እስከ ምዕራፍ 5)፣ መቀደስ (ምዕራፍ 6 እስከ 7) እና ዘላለማዊ ክብር (ምዕራፍ 8)[19]፡፡  

ፕሮፌሰር ጋይዝለር መጽደቅ፣ መቀደስና መክበር[20] የሚሉትን ቊልፍ ነጥቦች የሚያብራሩት በሚከተለው መልክ ነው፡፡ “መጽደቅ ቀድሞ ከተሠራ ኀጢአት ነጻ መሆንን ይጠቅሳል፡፡ መቀደስ ኀጢአት ዛሬ በእኛ ላይ ካለው ኀይል ነጻ መሆናችንን ይጠቁማል፡፡ መክበር ደግሞ፣ ኀጢአት በመጻኢው ጊዜ ከሚኖረው ኀይል ዐርነት መውጣትን አመልከች ነው ይላሉ”[21]፡፡ ስለዚህ በሦስት አጽቅ (ደርዝ) ያቀረቧቸው ጊዜን ማዕከል ያደረጉ የድነት አንጓዎች፣ በሚከተሉት ዐሥራ አራት ትምህርቶች ተደላድለዋል፡፡ ስለዚህ እንደ ፕሮፌሰር ጋይዝለር አመለካከት፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ዐሥራ አራት ትምህርቶች፣ ከድነታችን ጋር የተሰናሰሉ (የተቈራኙ) ዐበይት ትምህርቶች ናቸው:—

ዐሥራ አንድ ትምህርቶች የተዘረዘሩት፣ “ጽደቅ” በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ እነርሱም:— (1) የሰው ልጆች ሁሉ ኀጢአተኛ መሆናቸው፣ (2) ክርስቶስ ኢየሱስ ከድንግል መወለዱ፣ (3) ክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአት ነጻ መሆኑ፣ (4) ክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆኑ፣ (5) ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑ፣ (6) እግዚአብሔር አንድ መሆኑ፣ (7) አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት መሆናቸው፣ (8) የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ጸጋ የሚያስፈልገው ፍጡር መሆኑ፣ (9) ዘላለማዊ ድነት ለማግኘት፣ እምነት አስፈላጊ ጒዳይ መሆኑ፣ (10) የክርስቶስ ሞት ቤዞታዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ፣ (11) የክርስቶስ ኢየሱስ በሞተበት ቊሳዊ አካል ከሙታን መነሣቱ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ጋይዝለር፣ “መቀደስ”[22] በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ ሁለት ዐበይት ትምህርቶችን አካተዋል፡፡ እነርሱም:— (12) የክርስቶስ አካላዊ ዕርገት[23] እንዲሁም (13) ክርስቶስ እስከ አሁን ድረስ ክህነታዊ ምልጃ ያካሂዳል የሚሉት ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ጋይዝለር፣ “መክበር” በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ አንድ ትምህርት ብቻ አስቀምጠዋል፡፡ ይኸውም:— (14) የክርስቶስ ዳግም ምጽአት[24]፡፡ በአጠቃላይ ፕሮፌሰር ጋይዝለር ዐበይት የሚሏቸው እነዚህን ዐሥራ አራት ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ነው፡፡

ሐ. ዐበይት ትምህርቶች

በዚህ ረገድ ክርስቲያኖችን ሁሉ የሚያስማማ ማዕቀፍ በማበጀት፣ ዐበይት የሆኑትን ዐበይት ካልሆኑት ትምህርቶች መለየት አዳጋች ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጋይዝለር እጅግ ስመ ጥር ሊቅ ቢሆኑም፣ እኔ ተማሪያቸው[25] እንኳ፣ በዝርዝራቸው መስማማት አልተቻለኝም፡፡ እኔ የማቀርበውንም አማራጭ አካሄድ፣ ሁሉ ሰው ይቀበለዋል የሚል ዐሳብ የለኝም፡፡

ሁሉንም ነገረ መለኮት ምሁራን የሚያስማማው ነጥብ ግን፣ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ሁሉ እኲል ገቢራዊ ፋይዳ እንደሌላቸው፣ አንዳንዱ ትምህርት ዘላለማዊ ድነታችንን የሚጐዳ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ግን ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችንን የማይጐዱ መሆናቸው ሁሉንም ያግባባል፡፡

ለድነት ወሳኝ ናቸው ከምላቸው ትምህርቶች መኻል፣ የሚከተሉት ይገኙበታል:

  1. እግዚአብሔር አንድ መሆኑ (ዘዳ. 4÷35:39፤ 32÷39፤ 2ሳሙ.  22÷32፤ 2ነገ. 5÷15፤ ኢሳ. 37÷20፤ 43÷10፤ 44÷6-8፤ 45÷5:14: 21-22፤ 46÷9፤ ዮሐ. 5÷44፤ ሮሜ 3÷30፤ 16÷27፤ 1ቆሮ. 8÷4-6፤ ገላ. 3÷20፤ ኤፌ. 4÷6፤ 1ጢሞ. 1÷17፤ 2÷5፤ ያዕ. 2÷19፤ ይሁ.  25)፡፡  
  2. ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር እኲል ሪና ያለው፣ ዘላለማዊ  አምላክ መሆኑ[26] (ዮሐ. 1÷1-3:18፤ ሉቃ. 22÷70፤ ማር. 3÷11፤ ፊልጵ. 2÷5-11፤ 1ዮሐ. 4÷2-3፤ 10÷9፤ ዮሐ. 1÷14፤ 4÷6፤ 19÷28-30፤ ዕብ. 2÷17-18፤ 1÷6፤ ዮሐ. 11÷33-36፤ ማቴ. 4÷1-11፤ ፊልጵ. 2÷5-11፤ 2ቆሮ. 5÷21፤ 20÷28፤ ሮሜ 10÷9፤ 9÷5፤ ሐሥ. 20÷28፤ 1ዮሐ. 5÷20፤ ራእ. 5)፡፡
  3. አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት መሆናቸው (ማቴ. 28÷19፤ ሮሜ 1÷7፤ 1ቆሮ. 1÷3፤ ዮሐ. 5÷31-32፤ 8÷16-18፤ 3÷16-17፤ ገላ. 4÷4፤ ዮሐ. 3÷35፤ 5÷20፤ 14÷31፤   11÷41-42፤ 12÷28፤ 17÷1-26፤ ማቴ. 11÷27፤ ሉቃ.  10÷22፤ 1ዮሐ. 2÷1)፡፡
  4. ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአት የሌለበት ሰው መሆኑ (1ጴጥ 2÷22፤ 1÷19፤ 1ዮሐ. 3÷5፤ 1÷5፤ 2ቆሮ. 5÷21፤ ዕብ. 4÷15፤ 9÷22፤ 13÷5-6፤ ኤፌ. 5÷1-2)፡፡       
  5. የሰው ልጆች ሁሉ፣ ኀጢአተኞች መሆናቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ ድነት የሚያስፈልጋቸው መሆኑ (ሮሜ 11÷33-36፤ ገላ. 5÷19-20፤ ያዕ. 1÷14-15፤ ዘፍ. 3÷6፤ ሮሜ. 6÷12-14፤ 5÷12-15፤ ቈላ. 3÷5-6፤ ሮሜ 3÷9-12፤ 1ዮሐ. 3÷4-6፤ 2ቆሮ. 5÷21፤ 1ዮሐ.1÷7-9)፡፡
  6. ክርስቶስ ኢየሱስ ለሰብአውየን ኀጢአት የትኪ ሞት በመሞት፣ አማኒያኑን ከሞት ባርነት ዐርነት ማውጣቱ (ዮሐ. 12÷23-26፤ ሮሜ 6÷8-11፤ ማቴ. 28÷2-7፤ ማር. 15÷46-47)፡፡
  7. ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ፣ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ (ዮሐ. 11÷25-26፤ ሮሜ 10÷9፤ ማር. 16÷5-7፤ ማቴ. 28÷6፤ ሉቃ. 24÷38-40፤ 1ጴጥ. 1÷3፤ ፊልጵ. 2÷8-11፤ 1ቆሮ. 15)፡፡
  8. ዘላለማዊ ድነትን ለማግኘት፣ የሰው ልጆች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዞታዊ ሥራ ማመን እንደሚጠበቅባቸው (ኤፌ. 2÷8-9፤ 2÷4-5፤ 1÷4-6፤ ሮሜ 5÷12፤ 3÷20:24፤ ዕብ. 12÷2፤ 2ጴጥ. 1÷3-4፤ ዮሐ. 1÷12፤ 3÷16)፡፡ 

መ. መኻል ሰፋሪ ትምህርቶች

ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርሁት፣ “መኻል ሰፋሪ” ያልኋቸው፣  ከድነት ጋር በቀጥታ ያልተያያዙ፣ ነገር ግን ዐበይት የሚባሉት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ጸንተው እንዲቆሙ፣ ምክንያት የሚሆኑትን ትምህርቶች ነው፡፡ አንድ ሰው እነዚህን መኻል ሰፋሪ ትምህርቶች አልቀበልም ካለ፣ ዐበይት የሚባሉትንም ለመቀበሉ ወይም በቀጣይነት ዐበይት ትምህርቶችን ላለመካዱ፣ አንዳችም ዋስትና የለም[27]፡፡  

  1. የብሉይና የዐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የአምላክ አፊዎተ ቃል መሆናቸው (2ጢሞ. 3÷16-17፤ 2ጴጥ. 1÷20-21፤ መዝ 12÷6፤ 1ተሰ. 2÷13፤ 1ጴጥ. 2÷9፤ ኤፌ. 2÷10፤ ዕብ. 4÷12፤ ዮሐ. 15÷3፤ 17÷17፤ ኤፌ 5÷26፤ ኢያ. 1÷8፤ ያዕ. 1÷25፤ መዝ. 119÷105:160)፡፡  
  2. ለክርስቲያናዊ ሕይወት ጅማሮ የውሃ ጥምቀት አስፈላጊነት (ማቴ. 28÷18-20፤ ማቴ. 3÷11-17፤ ሐሥ. 2÷38-41፤ ሮሜ 6÷4፤ ሉቃ. 3÷21-22፤ ሐሥ. 22÷16፤ 19÷46)፡፡
  3. የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል የመሆን አስፈላጊነት (ዕብ. 13÷17፤ 1ቆሮ. 5÷12-13፤ ኤፌ. 4÷16፤ ገላ. 6÷10፤ 1ቆሮ. 12÷21፤ 1ተሰ. 5÷12፤ 1ጢሞ. 5÷17፤ ማቴ. 18÷15-20፤ 1ቆሮ. 12÷12-24)፡፡
  4. ለቅዱሳን መታነጽና ለወንጌል ሥርጭት፣ የጸጋ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖራቸው (1ቆሮ. 12÷4-6:8-11:26-31፤ 14÷1-5፤ 1÷4-8፤ ኤፌ. 4÷7-16፤ ሮሜ. 12÷3-8፤ 1ጴጥ. 4÷10-11፤ 2ጢሞ. 1÷6-7)፡፡
  5. ክርስቶስ በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚሠራ (ኤፌ. 3÷20-21፤ 2÷21-22፤ 2ጴጥ. 1÷3፤ ቈላ. 1÷10-12፤ 1ጴጥ. 2÷9፤ ማቴ. 16÷18፤ ሐሥ. 19÷46)፡፡
  6. ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ መስበክ እንደሚገባ (ማቴ. 28÷18-20፤ ማር. 16÷15፤ ሉቃ. 24÷46-47፤ ማቴ. 9÷37-38፤ ዮሐ. 20÷21፤ ኢሳ. 1÷8፤ ሐሥ. 1÷7-8፤ ሮሜ 10÷15፤ ሐሥ. 28÷28፤ ሐሥ. 2÷1-47፤ ዮሐ. 4÷35-38፤ ዮሐ. 3÷16፤ ሉቃ. 1÷1-26፤ 2ጢሞ 2÷15)፡፡

ሠ. ንዑሳን ትምህርቶች

ታናናሽ (ደቂቃን ወይም ንዑሳን) ከምንላቸው ትምህርቶች መኻል (ወይም ዐበይት አይደሉም ከሚባሉ ትምህርቶች መኻል) ጥቂቶቹን እነሆ:—

  1. አምላክ ድነት የሚያገኙ ሰዎችን በቅድሚያ መርጧል ወይስ አልመረጠም?
  2. ሰዎች ነጻ ፈቃድ አላቸው ወይስ የላቸውም?
  3. ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው ወይስ የለባቸውም?
  4. ተጠማቂውን በጥልቅ ውሃ ውስጥ እናጥምቅ ወይስ ውሃውን በተወሰነ የሰውነት ክፍል ላይ በማፍሰስ ወይም ደግሞ  በመርጨት?
  5. በዛሬ ጊዜ የተኣምራት ስጦታዎች (ፈውስና ልሳን) አሉ ወይስ የሉም?
  6. ትንቢተ ዮናስ፣ መጽሐፈ ኢዮብ፣ ሁለተኛ ጴጥሮስ መጻሕፍት በቀኖና ውስጥ መካተተ አለባቸው ወይስ የለባቸውም?
  7. ቤተ ክርስቲያናችን መጠቀም ያለብን ወይም ክርስቲያኖች ሊያነቡት የሚገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም የቱ ነው?  
  8. ከወንጌላት መኻል በመጀመሪያ የተጻፈው የትኛው ወንጌል ነው?
  9. የጌታ ራት መሰጠት ያለበት፣ በምን ያህል ጊዜ ውሰጥ ነው?
  10. ኢየሱስ ያስተማረው በአረማስጥ ነው ወይስ በግሪክ?
  11. የጌታ ትክክለኛው የልደት ቀን መቼ ነው?
  12. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠቀም ያለብን የሙዚቃ መሣሪያ የቱ ነው?
  13. ማኅሌተ እግዚአብሔር ሲቀርብ (መዝሙር ሲዘመር) ውዝዋዜ ማድረግ ክልክል ነው ወይስ፣ የሽብሸባና የወረብ ዐይነት ውዝዋዜ ብቻ መሆን አለበት?
  14. ለጌታ ራት መቅረብ ያለበት የወይን ጭማቂ ነው ወይስ የወይን ጠጅ?
  15. ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው መቀበል የማይችሉ የአእምሮ ሕሙማን፣ ዕጣ ፈንታችው ምንድን ነው?
  16. መጥምቁ ዮሐንስ አሴናዊ (Essence) ነበር ወይስ አልነበረም?
  17. የቤት ወይም የዱር እንስሳት ዘላለማዊ ድነት አላቸው ወይስ የለባቸውም?
  18. ፍጥረትን ከመፍጠሩ በፊት እግዚአብሔር ምን ያደርግ ነበር?

ረ. ዕቅበተ እምነት ዐበይት ትምህርቶች ላይ ትኲረት ያደርጋል

የዕቅበተ እምነት ቀዳማይ ዐላማ፣ መሠረታውያኑን የክርስትና ትምህርቶች ከመናፍቃን መጠበቅ ነው፡፡ ሲ. ኤስ. ልዊስ (C. S. Lewis) የተባለው ዕውቅ ዐቃቤ እምነት፣ እነዚህን መሠረታውያን ትምህርቶች “Mere Christianity” ይላቸዋል[28]፡፡ አልቪን ፕላንቲንጋ የተባለው ዕውቅ የፍልስፍናና ዐቃቤ እምነት ሊቅ፣ ዐቃብያነ እምነቶች ሊጠብቁት የሚገባቸው ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን የገለጸው በሚከተለው መንገድ ነው:— ካቶሊኮችን፣ ኦርቶዶክሶችንና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን እንድ የሚያደርጉ፣ በኒቂያ፣ በቈስጥንጥንያ፣ በኬልቄዶንና በኤፌሶን ይፋ የተደረጉትን አንቀጸ ሃይማኖቶች የሚመለከት ነው፡፡ “ጆን ካልቪንን ከአኳይናስ፣ ማርቲን ሉተርን ከአውጉስጢኖስ፣ ሜኖ ሳይመንን ከካርል ባርት፣ እማሆይ ትሬሳን  ከማክሲመስ ዘኮንፌሰር፣ ቢሊ ግርሃምን ከቅዱስ ጐርጐርዮስ ባላማስ ጋር እንድ የሚያደርጓቸውን (የሚስማሙባቸውን) መሠረታውያን እምነቶች ነው”[29]፡፡ የዕቅበተ እምነት ተልእኮ እነዚህን መሠረታውያን ትምህርቶች ከአደጋ መጠበቅና ይህን መሠረተ እምነት ማወጅ እንጂ፣ በደቃቅ ትምህቶች ላይ ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር መወዛገብ፣ የዕቅበተ እምነት ተልእኮና ግብ አይደለም፡፡

ይህ ሲባል በደቃቅ ትምህርቶች ላይ አንወያይ (አንነጋገር) ማለት በጭራሽ አይደለም፡፡ ጊዜና ዕውቀቱ በፈቀደ መጠን በደቃቅ ትምህርቶችም ላይ ዐውደ ጥናት ልናካሂድ፣ የመድረክ ውይይቶችንና ሙግቶችን ልናደርግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ እንደ ዕቅበተ እምነት ክርክር፣ አንዱ ርቱዕ ሌላው መናፍቅ ነው በሚል መንፈስ  መካሄድ የለበትም፡፡ ብዙውን ጊዜ በደቃቅ ትምህርቶች ላይ የምናካሂደው ውይይት፣ ዐዳዲስ ክርስቲያኖችን በብዙ የሚያውካቸው ስለሆነ፣ እንዲያ እንዳይሆን ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ሰ. ርቱዕ እምነት ወይስ ርቱዕ ምግባር      

አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ርቱዕ ምግባር ላይ እንጂ፣ ርቱዕ ትምህርት[30] (ዶክትሪን) ላይ ትኲረት ማድረግ ተገቢም አስፈላጊም አይደለም ይላሉ፡፡ ይህ ዐስተሳሰብ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛ፤ ይህን ዐስተሳሰብ በሌላ መንገድ እንግለጸው ካልን፣ “ትምህርት ላይ ትኲረት አታድርጉ የሚል ትምህርት (ዶክትሪን)” ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከትምህርት በፊት ምግባር ይቅደም የሚል ዶክትሪን ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ጥሩ ዶክትሪን ግን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከጥሩ ምግባር በፊት ምግባሩ የሚመራበት ጥሩ ዶክትሪን ይፈልጋልና፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ተግባራዊ የሚያደርጉት፣ ትክክል ነው ብለው የሚያስቡትን ትምህርት ስለሆነ፡፡ ይህ ደግሞ ከጥሩ ምግባር በፊት፣ ጥሩ ዐስተሳሰብ እንደሚቀድም ጠቋሚ ነው፡፡ “ቀና ዐስተሳሰብ የቀና ድርጊት መሠረት (ዋስትና) ነው” የሚባለው በዚህ አግባብ ነውና፡፡

ይህ ሲባል ግን፣ ሁል ጊዜ ድርጊታችን ከዐስተሳሰባችን ይቀዳል ማለት አይደለም፡፡ ትክክል ያልሆነን ነገር፣ ትክክል አለመሆኑን እያወቅን እናደርጋለንና፡፡ መዋሸት ወይም ተገቢ ያልሆነ ቊጣ፣ ስሕተት መሆኑን እያወቅን፣ ስንዋሽና ስንቈጣ ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ ምግባራችን በዐስተሳሰባችን ላይመራ ይችላል፡፡ ለትክክለኛ ምግባር ግን ትክክለኛ ዕውቀት ማፈለጉን ማስተባበል አይቻልም፡፡ ሲ. ኤስ. ልዊስ፣ “አንድ መስመር ጠማማ  ነው ልትል የምትችለው፣ ስለ ቀጥተኛ መስመር ዕውቀት ሲኖርህ ነው” የሚለው በዚህ አግባብ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትም ምስክርነት ይኸው ነው (የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል:— ማቴ. 22÷23-33፤ ሮሜ 12÷3፤ 2ጢሞ. 4÷3-4)፡፡

ሦስተኛ፤ ትክክለኛ ትምህርት የተሳሳተውን መንገድ እንዳንከተል፣ የተሳሳተም ጐዳና ከእውነት እንደሚያፈናቅለን ያስተምረናል፡፡ የስሕተት መጨረሻ ጥፋት (ውድመት) ነውና (1ጢሞ. 4÷1-6፤ 2ጢሞ. 1÷3፤ 2ጢሞ. 2÷18፤ ቲቶ 1÷11)፡፡

አራተኛ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ዶክትሪን ከነገረን በኋላ ነው፣ ስለ ምግባራዊ ሕይወት የሚያስተምረን፡፡ ይህ ደግሞ ከርቱዕ ምግባር በፊት፣ ርቱዕ ትምህርት እንደሚቀድም ማረጋገጫ ነው (ኤፌ. 4÷1:11-12፤ ሮሜ 12÷1)፡፡

ሸ. የድነት መሠረት፣ ክርስቶስ ወይስ ርቱዕ ትምህርት?  

በርግጥ ትክክለኛው የሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት፣ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችንን የሚወስነው ከሆነ፣ ድነት የሚገኘው ደርዛዌ ነገረ መለኮትን በማወቃችንና ባለማወቃችን ነውን? ድነት ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን በመቀበላችን የሚገኝ ነገር ከሆነ፣ ክርስትና መሠረተ እምነትን ማወቅና ያለማወቅ ከድነት ጋር ተዳምሮ ለምን ቀረበ? ዕውቀታችን የድነት መሠረት ከሆነ፣ ሰው ሁሉ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ምግባት አለበት ማለት ነው? ምናልባትም የደርዛዌ ነገረ መለኮት ፈተና በመስጠት፣ የአንድን ሰው ድነት ማረጋገጥ ይቻላል ማለት ነው? እነዚህ ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህንና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች በጥሩ መንገድ ለመመለስ ግን፣ በቀጣይ የቀረቡትን ፅነሰ ዐሳቦችን መተዋወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይኸውም:— (1) ትውውቃዊ እምነት (Belief-In)፣ (2) ዐዋጃዊ እምነት (Belief-That) እንዲሁም (3) ዐብሮ መኖር (Living-With) የሚሉትን ፅንሰ ዐሳቦች መተንተን ያስፈልጋል፡፡    

ክርስትና ልዕለ ተፈጥሮአዊ ከሆነው አካል (ከአምላክ) ጋር አንድነት መፍጠር ነው፡፡ ትውውቃዊ እምነት (Belief-In)፣ ለአንድ አካል ራስን መስጠት እንዲሁም አንድን አካል ማመን (መቀበል)፣ ማለት ነው፡፡ ያዕቆብ 2÷19 ላይ፣ “እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል” በሚለው ምንባብ ውስጥ አጋንት እንኳ፣ ትክክል ነው ብለው የሚቀበሉት ዐዋጃዊ እምነት (Belief-That) እንዳለ የሚገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አጋንንት ከአምላክ ጋር ኅብረት የላቸውም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ዐሳብና ፈቃድ ለመኖር የወሰኑ ፍጡራን አይደሉም፡፡ እንዲያውም በአምላክና በዐላማው ላይ የሚያምፁ፣ አካላት ናቸው እንጂ፡፡ ልባቸውን፣ ፈቃዳቸውንና ምግባራቸውን ለአምላክ ፈቃድና ዐላማ የሰጡ መንፈሳውያን አካላት አይደሉም፡፡ እንዲያውም የአምላን ዐላማና ፈቃድ የሚጻረሩ አካላት እንደ ሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ስመ ጥሩ ስዊዘርላንዳዊ ነባቤ መለኮት፣ ካርል ባርት (Karl Barth) ይህን ጒዳይ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:— “በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው፣ እግዚአብሔርን ተስፋ ያደርጋል፤ እግዚአብሔርን የሙጥኝ ብሎ ይይዛል፤ በእርሱም ይደገፋል” ይላል[31]፡፡

ዐዋጃዊ እምነት (Belief-That) የምንለው ጒዳይ፣ ትውውቃዊ እምነት (Belief-In)፣ ከሚባለው ጒዳይ በብዙ ይለያል፡፡ ዐዋጃዊ እምነት ትክክለኛ የሆነውን ዐዋጅ ወይም ትምህርት ማወቅን ይመለከታል፡፡ አንድን አስተምህሮ ትክክለኛ ነው ብሎ መቀበልን ያሳያል፡፡ ስለ ገሓዱ ዓለም የቀረበውን አንድ ገለጻ፣ ከሌላው ገለጻ ወይም ትንታኔ ይሻላል ብሎ ማሰብን ይመለከታል፡፡ አንዳንድ ነባብያነ መለኮት፣ ይህ ዐይነቱን ዕውቀት፣ “የእምነት ሕግ” (Rule of Faith በላቲን፣ “Regula fidei”) ይሉታል፡፡ ይህ መሠረታውያን የሆኑትን ክርስቲያዊ አስተምህሮዎች የሚመለከት እምነት ነው፡፡

እምነት ገደፍ[32] በሆኑ የነገረ መለኮት ተቋማት ውስጥ የሚያስተምሩ የነገረ መለኮት ምሁራን፣ ስለ ክርስትናና ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ሰፊ ዕውቀት አላቸው፡፡ የሚያውቁትን ነገር ስለማይቀበሉ ግን፣ ክርስቲያን ነን አይሉም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ እንኳን በክርስትና በሀልዎተ እግዚአብሔር እንኳ አያምኑም፡፡

በአንጻሩ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስትና ሰፊ ዕውቀት ባይኖራቸውም፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል መድኀኒታቸው ተቀብለዋል፤ ከአምላክ ጋር ኪዳናዊ ትስስር አበጅተዋል፤ ሊከተሉት እንደ ዐሳቡና ፈቃዱ ሊኖሩ ወስነዋል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያን ታሪክን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ባይኖራቸውም፣ እግዚአብሔርን ግን በግል ያውቁታል፡፡ ጌታን በግል ለማወቅ ዝርዝር የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ዕውቀት የግድ አይፈልግም፡፡  ትውውቃዊ እምነት እጅግ ውስን፣ ነገር ግን መሠረታውያን የሆኑ ዐዋጃዊ እምነቶችን መፈለጉ እሙን ነው፡፡ ዐዋጃዊ ዕውቀት ግን፣ ትውውቃዊ እምነትን የግድ አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ትውውቃዊ ዕውቀት በተወሰነ መጠንም እንኳ ቢሆን ዐዋጃዊ ዕውቀትን በግብዐትነት ይፈልጋል፡፡ ዐዋጃዊው ግን ትውውቃዊውን የግድ አይሻም[33]፡፡

ክርስትና ትውውቃዊ እምነት እንዲሁም ዐዋጃዊ እምነት መፈለጉን አይተናል፡፡ የክርስትና ሕይወት በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ዐብሮ መኖር (Living-With)፣ በሚለውም ፅነሰ ዐሳብ ይጨምራል፡፡ ዐብሮ መኖር ሕይወትን በጋራ መካፈል ይፈልጋል፡፡ ዐብሮ መኖር መጠቃቀምን ታሳቢ ቢያደርግም፣ ዐብሮ በመኖር ውስጥ ጒዳትም ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ከጌታ ሞትና ትንሣኤ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርት በኅብረት ይኖሩና በኅብረት ለመኖርም ይተጉ እንደ ነበር፣ በዝርዝር ተጽፎአል (ሐሥ. 1÷12-26፤ 2÷1፤ 2÷42:44፤ 1ተሰ. 1÷2፤ ኤፌ. 6÷19፤ ገላ. 2÷11-14፤ 1ቆሮ. 11÷20-21)፡፡   

ክርስቲያን መሠረታውያን የተባሉትን ክርስቲያዊ ትምህርቶች ማወቅ አለበት፡፡ የክርስትናን መሠረታውያን ትምህርቶች የሚያውቅ ሰው ሁሉ ግን፣ ክርስቲያን ነው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያን ለመሆን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝና ጌታ አድርጎ ከመቀበል ባሻገር፣ መሠረታውያኑን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ማወቅ የግድ ይላል፡፡

አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላውቅም ማለት አይችልም፡፡ ወይም ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ለኀጢአቱ እንደ ሞተ፣ ሞትንም ድል አድርጎ እንደ ተነሣ አላውቅም ማለት አይችልም፡፡ ክርስቶስን ማወቅ መሠረታውያኑን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ማወቅ የግድ ይፈልጋል፡፡

የክርስትናን መሠረታውያን ትምህርቶች ማወቅ፣ የድነት ቅድመ ሁኔታ ከሆነ፣ ብዙ ክርስቲያኖች ትምህርተ ሥላሴን የማብራራት ዐቅም የላቸውም፡፡ ይህ ጒዳይ እንዴት ይታያል፣ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡

ትምህርት ሥላሴን ማመንና ትምህርተ ሥላሴን ማብራራት እጅግ የተለያዩ ጒዳዮች ናቸው፡፡ እውነትን ማወቅና ያወቁትን እውነት ማብራራት፣ እጅግ የተለያየ ጒዳይ ነውና፡፡ በአንድ ወቅት፣ “ሰዎች የሥላሴ ዕውቀታቸው ምን ያህል ነው?” የሚለውን ጒዳይ ለማጣራት፣ አባል በሆንሁበት የኢትዮጵያውያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ መጠይቅ በትኜ ነበር፡፡ “ሥላሴ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ማብራሪያ ጻፉ” ያልሁትን፣ ብዙዎቹ ማብራሪያውን በትክክል መጻፍ   አልተቻላቸውም፡፡ “አምናለሁ”፣ “አላምንም” በሚል ምላሽ የሚሰጣቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ  ዘጠና አራት ከመቶ (94%) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ ጥያቄውን በትክክል መመለስ ችለዋል፡፡ ከዚህ የምንማረው ብዙ ክርስቲያኖች ሥላሴን በተመለከተ የሚቀርበውን ዝርዝር ትምህርት በትክክል ባያውቁም፣ የተሳሳቱ ትምህርቶችን መሳሳታቸውን መግለጽ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች በትክክል የመለሷቸው ጥያቄወች የሚከተሉት ነበሩ:—

  • እግዚአብሔር ስንት ነው?
  • አብ ፍጹም አምላክ ነውን?
  • ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ የዓለማት ፈጣሪ እንዲሁም ስግደት የሚገባው አምላክ ነውን?
  • መንፈስ ቅዱስ፣ “ትንፋሽ” ነው ወይስ፣ የራሱ ማንነት ያለው አማኞችን ወክሎ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ አካል ነው?
  • አብ እና ወልድ አንድ አካል ናቸውን ወይስ የተለያዩ?
  • ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አካል ናቸው ወይስ የተለያዩ አካላት?

ጥያቄው ከቀረበላቸው ውስጥ፣ ዘጠና አራት ከመቶ (94%) የሚሆኑቱ፣ ጥያቄውን በትክክል በመመለስ፣ ሥላሴአዊ እምነታቸውን በትክክል አጽንተዋል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተዘረዘሩትን እነዚህን ጥያቄዎች መሠረት አድርገን፣ “አምላክ አንድ ከሆነ፣ በአንጻሩ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት ከሆኑ፣ ‘አንድ’ እንዲሁም ‘የተለየዩ አካላት’ የሚሉትን ቅራኔ መሰል ዐዋጆች እንዴት ያስታርቋቸዋል?” የሚለውን የማብራሪያ ጥያቄ፣ አጥጋቢ በሆነ መንገድ የመለሱ ሦስት ከመቶ (3%) የመሆኑት ብቻ ናቸው፡፡

ከዚህ መለስተኛ ጥናት የምንገነዘበው ሐቅ፣ ሰዎች ትምህርተ ሥላሴን ለማብራራት የሚያስችል ዕውቀት እንደሌላቸው፣ በዚህ ጒዳይ ቤተ ክርስቲያን ጠንክራ መሥራት እንዳለባት የሚያስገነዝብ ሲሆን፣ ትምህርተ ሥላሴ በተሳሳተ መንገድ ሲቀርብ፣ ይህ የእኔ እምነት አይደለም የማለት ዕውቀት እንዳላቸው አመልካች ነው[34]፡፡

በዐጭሩ ይህ ጥናት፣ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ትምህርተ ሥላሴ በቅዱሳት መጻሕፍት የተደገፈና በሥነ አመክንዮ የተብራራ መልስ መስጠት ባይችሉም፣ ስለ ሥላሴ የተዛባ ምልከታ አላቸው ማለት እንዳልሆነ አመልካች ነው፡፡  

ማጠቃያ  

በርቱዕ ትምህርትና በመናቃን መኻል ያለውን ዳር ድንበር የወሰነው፣ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ዐበይት እንዲሁም ዐበይት ያልሆኑ በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ በመናፍቃንና በርቱዕ ሃይማኖት መኻል ያለው ልዩነት፣ ከዐበይት ትምህቶች አንጻር የሚተነተን እንጂ፣ ደቂቃን የሚባሉትን ትምህርቶች የሚያጠቃልል አይደለም፡፡

ንዑሳን ትምህርቶችን ሁሉ በአንድ መስፈር አደገኛ ሊሆን ስለሚችል፣ አንዳንዶቹን ትምህርቶች፣ መኻል ሰፋሪ በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ ከትቶ፣ ክርስቲያኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉባቸው ማሳሰብ  ተገቢ ነው[35]፡፡ ድነት ያገኘነው ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ቢሆንም (ትውውቃዊ እምነት) ይህ እምነታችን ግን፣ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ዐዋጃዊ እምነት የሚፈልግ ነው፡፡

ክርስትና ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ አድርጎ በመቀበል (በትውውቃዊ እምነት) የሚጀመር ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ እምነት ግን መሠረታውያን የሚባሉትን፣ ስለ አምላክ ክርስትና የሚያቀርባቸውን ገለጻዎች (ዐዋጃዊ እምነቶች) በተወሰነ ደረጃም እንኳ ቢሆን፣ ማወቅ የግድ ይፈልጋል፡፡ ስለ እግዚአብሔር የብዙ ዕውቀት ባለቤት መሆን ብቻ፣ አንደን ሰው ክርስቲያን አያደርገውም፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ግን፣ ቢያንስ መሠረታውያን የሆኑ ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡     


[1] “በይሖዋ ምስክሮች” ታሪክና አስተምህሮ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ፣ የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “አርዮሳውያን የይሖዋ ምስክሮች አስተምህሮ በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን” የሚለውን መጽሐፍ ይመለከቷል፡፡

[2] “በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ታሪክና አስተምህሮ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ፣ የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “ሰባልዮሳውያን፤ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን” በሚል ርእስ ያሰናዳውን መጽሐፍ ይመለከቷል፡፡

[3] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ መሠረታውያን የሆኑትን ክርስቲናዊ ትምህርቶች (ለምሳሌ:— ትምህርተ ሥላሴ፣ ምስጢረ ሥጋዌ፣ ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ፣ ትምህርተ ጥምቀት፣ ትምህርተ ድነት) ለማመልከት “ዶግማ” የሚለውን ቃል ስትጠቀም፣ “ቀኖና” የሚለውን የግሪክ (የጽርዕ) ቃል ደግሞ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዐትን፣ ደንብን ወዘተ ለማመልከት ግልጋሎት ላይ ይውላል፡፡

[4] The Islamic State—IS.

[5] በዚህ ማስፈንጠሪያ፣ “The New York Times” ያቀረበውን ዘገባ ይመለከቷል: https://www.nytimes.com/2015/04/20/world/middleeast/isis-video-purports-to-show-killing-of-ethiopian-christians.html

[6] ዘፈን ነው መሰለኝ

[7] ትምህርተ ድነትን (soteriological or salvific) መሠረት ያደርጋሉ የሚባሉትን ትምህርቶች ታሳቢ አድርጌ ነው፡፡ “ድነት” የሚለውን ቃል የተጠቀምነው ዘላለማዊ ሕይወትን በሚያሳይ መልክ ነው፡፡ ቃሉ መጻፍ የነበረበት፣ “ድኅነት” ተብሎ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች የሆሄ ልዩነቱ በውል ባለመረዳት፣ “ድኽነት”  ማለትም ማጣት፣ መቸገር በሚለው ትርጒም ተረድተውት የተሳሳተ ግንዛቤ ላይ እንዳወድቊ፣ ብዙኃኑ፣ “ኀ” በማግደፍ፣ “ድነት” ብለናል፡፡  

[8] የሚከተለው መጽሐፍ ዐበይት የሚላቸው የሚከተሉትን ትምህርቶች ነው:— (1) የድንግል መውለድ፣ (2) የክርስቶስ አምላክነት፣ (3) ቤዞታዊ ሞቱ፣ (4) የአካል ትንሣኤ፣ (5) የክርስቶስ ዳግም ምጽአትና (6) የቅዱሳት መጻሕፍት አፊዎተ ቃልነት:— Ernest R. Sandeen, The Roots of Fundamentalism: British and American Millenarianism, 1800-1930 (Grand Rapids, MI.: Baker, 1978)፡፡ ይህ ብዙዎችን የሚያስማማ ዝርዝር አይመስልም፤ ምክንያቱም ትምህርተ ሥላሴ፣ የሰው ልጆች ኀጢአተኛነት፣ ክርስቶስ ኀጢአት አልቦ መሆኑ፣ ድነት በእምነት አማካይነት በጸጋ የሚገኝ የአምላክ ስጦታ መሆኑ ወዘተ አልተካተተም፡፡ 

[9] ከዘመነ ደርግ ጀምሮ፣ “መኻል ሰፋሪ” የሚለው ቃል፣ አሉታዊ እማሬ (connotation) ይዞአል፡፡ አስፋላጊ በሆነ ጊዜ በመኻል መስፈር፣ ትክክል እንጂ ስሕተት ሊሆን አይችልም፡፡ አሉታዊ እማሬው  በይርጋ የሚታገድ ስላልሆነ፣ እነሆ እኔ አዎንታዊ እማሬ ሰጥቼ አቅርቤዋለሁ፡፡ 

[10] ቢያንስ እኔ አላውቅም፡፡

[11] ትክክለኛ የሆነውን የቅዱሳት መጻሕፍት የአፈታት ጥበብ (ሥነ ትርጓሜ ያለመከተል) ለተሳሳተ ትምህርት ሊዳርግ ይችላል፡፡ አንድ ሰው የተሳሳተ የትርጓሜ አካሄድ መከተሉ ብቻ ግን መናፍቅ ሊያሰኘው አይችልም፡፡     

[12] ካቶሊካውያን፣ ኦርቶዶክሳውያንና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚስማሙባቸው የቤተ ክርስቲያን ጒባኤዎች (Ecumenical Councils) የሚከተሉ ናቸው:— የኒቂያ ጉባኤ (Council of Nicaea-325)፣ የቊስጥንጥኒያ ጉባኤ (Council of Constantinople- 381)፣ የኤፌሶን ጉባኤ (Council of Ephesus-431)፣ የኬልቄዶን ጉባኤ (Council of Chalcedon-451) ናቸው፡፡

[13] እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ያወጧቸውን የሃይማኖት መግለጫዎች፣ በመጽሐፉ መጨረሻ ዐባሪ በሚለው ክፍል ውስጥ፣ ማያያዣችንን ልብ ይሏል፡፡

[14] በመጽሐፉ መጨረሻ፣ ዐባሪ የተደርገውን ይመለከቷል፡፡  

[15] Norman L. Geisler and Chad V. Meister, Reasons for Faith: Making a Case for the Christian Faith (Wheaton, Ill.: Crossway Books, 2007), 95-111.

[16] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 96-97፡፡

[17] እስከ ቊጥር 8 ያለው፡፡

[18] ከቊጥር 9 ጀምሮ፡፡

[19] ዝኒ ከማሁ፡፡

[20] እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ የእንግሊዝኛ አቻ ስያሜአቸው እነሆ:— Justification, Sanctification, Glorification

[21] እኔ ከፕሮፌሰር ጋይዝለርን አካሄድ ካልተቀበልሁበት ምክንያት መኻል አንዱ፣ መጽደቅ ዐላፊውን ጊዜ ያመለክታል፤ እንዲሁም መቀደስ አሁን ያለውን የኀጢአት ተጽኖ ያሳያል የሚለው ገለጻቸው ትክክል መስሎ ስላልታየኝ ነው፡፡ ጽሑፋቸውን ቃል በቃል እነሆ:— “Justification is defined as salvation from the past penalty of sin; Sanctification is salvation from the present power of sin; and glorification is salvation from the future presence of sin.” ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 96፡፡ መጽደቅ ዐላፊያቱንም ሆነ መጻኢውን እንዲሁም አሁናዊውን ጊዜ ያመለክታል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ የልዩነት ምክንያት የሆነኝ ሌላ ነጥብ፣ ጋይዝለር ዐበይት ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን እንድንክድ ምክንያት ይሆናሉ ያሏቸውን ትምህርቶች ሁሉ፣ ዐበይት በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ከተዋቸዋል፡፡ እኔ እነዚን ትምህርቶች ዐበይት ከማለት ይልቅ፣ “መኻል ሰፋሪ” ማለቱ የተሻለ እንደ ሆነ ዐስባለሁ፡፡ ምክንያቱም መኻል ሰፋሪዎቹን በቀጥታ የአንድን ሰው ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ አልመሰለኝምነና፡፡

[22] ፕሮፌሰር ጋይዝለር፣ “መቀደስ” ክርስቶን በማመን የሚገኝ ሳይሆን፣ አሁን ከኀጢአት ጋር የምናደርገውን ትንቅንቅ አመልካች ነው ይላሉ፡፡ “Unlike justification, sanctification is not a positional matter before God: it is a practical matter on earth.”  ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 97፡፡ በርካታ የደርዛዌ መለኮት መጻሕፍት፣ “መቀደስ” ሁለት ገጽ እንዳለው፣ አንደኛው ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን እንደሚገኝ (positional sanctification–1ቆሮ. 6÷11፤ ዕብ. 10÷10፤ 1ጴጥ 2÷9)፣ ሌላኛው ደግሞ ጋይዝለር እንደሚሉት፣ ከኀጢአት ጋር ተፋልሞ ድል በመንሣት የሚገኝ (progressive sanctification–1ጴጥ. 1÷6:15-16፤ 2ቆሮ. 7÷1) እንደ ሆነ ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ:— የቆሮቶስ ክርስቲያኖች ምግባራዊ ችግር ያለባቸው ቢሆንም፣ ሐዋርያው በ1ቆሮንቶስ 1÷2 በክርስቶስ ኢየሱስ፣ “ቅዱሳን” ናችሁ ይላቸዋል፡፡ በአንጻሩ ተቀደሱ እያለ ያሳስባቸዋል፡፡ Positional anctification–የሚለውን የደርዛዌ ነገረ መለኮ መጻሕፍት በዚህ መልክ ይገልጹታል፣ “Positional sanctification relates to the fact that the believer has been redeemed and cleansed by the shed blood of Jesus Christ” — ይህ ዐይነቱ ቅድስና በሥራ የተገኘ ሳይሆን፣ ጌታን ከማመን ጋር የተያያዘ ነው (ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ደረጃ) ብለን እንድናምን እንገደዳለን፡፡ በዚህ ጒዳይ፣ የደርዛዌ ነገረ መለኮት መጻሕፍት የሚሰጡትን ትንተና ይመለከቷል፡፡     

[23] ፕሮፌሰር ጋይዝለር ዕርገት ከድነት ጋር የተያያዘበትን አግባብ ያብራሩት በሚከተለው መልክ ነው:— ኢየሱስ በሚያርግበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው፣ “እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ አይመጣም” (ዮሐ. 16÷7) እንዲሁም አብ የሰጠውን ተልእኮ ማጠናቀቁን በይፋ ለማወጀ ነው፡፡ ዕርገቱ ተልእኮውን ማጠናቀቁን በይፋ የሚያበሥርበት ስለሆነ (ዕብ 7÷25፤ 9÷11-12)፣ የድነታችን አንዱ ክፍል ነው ባይ ናቸው፡፡ ዝኒ ከማሁ፡፡      

[24] ፕሮፌሰር ጋይዝለር፣ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ሞትና ኀጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሸነፋቸው ይፋ የሚሆንበት ክሥተት ስለሆነ፣ ከድነታችን ጋር በቀጥታ ይያያዛል ባይ ናቸው፡፡ ስለዚህም እንደ ጋይዝለር ዐሳብ፣ ዳግም ምጽአት ዐበይት አስተምህሮ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁለተኛ ሙግት አድርገው ያቀረቡት፣ የአትናቴዎስ የሃይማኖት መግለጫ ዘላለማዊ ኲነኔን እንደ ዐበይት ትምህርት ስለሚጠቅስ፣ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ስለሆነ፣ የምጽአት ትምህርት ይህን ሁሉ ዐቅፎ ስለሚይዝ በዐበይት ትምህርት ውስጥ ይካተታል ባይ ናቸው፡፡ ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 97-98፡፡        

[25] እኔ የዶክትሬት ትምህርቴን የተከታተልሁት፣ እርሳቸው ያስተምሩበት በነበረው ትምህርት ቤት ነው፡፡ በእግራቸው ሥር የመማር ዕድል በማግኘቴም፣ እግዚአብሔርን አመስጋኝ ነኝ፡፡      

[26] የክርስቶስ የመስቀል ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ “ኢየሱስ ማነው?” የሚለውም ጒዳይ፣ የሰዎችን ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል፡፡ (ዮሐ. 8÷21:24፤ 3÷18:36፤ 424፤ 13÷19፤ ዕብ. 12÷25፤ 10÷26-29፤ 2÷3፤. ማር. 13÷6፤ ሐሥ. 4÷12፤ ሉቃ. 21÷8)፡፡ ይህ ደግሞ ከቊጥር 1 እስከ 4 እንዲሁም ቊጥር 6 እና 8 ይመለከታል፡፡     

[27] በዝርዝር ውስጥ ያላካተትኋቸው ነገር ግን እነዚህን መሰል ትምህርቶች በርካታ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

[28] C. S. Lewis, Mere Christianity (Geoffrey Bles, 1952).   

[29] Alvin Plantinga, Warranted Christian Belief (Oxford University Press, 2000), 7.

[30] ርቱዕ ትምህርት (orthodoxy) ርቱዕ ምግባር (orthopraxis)፡፡

[31] Karl Barth, Church Dogmatics. Volume 4: The Doctrine of Reconciliation, Part I. (Geoffrey W. Bromiley, trans. London: T & T Clark, 1956), 743.

[32] በእንግሊዝኛው፣ “secular” የሚለውን ቃል እንዲተካ የተቀመረ ነው፡፡

[33] ትውውቃዊ እምነትን (Belief-In) እንዲሁም ዐዋጃዊ እምነትን (Belief-That) በተመለከተ፣ የነገረ መለኮት ሰዎች የጦፈ ክርክር አላቸው፡፡ በሁለቱ ፅንሰ ዐሳቦች መካከል ያለው ልዩነት በተወሰንም እንኳ ቢሆን ረቂቅ እንዲሁ አወዛጋቢ ነው፡፡ የበለጠ መረጃ ከፈለጉ ይህን መጽሐፍ ይመለከቷል:— Gerald O’Collins, Rethinking Fundamental Theology (New york: Oxford University Press,  2011), 167.  

[34] ይህ ጒዳይ በእናንተ ዐውድ ምን ያህል ትክክል ነው የሚለውን ጒዳይ በትክክል ለመመለስ፣ ጥያቄውን ለእናንተ ጉባኤ በመጠየቅ ውጤቱን ማወቅ ይቻላል፡፡

[35] ዐበይት፣ መኻል ሰፋሪና ንዑሳን በሚሉት ማዕቀፎች ውስጥ የቀረቡት ዝርዝሮች የተሟሉ ስላልሆኑ፣ አንባቢ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፡፡

Share the Post:

Related Posts