ሀ. ትልም
የዚህ ምዕራፍ ቀዳማይ ዐላማ:—
- በዕቅበተ እምነት የሙያ ዘርፍ ውስጥ በብዛት የምንጠቀምባቸውን ሙያዊ ቃላት፣ ቋንቋዊና ነገረ መለኮታዊ ትርጒማቸውን እንተዋወቃለን፡፡
ፊት በር
በየትኛውም ቋንቋ፣ አንድ ቃል ከአንድ በላይ ትርጒም ሊወክል ይችላል፡፡ የቃሉን አማራጭ ትርጒም የሚወስነውም፣ ቃሉ የሚገኝበት ዐረፍተ ነገር ወይም ዐውድ ነው፡፡ የሥነ ሐቲት ሊቃውንት፣ “ከዐውዱ የተፋታ ቃል፣ ለተሳሳተ ዐላማና ድምዳሜ የተዳረገ ነው”[1] የሚሉት፣ ይህንን ሐቅ መሠረት አድርገው ነው[2]፡፡ ይህ መጽሐፍ ቊልፍ የሆኑ ሙያዊ ቃላት ምን ትርጒም እንደሚወክሉ በመግለጽ፣ የማለዳ ጒዞውን አሐዱ ብሉ ይጀምራል፡፡
የቋንቋ ፍልስፍና፣ የሰብአውያን ቋንቋ የሰዎችን ስምምነት መሠረት ማድረጉን ይገልጻል[3]፡፡ አህያን፣ “አህያ” መጽሐፍን፣ “መጽሐፍ” ለማለት፣ ከቋንቋው ባለቤቶች[4] ስምምነት ውጪ፣ አንዳችም ነባራዊ መሠረት የለም፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ የቃላት ስያሜም ሆነ የሰዋስው ሕግ መሠረቱ፣ የቋንቋው ተናጋሪዎች የቋንቋ አጠቀቀም ስምምነትና ቋንቋው የሚመራበት ሥርዐት (ሰዋስው) ብቻ፣ የተግባቦት አልፋና ዖሜጋ (ዋስትና) ነው፡፡ ይህ ሥርዐት ሲዛባ፣ ተግባቦት ይስተጓጐላል፤ ዐሳብ ይደነቃቀፋል፤ ሊተላለፍ ተፈለገው ጭብጥ፣ በተሳካ መንገድ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ሰው ሊሻገር አይችልም፡፡
የተለመዱ ቃላትን በተለመደ መልክ መጠቀም፣ የቋንቋው ተናጋሪ ግርታ እንዳይፈጠርበት፣ አሻሚ ትርጓሜ እንዳያድርበት ማድረጉ እሙን ነው፡፡ ዐዳዲስ ፅንሰ ዐሳቦችን ለማስተዋወቅ ግን፣ ዐዳዲስ ቃላትን መቀመር ወይም ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ ሲያገለግሉ የቈዩትን ቃላት፣ ዐዲስ ስያሜ አላብዞ ማቅረብ፣ አማራጭም አስገዳጅም አካሄድ ነው[5]፡፡
የቋንቋ ምሁራን፣ “ቃላት ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ” የሚለው አነጋገራቸው፣ ይህን እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የዚህ ምዕራፍ ቀዳማይ ዐላማና ግብ፣ በዕቅበተ እምነት ውስጥ አዘውትረን የምንጠቀምባቸውን ቃላት፣ ቋንቋዊና ነገረ መለኮታዊ ይዘታቸውን ማስተዋወቅ፣ ትርጒማቸውንም መወሰን (መቀንበብ) ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ በየትኛው ትርጒማቸው ግልጋሎ ላይ እንደ ዋሉ መግለጽ፣ የምዕራፉ ዐላማና ግብ ነው፡፡
ሀ. ትርጓሜ፣ ፍካሬና እማሬ
በምጽፋቸው የዕቅበተ እምነት፣ የፍልስፍናና የደርዛዌ ነገረ መለኮት መጻሕፍት ውስጥ፣ የቃላትን ትርጓሜና ዳር ድንበር የመበየን (የመወሰን) እንዲሁም ይህ ጥሩ ልማድ ነው የሚል፣ ነባር አቋም አለኝ፡፡
ሢሶ[6] ወይም እርቦ[7] የሚሆነው የዐማርኛ ቃል፣ ከልሳነ ግእዝ እንደ ተወረሰ ይታወቃል[8]፡፡ ዐማርኛ ከግእዝ የወሰዳቸውን ቃላት፣ ርባታቸውንና ጓዛቸውን በመመልከት ብቻ፣ ሥሪታቸው ግእዝ መሆኑን በቊርጥ መናገር ይቻላል[9]፡፡ በአርእስቱ ላይ የተቀመጡት ሦስቱም ቃላት ማለትም ትርጓሜ፣ ፍካሬና እማሬ ምንጫቸው ግእዝ መሆኑን በዚሁ አግባብ ማረጋገጥ ይቻላል[10]፡፡
“ፍካሬ” የግእዝ ቃል ሲሆን፣ “ተረጐመ፣ ፈታ፣ አፍታታ፣ ዘረዘረ፣ መረመረ” ማለት ነው[11]፡፡ ቋንቋን ወደ ቋንቋ ለመመለስ፣ “ትርጓሜ” ስንል፣ ቅኔ፣ ህልም፣ ረቂቅ የሆነ ዐሳብ ለመተንተን እንዲሁም ሌላ ኅቡእ (ድብቅ) የሆነን ነገር ለመተርጐም ግን፣ “ፍካሬ” የሚለውን ቃል እንጠቀማለን[12]፡፡ “እማሬ” ማለት ይኼ (እነሆኝ) ብሎ በጣት መጠቈም ነው[13]፡፡ አንዳንድ ጸሓፍት “ፍካሬ” እና “እማሬ” የሚለውን ቃል የእንግሊዝኛ፣ “connotation” እና “denotation” የሚሉትን ቃላት ለመተካት ተገልግለውበታል[14]፡፡ እኔ (ቢያንስ በዚህ ጽሑፍ)፣ “ፍካሬ” የሚለውን፣ “ትንታኔ፣ ሐተታ” የሚለውን ዐሳብ በሚወክል መንገድ የተጠቀምሁበት ሲሆን፣ እማሬን ግን፣ “የትንታኔው ፋይዳ፣ የትርጒሙ ገቢራዊ ፋይዳ” የሚለውን ዐሳብ እንዲይዝልኝ አድርጌአለሁ፡፡ ስለዚህ አንባብያን ፍካሬ የሚለውን ትንታኔና ሐተታ እንዲሁም እማሬ የሚለውን የትንታኔው ገቢራዊ ፋይዳ (በእንግሊዝኛ significance) ምንድን ነው፣ የሚለውን ዐሳብ በሚወክል መንገድ እንዲመለከቱ እጠይቃለሁ፡፡
ለ. ዕቅበተ እምነት በዐማኛና በልሳነ ግእዝ
“ዕቅበተ እምነት” በነገረ መለኮቱ ዓለም፣ ምን ትርጒም ወክሎ ግልጋሎት ላይ እንደሚውል እንዲሁም የስያሜው ቋንቋዊ መሠረት ምን እንደ ሆነ፣ በዐጭሩ እንመልከት፡፡
“ዐቃቢ” ወይም “ማቀብ” ከሚለው ቃል ጋር ተዛርፈው የሚነገሩ፣ በርካታ ስሞች አሉ፡፡ አስረጅ:— ዐቃቤ ሕግ፣ ዐቃቤ ንዋይ፣ ዐቃቤ ሥራይ፣ ዐቃቤ አገር፣ ዐቃቤ ሰዓት፡፡ “ዕቁብ” እንዲሁም “ማዕቀብ” የሚሉት ቃላት፣ ከዚህ ዘር አንቀጽ የተገኙ ናቸው፡፡ “ዐቃቢ” የሚለው ቃል፣ ሥሪቱ ግእዝ ነው[15]፡፡ ልሳነ ግእዝን ወደ ዐማርኛ በሚተረጒመው፣ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ[16] መጽሐፍ፣ “ዐቃቢ” ማለት፣ “የሚጠብቅ፣ ጠባቂ፤ ተመልካች፤ ከልካይ ማለት ነው”[17] ይላል ፡፡ “ተዐቀበ” ደግሞ ተገብሮ (ተደራጊ) ስለሆነ፣ “ተጠበቀ፤ ዘበኛ አስቆመ፤ ዐደራ ተሰጠ” ማለት ነው[18]፡፡ “ዐቃቤ ሕግ” ማለት ሕግን የሚጠብቅ የሚያስጠብቅ፣ የሕግ ተቈርቋሪ፣ የሕግ ጠበቃ፣ የሕግ ተመልካች፣ ሕግ ዐዋቂ ማለት ነው፡፡ “ዐቃቤ ሥራይ” መድኀኒት የሚጠብቅ፣ በእንግሊዝኛው “ፋርማሲስት” (pharmacist) የሚለውን ቃል ይዳበላል[19]፡፡ “ዐቃቤ አገር” አገር ጠባቂ፣ ወታደር፡፡ “ዐቃቤ ሰዓት” ሰዓት የሚቈጣጠር፣ በሰዓት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመ፡፡ “ዕቊብ” “በጥንቃቄ ተጠብቆ የሚጠራቀም ገንዘብ”፡፡ “የመዋጮ ገንዘብ፤ በአንድ ሰው እጅ ተጠብቆ፣ በዕጣ ለዕቊብተኛው የሚታደል”[20] ማለት ነው፡፡ “ዐቃቤ ንዋይ” ገንዘብን በኀላፊነት ወስዶ የሚያስቀምጥ፣ ተኣማኒ የገንዘብ ሹም (ኀላፊ)፡፡
“ዐቃቤ እምነት” የሚባለው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ የሆነውን የክርስትና መሠረታውያን ትምህርቶች ወይም የክርስትናን ንጽሮተ ዓለም ከመናፍቃን፣ በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ ሆነው ክርስትናን የሚተቹ ተቺዎች፣ ከኢማኒያን ፍልስፍና እንዲሁም የተለየ ንጽርዖተ ዓለም ውስጥ ካሉ ነቃፊዎች የሚጠብቁ፣ ሌሎች እንዲጠብቁ የሚያበረታቱ፣ ሌሎች ክርስቲያኖች ክርስትናን እንዲያቅቡ በዕውቀት የሚያስታጥቁ፣ ለክርስትና እውነት የሚሟገቱ (የሚያሟግቱ) ክርስቲያኖች የአገልግሎ መጠሪያ ነው[21]፡፡
የሙያው መጠሪያ ደግሞ፣ “ዕቅበተ እምነት” ነው[22]፡፡ “ጻፈ” ግሥ ወይም ድርጊት ነው፡፡ ሙያው ደግሞ፣ “ጽሕፈት” ነው፡፡ በዚሁ አግባብ፣ “ዐቀበ” ድርጊት ከሆነ፣ “ዕቅበት” ደግሞ የሙያው መጠሪያ ይሆናል ማለት ነው[23]፡፡ ይህ የሰዋስው አመክንዮ ትክክል ከሆነ[24]፣ “ዕቅበተ እምነት” የሚለው ስያሜ በእንግሊዝኛው፣ “Christian Apologetics” የሚለውን ሙያዊ ቃል በትክክል ይወክላል፡፡ የልሳነ ግእዝንና የዐማኛውን ሙያዊ ቃል ይህን ያህል ከመረመርን ዘንዳ፣ አሁን ደግሞ የእንግሊዝኛውን አቻ ቃል እንመልከት፡፡
ሐ. ዕቅበተ እምነት በበኲረ ጽሑፋት
“አፖሎጄቲክስ”፣ “apologetics” የሚለው የእንግሊዝኛ ስያሜ የተወለደው፣ ከልሳነ ጽርዕ (ከግሪክ ቋንቋ) ሲሆን፣ ዘር አንቀጹ (ስም)፣ “አፖሎጊያ” “ἀπολογία”፣ ግሡ ደግሞ፣ “አፖሎጊዮማይ” “ἀπολύομαι” ወይም “አፖሉኦ” “ἀπολύω” ነው[25]፡፡
የግሪክ ቋንቋ ባለቤቶች፣ “አፖሎጊያ” “ἀπολογία” ሁለት ቃላት በአንድ ተዳብለው፣ የፈጠሩት ስያሜ እንደ ሆነ ያስረዳሉ፤ ይኸውም:— “አፖ” “ἀπο” “ማራቅ” ወይም “ማብረር” የመነሻው ክንፍ (ምዕላድ) ሲሆን፣ “ሎጊያ” “λογία”፣ “ንግግር” ወይም “ቃል” ማለት ደግሞ፣ የመድረሻው ግማሽ ክፋይ ነው፡፡ በተገናኝ፣ “ውንጀላን፣ ነቀፌታን፣ ክስን በቃል ከራስ ማብረር (መከላከል)” ማለት ነው[26]፡፡
የጥንት አቴና ነዋሪዎች፣ “አፖሎጊያ” “ἀπολογία” የሚለውን ቃል፣ በችሎት ዐውድ አብዝተው ይጠቀሙበት እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ተከሳሽ ጥፋተኛ ነህ የተባለበትን ሙግት ለማስተባበልና ንጹሕነቱን ለማረጋገጥ፣ በፍርድ አደባባይ የሚያቀርበውን አጸፋና ማስረጃ አመልካች ነው፡፡ የክሱ ዶሴ (መዝገብ) ከተነበበ በኋላ ተከሳሽ፣ በእርሱ አንጻር ያለውን፣ “አፖሎጊያ” እንዲያቀርብ ይፈቀድለታል፡፡
በዚህ ረገድ፣ የጥንት ግሪካውያን የችሎት አካሄድ ምን ይመስላል የሚለውን በጥሩ መንገድ የሚያሳየን፣ የታላቁ ፈላስፋ የሶቅራጥስ የፍርድ ውሎና አሟሟት ነው[27]፡፡ ሶቅራጥስ የተወነጀለው በአራት ተያያዥ ክሶች እንደ ነበር ይነገራል[28]፡፡ በወንጀሉም ጥፋተኛ ነህ በመባሉ፣ በወቅቱ ትልቅ ወንጀል የተገኘባቸው ሰዎች፣ የሄምሎክ መርዝ ጠጥተው እንዲገደሉ ይደረግ ስለነበር፣ ይህን ታላቅ ፈላስፋ ሄምሎክ አጠጥተው ገደሉት[29]፡፡
በዐዲስ ኪዳን ግሪክ፣ ቃሉ ስም ሆኖ ስምንት ጊዜ፣ ግሥ ሆኖ ደግሞ ዘጠኝ ጊዜ ግልጋሎት ላይ እንደ ዋለ የጽርዕ (የግሪክ) መዛግብተ ቃላት ያስረዳሉ[30]፡፡ በስም መልክ ጥቅም ላይ የዋለባቸው ቦታዎች እነሆ[31]:—
- “እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት (ἀπολογίας)[32] ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው” (ሐሥ 25÷16)።
- “ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት (ἀπολογίαν)[33] ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅንኣት፣ እንዴት ያለ ተግሣጽ እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ” (2ቆሮ. 7÷11)።
- “በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና (ἀπολογίᾳ)[34] ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና” (ፊልጵ 1÷7)።
- “እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት (ἀπολογίαν)[35] እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ” (ፊልጵ. 1÷16)።
- “በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ (ἀπολογίᾳ)[36] ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው” (2ጢሞ. 4÷16)።
- “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት (ἀπολογίαν)[37] ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት” (1ጴጥ. 3÷15)።
- “‘ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አሁን የማቀርብላችሁን የመከላከያ መልሴን (ἀπολογίας)[38] ስሙኝ’” (ሐሥ. 22÷1)።
- “ለሚመረምሩኝ የምሰጠው መልስ (ἀπολογία)[39] ይህ ነው” (1ቆሮ. 9÷3)።
ዐዲሱ መደበኛ ትርጒም[40]፣ “አፖሎጊያ” “ἀπολογία” የሚለውን ዘር አንቀጽ፣ “መልስ መስጠት”፣ “ለወንጌል መመከት”፣ “ለወንጌል መሟገት”፣ “መከላከያ ማቅረብ”፣ “መከላከያ መልስ” ብሎ የተተረጐመው ሲሆን፣ ነባሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም ደግሞ[41]፣ “ለተከሰስሁበት መልስ”፣ “ወንጌልን መመከቻ”፣ “ሙግት”፣ “መልስ መስጠት”፣ “ነገርን መግለጥ” ብሎ ተርጒሞታል፡፡ 1879 ትርጒም[42] ደግሞ፣ “ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ለፊት መቆም”፣ ለመርማሪዎች የሚሰጥ፣ “ምላሽ”፣ “ስለወንጌል ምላሽ” መስጠት፣ የፍርድ ቤት “ክርክር”፣ “መናገር” ብሎ ተርጒሞታል፡፡ 1980 ትርጒም[43] ይህንኑ ቃል፣ “መከላከያ”፣ “የመከላከያ መልስ”፣ “መከላከያ ማቅረብ”፣ “የምሥራች ቃል ማብሰር” ብሎታል፡፡
“ሕያው ቃል” የዐዲስ ኪዳን ትርጒም[44]፣ “የመከላከያ መልስ”፣ “ተገቢውን መልስ መስጠት”፣ “ፍርድ ቤት መቅረብ”፣ “ወንጌልን ማስተማር”፣ “ስለእውነት መመስከር”፣ “ንጹሓን መሆናችሁን እንድታስመሰክሩ”፣ “ጒዳይን በአግባቡ ማጣራት” ብሎታል፡፡ ሕያው ቃል፣ ከቊማዊ ትርጒም ይልቅ፣ ለዐውዳዊ ትርጒም ትኲረት የሚሰጥ እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡
“አፖሎጊያ”፣ “ἀπολογία” በስም መልክ ከቀረበባቸው ስምንት ምንባባት መኻል አራቱ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የራሱን ንጽሕና ከከሳሾቹ (ከወደረኞቹ) ለመከላከል ያቀረበውን ሙግት አመልካች ሲሆን (ሐሥ. 22÷1፤ 25÷16፤ 1ቆሮ. 9÷3፤ 2ጢሞ. 4÷16)፣ አራቱ ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል እውነተኝነት ከባላንጣዎቹ ለመከላከል የቀረበውን ማረጃ አመልካች ነው (ፊልጵ. 1÷7፤ 1÷16፤ 2ቆሮ. 7÷11፤ 1ጴጥ. 3÷15)[45]፡፡
በአንደኛ ጴጥሮስ 3÷15 ላይ፣ ክርስቲያኖች ዕቀበተ እምነትን ሥራዬ ብለው እንዲተገብሩት፣ በሚያሳስብና በሚያስጠነቅቅ መልክ በትእዛዝ አንቀጽ ተቀምጦ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ራሳቸውን ለዚህ ትልቅ ሙያ ሎሌ አድርገው ያሳደሩ ሰዎች እንደ ነበሩ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በስፋት ያስተምራል[46]፡፡
እስካሁን ያየነው፣ “አፖሎጊያ” “ἀπολογία” የሚለውን የበኲረ ጽሑፍ ቃል፣ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጸሓፍያን፣ ምን ዐይነት አማራጭ ትርጒም ወክሎ ግልጋሎት ላይ እንዲውል እንዳደረጉ የሚለውን የሚያብራራ ነበር፡፡ ነባብያነ መለኮት ቃሉን የሚጠቀሙበት በዚሁ አግባብ ነው፡፡
“አፖሎጊያ” “ἀπολογία” የሚለው ቃል ግልጋሎት ላይ ሳይውል የዕቅበተ እምነትን አገልግሎት የሚመለከቱ ምንባባትን በብዛት እናገኛለን[47]፡፡ ለምሳሌ:—
- “በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን” (2ቆሮ. 10÷5)።
- “እውነትን ወደ ማወቅ ይደርሱ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን እንደሚሰጣቸው ተስፋ በማድረግ የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል” (2ጢሞ. 2÷25)።
- “ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅሥ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት” (ቲቶ 1÷9)።
- “ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጕቼ ነበር፤ ነገር ግን ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” (ይሁዳ 3)።
ስለዚህ የቃሉን ቋንቋዊ ትርጓሜና ነገረ መለኮታዊ አጠቃቀም በሚከተለው መልክ መቋጨት ይቻላል:— በማስረጃና በሙግት የተደገፈ መከላከያ ማቅረብ፤ እውነት ያልሆነን አመለካከት ወይም አስተምህሮ በማስረጃና በሙግት የተደገፈ አጸፋ በማቅረብ ከንቱነቱን ማሳየት፤ ስለ እውነት ጥብቅና መቈም፤ የወንጌልን ንጽሕናን ማወጅ፤ ስሑት ሙግቶችን በማስረጃና በሙግት ከትክቶ መጣል፤ ጤናማውን ትምህርት የሚቃወሙ ሰዎችን መገሠጽ፤ እውነተኛውን ትምህርት መደገፍና የኂስ ጭብጥ ማምከን፡፡
መ. የኑፋቄ ቋንቋዊ ፍቺ
የዕቅበተ እምነት ቀዳማይ ትኲረት መኻል አንዱ መናፍቃን በመሆናቸው፣ መናፍቅ የሚለው ቃል፣ ቋንቋዊ ትርጒሙና ነገረ መለኮታዊ አጠቃቀሙ ምን እንደ ሆነ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
- “ኑፋቄ” የሚለው ቃል፣ “ነፊቅ” ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን፣ “ነፊቅ፤ (ነፈቀ፤ ይነፍቅ፤ ይንፈቅ)፤ መንፈቅ መሰንጠቅ፤ አስተካክሎ መክፈል መለየት”[48]፡፡
- “መናፍቅ፤ (ቅት፤ ቃን፤ ቃት)፤ ናፋቂ፣ አናፋቂ፣ የሚጠራጠር፤ ጠርጣሪ አጠራጣሪ፤ ሃይማኖቱ ሕጹጽ የኾነ፤ ምሉዕና ፍጹም ትክክል ያይደለ፤ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ”[49]፡፡
- “ኑፋቄ፤ (ያት)፤ በቊሙ፤ መክፈል፣ መከፈል፤ ክፍያ አከፋፈል ጥርጥር፣ ጥርጠራ፤ ምንታዌ”[50]፡፡
እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “ኑፋቄ” የሚለው ቃል፣ “ነፊቅ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን፣ ትርጒሙም አንድን ነገር አስተካክሎ ለሁለት መክፈል፣ ማመንታት ወይም መጠራጠር፣ እምነተ ሰንካላ መሆን፣ ግማሹን አምኖ ግማሹን መካድ፣ በአጠቃላይ ሃይማኖቱ ሕጹጽ (ጐደሎ) የሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ የግእዝ መዝገበ ቃላት ፍቺ ነው፡፡ የዐማርኛ አቻውን ደግሞ እንመልከት፡፡
ከሣቴ ብርሃን ተሰማ፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ኑፋቄ የሚለውን ቃል በሚከተለው መልኩ ይመታዋል፡፡
- “ነፈቀ፤ ዐመትን ዕለትን ወርን ከፈለ፣ ለየ ወይም አንድ ሙሉ የኾነ ነገርን ከኹለት ከፈለ ወይም የብርቱካንን፣ የሎሚን አካል ክፍልፋዮች በየክፍላቸው ለየ”፡፡
- “ነፈቀ፤ ከሃይማኖት ወጣ፤ ተጠራጠረ፤ መናፈቅን፣ ከሓዲን ኾነ ነፈቀ”፡፡
የዐማርኛው ገለጻ በአብዛኛው ከግእዙ ጋር አንድ ቢሆንም፣ “ከሃይማኖት መውጣት፣ ከሓዲ መሆን” የሚለውን ትርጒም ጨምሮአል፡፡ በአጠቃላይ ኑፋቄ የሚለው ቃል ቋንቋዊ አጠቃቀሙ:—
- “አንድን ነገር ለሁለት አስተካክሎ መክፈል፤ ማመንታት ወይም መጠራጠር፤ ግማሹን አምኖ ግማሹን በመካድ፤ እምነተ ሰንካላ ወይም ከሓዲ መሆን” ማለት ነው፡፡
ሠ. ኑፋቄ በዐዲስ ኪዳን በበኲረ ጽሑፋት
እኛ በዐማርኛችን ኑፋቄ የምንለውን ቃል ፈረንጆቹ፣ “ከልት” (cult) እና “ሔረሲ” (heresy) የሚባሉትን ቃላት አቀያይረው ይጠቀማሉ፡፡ “ከልት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፣ “ከልተስ” ከሚለው የላቲን ቃል እንደ ተወረሰ ይነገራል[51]፡፡ ትርጒሙም፣ “ማምለክ ወይም ለመለኮት ክብርን መስጠት” ማለት ነው፡፡ የላቲን ቨልጌት፣ ቃሉን ለእውነተኛው አምላክም ሆነ ለጣዖታት የሚቀርበውን አምልኮ በሚያመለክት መልክ ተገልግሎበታል፡፡ ለምሳሌ:— በሐዋርያት ሥራ 17÷23 ላይ የአቴና ሰዎች ያመልኳቸው ለነበሩ ጣዖታት ይቀርብ የነበረውን አምልኮ ሲያመለክት፣ በቊጥር 25 ላይ ደግሞ፣ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ” የሚሰጠው ልዑል እግዚአብሔር የሚሰጠውን አምልኮና ክብር ለማሳየት፣ ቃሉ ጥቅም ላይ ውሎ እንመለከታለን[52]፡፡
ይህ ትርጒም እኛ ልንጠቀምበት ካሰብነው እንዲሁም ዛሬ በዕቅበተ እምነት የትምህርት ዘርፍ ውስጥ፣ “ከልት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፣ ግልጋሎት ላይ ውሎ የምናገኘው በዚህ ትርጒሙ አይደለም፡፡ “ከልተስ” የሚለው ቃል አምልኮ ከሚለው ትርጒሙ ኑፋቄ ወደሚለው ትርጒሙ እንዴት ሊሸጋገር ቻለ የሚለው ጒዳይ፣ የሌላ ጥናት ጭብጥ ስለሆነ፣ ይህን ጒዳይ ለመመልስ አንሞርም፤ ከእኛ ጥናት ጋር አንዳችም ዝምድና የለውምና[53]፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ የዕቅብተ እምነት መጻሕፍት፣ “ከልት” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት፣ “አምልኮ” በሚለው ትርጒሙ ሳይሆን፣ “ኑፋቄ” የሚለው ትርጒም እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡
“ሔረሲ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፣ “ሔረሲስ” (αἵρεσις) ከሚለው የግሪክ ቃል የተወረሰ ሲሆን ትርጒሙም፣ “ምርጫ” ወይም “የተመረጠ” ማለት ነው[54]፡፡ ቃሉ በዐዲስ ኪዳን ግሪክ ጥቅም ላይ የዋለው፣ “ክፍፍል” ወይም “ልዩነት” በሚለው ትርጒሙ ነው (የሚከተሉን ክፍሎች ይመለከቷል:— ሐሥ 24÷14፤ 1ቆሮ. 11÷19፤ ገላ. 5÷19-20)፡፡ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፣ “ሔረሲ” የሚለውን ቃል ትገለገልበት የነበረው፣ መሠረታዊ የሆኑትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ለሚቃወም ግለሰብ ወይም እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ክርስቲያኖች ከእንዲህ ዐይነቱ ሰው ወይም እንቅስቃሴ መራቅ ወይም መለየት እንዳለባቸው በሚገልጽ መልኩ ግልጋሎት ላይ ውሏል (ሐሥ 24÷14 ይመለከቷል)[55]፡፡
ረ. ተጨማሪ ቃላት
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ የነገረ መለኮት መጻሕፍት ከልት እና ሔረሲ ከሚሉት ቃላት በተጨማሪ፣ “ኦከልት” (occult) እና “ሴክት” (sect) የሚሉትን ቃላት ይጠቀማሉ፡፡ ስለዚህ ስለእነዚህ ቃላት መጠነኛ ገለጻ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
“ኦከልት” የሚለው ቃል “ኦከልተስ” (occultus) ከሚለው የላቲን ቃል የተወለደ ሲሆን ትርጒሙም፣ “የተደበቀ” ወይም “ምስጢር” ማለት ነው፡፡ የዐማርኛ ጽሑፎች ለዚህ ቃል የሚሰጡት ትርጒም የተለያየ ሲሆን (ለምሳሌ:— አስማተኛ፣ ድግምተኛ፣ መተተኛ፣ ጠንቋይ፣ ቃላተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ዕድል ነጋሪ)፡፡ አብዛኞቹ የሚጠቀሙበት ግን፣ “ጥንቈላ” የሚለውን ስያሜ ነው፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ጥንቈላ (ኦከልት) በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የሚከፈሉ ሲሆን፣ እነዚህም:— (1) መናፍስት ጠሪት፣ (2) ዕድል ነጋሪነት እንዲሁም (3) አስማት ናቸው፡፡ እነዚህም ነገሮች በተለያየ መንገድ ይከወናሉ (ለምሳሌ:— ሞራ በመግለጥ፣ ጠጠር በመጣል ወዘተ)[56]፡፡
ምንም እንኳ አንዳንድ መናፍቃዊ ድርጅቶች ከጥንቈላ ጋር ንክኪ ቢኖራቸውም፣ ኑፋቄን ከጥንቈላ (ከኦከልት) ጋር በአንድ ቀይጠን መመልከት የለብንም፡፡[57]
“አሜሪካን ሄሪቴጅ” የተባለው የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት፣ “ሴክት” የሚለውን ቃል፣ “ሰፊና ትልቅ ከሆነው ሃይማኖት ተገንጥሎ የወጣ የሃይማኖት ክፍል” ሲል ይገልጸዋል[58]፡፡
ብዙ የነገረ መለኮት መዛግብተ ቃላት፣ “ሴክት” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ክርስቲያኖች ሆነው የሃይማኖት ባለሥልጣናትን የማይቀበሉ እንዲሁ ከቤተ ክርስቲያን ራሳቸውን ያገለሉ፣ ነገር ግን ጥለውት የሄዱት ቤተ እምነት አጒድሎታል የሚሉትን ትምህርት አጠንክረው የሚሰብኩትን ሰዎች ወይም እንቅስቃሴዎችን ነው[59]፡፡
በልሳነ ግእዝ “ርቱዕ”፣ “የረታ፣ የቀና፣ ቅን፣ እውነተኛ፣ ቀጥ ያለ፣ የተስተካከለ፣ ዐባጣ፣ ጐባጣ ያልሆነ” ስሕተት (ሕጸጽ) የሌለበት ማለት ነው[60]፡፡ ብዙ ጊዜ ትክክለኛ የሆነ እምነት ወይም ትምህርት፣ “ርቱዕ” በሚለው ቃል ይገለጣል፡፡ “ርቱዕ” የኑፋቄ አጸፋ (ተቃራኒ ቃል) ነው፡፡ “ርቱዕ ሃይማኖት” እንዲሉ፡፡
“ርቱዕ” የሚለው ቃል፣ የእንግሊዝኛ አቻው፣ “ኦርቶዶክስ” (orthodoxy) የሚለው ቃል ነው፡፡ እንግሊዝኛ ቃሉን የወሰደው “ኦርቶዶክሲያ” (ὀρθοδοξία) ከሚለው የግሪክ ቃል ነው፡፡ “ኦርቶዶክሲያ” (ὀρθοδοξία)፣ “ኦርቶስ” እና “ዶክሳ” የሚሉት ሁለት ቃላት፣ በተገናኝ የፈጠሩት እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ “ኦርቶስ” ግጽል ሲሆን፣ “የተስተካከለ፣ ቀጥተኛ ወይም ሥሙር” ማለት ነው፡፡ በዚህ አግባብ ኦርቶዶክስ መዛኝ ሥርው[61] ሲሆን፣ አዎንታዊ አንድምታ[62] ይዞ ትክክለኛ፣ እውነተኛ፣ የሚለውን ዐሳብ ወርሷል፡፡ አንድ ትምህርት ወይም ዐሳብ፣ “ኦርቶዶክስ” ነው ከተባለ፣ ትክክለኛ የሆነ፣ መልካም የሆነ፣ ቀጥተኛ የሆነ፣ ዘወርዋራ ያልሆነ፣ ጥመት የሌለበት ማለት ነው፡፡
“አባይ ነባይ” የሚለውንም ሐረግ በብዛት እንጠቀማለንና ትርጒሙ እነሆ:— ነቢይ፣ የሚለው ቃል፣ “ነበየ” ከሚለው ዘር አንቀጽ የሚወጣ ሲሆን፣ “ነበየ” ማለት፣ ነቢይ ኾነ፣ ትንቢት ተናገረ ማለት ነው[63]፡፡ ነባዪ[64]:— በቊሙ[65]፤ የሚተነብይ፣ ተንቢ ነባቢ፤ ትንቢት ያደረበት፤ ራእይ የሚያይ ትንቢት የሚናገር፤ ሰባኪ መምህር[66]፡፡ ነቢያዊ[67]:— የነቢይ ወገን፤ ነቢይ፤ ረድ ደቀ መዝሙር፤ ሀብተ ነቢይ የተሰጠው፤ እንደ ኢያሱና እንደ ኤልሳዕ ያለ[68]፡፡ ነቢይ፤ ወደ ፊት ሊሆን፣ ሊመጣ ወይም ሊደርስ የሚችለውን ነገር አስቀድሞ የሚናገር የእግዚአብሔር ሰው[69]፡፡ ነቢይ፤ በቊሙ ያለፈውንና የሚመጣውን ዐውቆ የሚናገር ሰው፣ ብቃት ያለው፡፡ ነባይ ዐማርኛ፤ ነቢይ ግእዝ ነው[70]፡፡ ነቢየ ሐሰት፤ ያላየውን አየኹ፣ ያልሰማውን ሰማኹ የሚል የሐሰት ነቢይ[71]፡፡ ነቢየ ጽድቅ፤ የእውነት ነቢይ[72]፡፡
ነቢይ ግእዝ ሲሆን፣ ነባይ ደግሞ የዐማርኛ አቻው ነው፡፡ በዐጭሩ፣ “አባይ ነባይ” ማለት ሐሰተኛ፣ ዋሾ፣ አምላክ ያልሰጠውን ሰጠኝ፣ ያልነገረውን ነገረኝ እያለ የሚቀላምድ፣ ቈርጦ ቀጥል ማለት ነው፡፡
“ዶክሳ”(δόξα)[73] ሁለት ዐቢይ ትርጒም እንዳለው ይነገራል፡፡ በግሪካውያኑ ዘንድ አመለካከት፣ ዐሳብ ወይም ብያኔ ማለት ሲሆን፣ አንድ ሰው በአንድ ዐዋጅ ላይ ያለውን አቋም አመልካች ነው፡፡ በዕብራውያኑ ዘንድ ደግሞ ክብር፣ ልዕልና፣ ግርማ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ:— የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም በዘፀአት 16÷10 ላይ፣ የእግዚአሔር ክብር (“ሄ ዶክሳ ኩርዩ” ἡ δόξα κυρίου) ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በማቴዎስ 4÷8 ላይ፣ “ክብር” (“ቴን ዶክሳ አውቶን” τὴν δόξαν αὐτῶν) በሚለው ትርጒሙ ግልጋሎት ላይ ውሏል፡፡ ከዚህ የምናማረው ቊም ነገር፣ “ዶክሳ” በግሪካውያኑ ዘንድ አንድን አመለካከት ትክክል ነው ብሎ መቀበልን አመልካች ሲሆን፣ በዕብራውያኑ ዐውድ ደግሞ ቃሉ ክብርን፣ የላቀ ድምቀትን፣ ልዕልናን አመልክቶአል፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ባርነት ዐርነት ሲወጡ፣ በሰብዓ ሊቃናት ትርጒም (LXX)፣ “እርሱ አምላኬ ነው ከፍ አደርገዋለሁ (δοξάσω)”[74] ተብሏል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1÷21 ላይ ጣዖት አምላኪ የሆኑ አሕዛብን፣ “እንደ እግዚአብሔርነቱ (እንደ ልዕልናው ወይም እንደ ክብሩ) መጠን እግዚአብሔርን ስላላከበሩት”[75] በሚልበት ቦታ፣ ልዕልና (ክብር) ለሚለው፣ “ዶክሳ” የሚለውን ቃል ተጠቅሞአል፡፡
በዮሐንስ 7÷39 ላይ፣ “ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበር”[76] በሚለው ቦታ፣ “ዶክሳ” የሚለው ቃል ግልጋሎት ላይ ውሏል፡፡ የዕብራውያኑንና የግሪካውያኑን አጠቃቀም በአንድ ከቀየጥነው ርትዕ በሆነ መንገድ አምላክን እንደ ክብሩ መጠን ማምላክ የሚል ትርጒም እናገኛለን፡፡ ይኸውም የትምህርት ጥራትንና የልዕልናል ምጥቀትን ያመለክታል፡፡
ሰ. የኑፋቄ በነገረ መለኮት መጻሕፍት
የቋንቋ ሊቃውንት፣ “ኑፋቄ” ለሚለው የግእዝ ቃል የሚሰጡትን ቋንቋዊ ፍቺ መሠረት አድርገን ነገረ መለኮት ሐተታው ውስጥ ከገባን፣ በብዙ እንሳሳታለን፡፡ ለምሳሌ:— መናፍቅ፣ “መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የካደ ሰው ነው” የሚለውን የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ፍቺ ይዘን ከሄድን፣ ነገረ መለኮት ይዛባል፡፡ ምክንያቱም በነገረ መለኮቱ ዓለም መሠረታውያን ከሆኑ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች መኻል አንዲት ቅንጣት ትምህርት የካደ (ያገደፈ፣ ያሳሳተ) ሰው፣ መናፈቅ እንቅስቃሴውም ኑፋቄ ይባላልና፡፡
ይህ ደግሞ ቋንቋዊ አጠቃቀሙን ብንቀበል እንኳ፣ ቋንቋዊ ዐዋጁን በነገረ መለኮት አካሄዱ ጋር አስማምተን መጠቀም እንዳለብን አስተማሪ ነው፡፡ ስለዚህ በነገረ መለኮቱ ዓለም ቃሉ ምን ትርጒም ወክሎ ግልጋሎት ላይ እንደሚውል መመልከት ይገባል፡፡ ነባብያነ መለኮት፣ “ኑፋቄ” ወይም “መናፍቅ” ለሚለው ቃል የሚሰጡት ትርጒም ለየቅል ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የሚስማሙበትና በርካታ የነገረ መለኮት መጻሕፍት ቃሉን የሚገለገሉበት በሚከተለው መልክ ነው:—
- “ከክርስትና እምነት የወጡ መናፍቃን ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ፤ በመሪዎቻቸው ወይም በድርጅቶቻቸው የተሰጠውን የተወሰነ አስተምህሮአዊ ሥርዐት የሚከተሉ፤ ይህም አስተምህሮአዊ ሥርዐት ከሥልሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍት የተቀዳውን የክርስትና እምነት መሠረታውያን ትምህርቶች መኻል አንድ ወይም ከአንድ በላይ ትምህርት የሚክዱትን፣ መናፍቃን ብለን እንጠራቸዋለን”[77]፡፡
ሸ. የዐዋጁ ሐተታ
ከላይ ኑፋቄ ለሚለው ቃል የሰፈረው የነገረ መለኮት ሐተታ፣ እጅግ ወሳኝ ጒዳይ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንድ ዐሳቦች ሰፊ ማብራሪያ የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ ኑፋቄ የሚለው ቃል በነገረ መለኮቱ ውስጥ ምን ትርጒም ወክሎ ግልጋሎት ላይ እንደ ዋለ፣ በግልጽ እንመልከት[78]፡፡
- “ከክርስትና እምነት የወጡ መናፍቃን…”
መናፍቃን በአስተምህሮ ልዩነት ምክንያት፣ እውነተኛ ከሆነው እናት ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠው የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም መናፍቃን ከቀዳሚቱን እምነት ወግድ ብለው የወጡ ሰዎች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እኛ እየተነጋገርን ያለነው ከክርስትና እምነት የወጡ መናፍቃንን ለማመልከት ቢሆንም፣ በሌሎች ሃይማኖቶችም ውስጥ ኑፋቄ ይከሠታል፡፡ ለምሳሌ:— በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ሱፊዎችና ጥቊር ሙስሊሞች (የእስልምና ሕዝቦች “Nation of Islam” በመባል ይታወቃሉ) የእስልምና ሃይማኖት መናቃን በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ወይም ኅብረቶች ራሳቸውን ሙስሊም እያሉ ቢጠሩም እንኳ፣ ከመሠረታዊው የእስልምና አስተምህሮ የራቁ ናቸው፡፡
“ከክርስትና እምነት የወጡ መናቃን” የሚለውን ሐረግ የተጠቀምንበት ዋነኛ ምክንያት፣ ብዙ ሰዎች መናፍቃን የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት እንደ እስልምና ወይም የባሃኢ እምነት ወዘተ ያሉትን ሃይማኖቶች በሚያመለክት መልኩ ስለሆነ እንዲሁም፣ የክርስትና እምነት መናቃን የሚለው ሐረግ፣ በክርስትናና በመናፍቃን መካከል ጒልሕ የሆነ ልዩነት መኖሩ ለማመልከት ነው፡፡
- “…ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ…”
መናፍቃንን መናፍቃን ከሚያሳኛቸው መስፈርቶች ውስጥ፣ “ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ” የሚለው ሐረግ አንደኛው ነው፡፡ ምንም እንኳ እስልምና ከክርስትና ጋር የሚቃረን እጅግ በርካታ ትምህርት ቢኖረውም፣ እስልምና ራሱን ክርስቲያን ብሎ ስለማይጠራ፣ በመናፍቃን ጐራ ሊፈረጅ አይችልም፡፡ እስልምና ራሱን የቻለ፣ ከክርስትና እምነት ጋር የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ የዓለማችን ሃይማኖት ነው፡፡ ስለዚህ እስልምናን እስልምና እንጂ፣ ክርስቲያናዊ ኑፋቄ አንለውም፡፡
“የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን”፣ “የይሖዋ ምስክሮችን”፣ “የእምነት እንቅስቃሴን”፣ “ሞርሞናችን” ግን፣ ከክርስትና እምነት የወጡ መናፍቃን ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፤ ምክንያቱም ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ስለሚጠሩ፡፡
ወንጌልን የሚቃወም ማንኛውም ሥርዐተ እምነትና ንጽሮተ ዓለም፣ ሰዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ራሱን የገለጠውን አምላክ፣ በትክክል እንዳያውቁ ስለሚያደርግ ስሕተት ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን ነን እያሉ መሠረታውያኑን የክርስትና እምነት የሚቃወሙትን ብቻ መናፍቃን እንላቸዋለን፡፡
- “…በመሪዎቻቸው ወይም በድርጅታቸው የተሰጠውን የተወሰነ አስተምህሮአዊ ሥርዐት የሚከተሉ…”
አንዳንድ መናፍቃዊ ድርጅቶችና እንቅስቃሴዎች (ለምሳሌ:— የእምነት እንቅስቃሴ፣ የእግዚአብሔር ልጆች፣ የዩኒፊኬሽን ቤተ ክርስቲያን) የተወሰኑ ነቢያቶቻቸውን፣ “ባለ ሥልጣን ነቢያት” በማለት የእውነት ምንጭ አድርገው ይቀበሏቸዋል፡፡
አንዳንድ የመናፍቃን ድርጅቶች ደግሞ እውነትን የማግኘትና ሰዎችን በእውነት የመምራት ሥልጣን፣ የድርጅቶቹ ብቻ እንደ ሆነ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ:— “የይሖዋ ምስክሮች” የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር በመባል የሚታወቀውን ድርጅታቸውን የሚመሩ የአመራር አካላትን፣ “ልባምና ታማኝ ባሪያ” በመባል ይጠሯቸዋል፡፡ ይህ ቡድን፣ ወቅታዊ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ ከአምላክ በቀጥታ ያወርዳል ተብሎ ስለሚታመን፣ የድርጅቱ ተከታዮች ለድርጅቱ አመራር አካላት ትምህርት፣ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲገዙ ይጠበቃል፡፡
- “…ይህም አስተምህሮአዊ ሥርዐት ከሥልሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍት የተቀዳውን…”
ክርስቲያናዊ ትምህርት መመሥረት ያለበት፣ የእግዚአብሔር ሥልጣናዊ ቃል በሆኑት፣ በሥልሳ ስድስቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ መናቃን በእነዚህ መጻሕፍት ላይ መጻሕፍትን ይጨምራሉ፡፡ ይህ ዐይነቱ ጭማሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ በቂ አንዳልሆነ ወይም የእነርሱ መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚተካ ከማሳየቱ ባሻገር፣ እነዚህ ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አቻ ተደርገው እንደ ተወሰዱ አመልካች ነው፡፡ ነገር ግን የእነዚህ መጻሕፍት ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ ይቃረናል፡፡
- “…የክርስትና እምነት መሠረታዊ አስተምህሮ አንድ ወይም ከአንድ በላይ ትምህርት የሚክዱትን…”
የክርስትና እምነት መሠረታዊ (ዐበይት) አስተምህሮዎች የሚባሉት፣ ክርስትናን ክርስትና የሚያሰኙት ትምህርቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዋልተር ማርቲን “ኑፋቄ ማለት፣ ርቱዕ ከሆነው የክርስትና ትምህርት ዐበይት ትምህርቶችን የሚክድ ማለት ነው” የሚለው፡፡ መሠረታዊ የሚባሉት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች የክርስትና ጽኑ አዕማድ ናቸው፡፡ እነዚህም አስተምህሮዎች ትምህርተ ሥላሴ፣ የክርስቶስ ፍጹም አምላክ እንዲሁም ፍጹም ሰው መሆኑ፣ ክርስቶስ በአካል ሥጋ ከሙታን እንደ መነሣቱ፣ አማኞችም በዚሁ መልክ በአካለ ሥጋ ከሙታን የሚነሡ መሆናቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የፈጸመው የድነት ሥራ መሆኑ፣ ድነትን በጸጋና በእምነት በኲል ብቻ መገኘቱን ወዘተ የክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች ወይም የክርስትና ማዕከል ናቸው፡፡
ከእነዚህም መሠረተ እምነቶች ማፈንገጥ፣ ኑፋቄ ነው፤ ፍጹም ውጉዝ ነው፡፡ እነዚህ አስተምህሮዎች ክርስትና ያረፈበት ታሪካዊ ዐለት መሆናቸውን፣ ቃል እግዚአብሔር ራሱ በግልጽ ይመሰግርልናል (ማቴ. 28÷19፤ ዮሐ. 8÷24፤ 1ቆሮ. 15፤ ኤፌ. 2÷8-10)፡፡ እነዚህን መሠረታውያን ትምህርቶች ክዶ፣ ክርስቲያን ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ከክርስትና አንጻር የዘላለም ሕይወት አገኛለሁ ማለት በጭራሽ አይቻልም፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች መሠረታዊ የሆነውን ክርስቲያናዊ ትምህርት፣ ደቂቃን (ንዑሳን) ከሆኑ ትምህርቶች ጋር በአንድ ይቀይጣሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው፡፡ ለምሳሌ:— አንድ ሰው 1ጴጥሮስ 3÷19 መሠረት አድርጎ፣ “በወኅኒ የነበሩ ነፍሳት” ማን እንደ ሆኑ በሚሰጠው ገለጻ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ወይም ምን ማለት እንደ ሆነ በግልጽ ላይረዳ ይችላል፡፡ ወይም ንጥቀት አለ ወይስ የለም በሚለው ጒዳይ ላይ የተለያየ አስተያየት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ ግን ትልቅ የሚባል ስሕተት አይደለም፡፡ ግለሰቡ ይህን ባለማወቁ ከዘላለም ሕይወት ሊጐድል አይችልም፡፡
ነገር ግን አንድ ሰው ድነት በጸጋ መሆኑን ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ከካደ ግን፣ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ምንፍቅና ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ጽንታ ከቆመችበት መሠረተት እምነት አፈንግጦአልና፡፡
መሠረታዊ በሆኑ ክርስቲያዊ ትምህርቶች ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ፕሮቴስታንቶች (የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት) አንድ ዐይነት አቋም አላቸው ባይ ነኝ፡፡ ምናልባት እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸውን መሠረተ እምነት፣ አማኒያኑ በግልጽ ሳይረዱ ቀርተው ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲረዱት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ እነዚህን ክርስቲያናዊ ቤተ እምነቶች እንደ መናፍቅ መቊጠር፣ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እርስ በርስ መነቃቀፋቸው፣ አንዱ ሌላውን እንደ መናፍቅ መቊጠሩ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡
መሠረታዊ ከሆኑት የክርስትና አስተምህሮዎች አንዱን እንኳ መካድ፣ በመናፍቃን ጐራ ለማስፈረጅ በቂ ነው፡፡ አብዛኞቹ መናፍቃን ግን መሠረታዊ ከሆነው የክርስትና ትምህርት አንድና ከአንድ በላይ ትምህርት የሚያጐድሉ (የሚያገድፉ) ናቸው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት፣ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች፣ እርስ በርስ የተጠላለፉ (እርስ በርስ የሚሰናሰኑ፣ እርስ በርስ የተቈራኙ) በመሆናቸው ነው፡፡
[1] D.A. Cardon, “A text without a context is pretext for a prooftext.”
[2] የሰዎችን ሙግት ወይም ትምህርት በተሳሳተ መንገድ አጣሞ በማቅረብ (በመተርጐም) ሙግትን ማደራጀት (ወይም አጸፋ መዘንዘር)፣ በሥነ አመክንዮ ትምህርት፣ “ቊልምምተ ወገራ” (Straw Man Fallacy) በመባል ይጠራል፡፡ ይህንና ይህን መሰል ስሑት ሙግቶች ዐይነታቸውንና ጠባያቸውን ለማወቅ፣ የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “ሥነ አመክንዮ፤ የሙግት አደረጃጀት አገማገምና አሰናዘር” በሚል ርእስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ይመለከቷል፡፡
[3] ለምሳሌ ትልቁ ፈላስፋ አፍላጦን የሚለውን እነሆ:— “[N]o one is able to persuade me that the correctness of names is determined by anything besides convention…No name belings to a particular thing by nature, but only because of the rules and usages of those who establish the usage and call it by that name.” (Plato, Craylus, 384c-d).
[4] በዚህ ዐውድ የዐማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች
[5] በሕግ መዛግብት (ሰነዶች) ውስጥ፣ ዐበይት የሆኑ ቃላትን እንዲህና እንዲያ ብሎ በመበየን ልማድ አለ፡፡ እንዲያውም ጊዜያት እየተራዘሙ ሲሄዱ ቃላት ትርጒማቸውን የመቀየር ጠባይ ስላላቸው፣ ለአሻሚ ቃላቱ ትርጒም የበጨረሻ ብያኔ የሚሰጠው አካል ማን እንደ ሆነ፣ በሕግ ሰነዱ ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ በሥነ አመክንዮና በሒሳብ ትምህርት፣ “x, y, z…” የሚሉ የተለያዩ “variables” ግልጋሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ስምምነቱ በግልጽ እስከ ተቀመጠ ድረስ፣ ይህን ማድረግ አይከለከልም፤ እንዲያውም ተግባቦቱን ይበልጥ ግልጽ ፍለጋውንም ቀሊል ስለሚያደርግ፣ ይበረታታል እንጂ፡፡
[6] አንድ ሦስተኛ (1/3)፡፡
[7] አንድ አራተኛ (1/4)፡፡
[8] የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “ሆህያተ ጥበብ” በሚል ርእስ ባዘጋጀው መጽሐፍ፣ ይህን ዐሳብ በስፋት ለመሞገት ሙከራ አድርጓል፡፡
[9] ተርጓሚ ተባዕታይ ነጠላ ሲሆን፣ ተርጓሚት ደግሞ አንስታይ ነጠላ ነው፡፡ ተርጓምያን ተባዕታይ ብዙ፣ ተርጓምያት አንስታይ ብዙ ነው፡፡
[10] ፈካሪ፣ ፈካሪት፣ ፈካርያን፣ ፈካርያት፡፡ እሙር፣ እሙራን፣ እሙራት፣ እምርት፡፡
[11] አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ ገጽ 722፡፡
[12] መጋቢ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ እንየው፡፡
[13] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 228፡፡
[14] “denotation” የቃሉ ቊማዊ ትርጒም ሲሆን፣ “cannotation” ደግሞ ቃሉ መቋንቋው ባለቤቶች ዘንድ ያለውን አሉታዊና አዎንታዊ እንድምታ አመልካች ነው፡፡ ለምሳሌ:— “ጦጣ” የዱር እንስሳን አመልካች ቃል ሲሆን፣ በዐማርኛ ብልጠትን ለማሳየት ግልጋሎ ላይ ይውላል፡፡
“ጌታ ፍቅሩ ብሶበታል” የሚል ዝማሬ ማኅሌት የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ “ብሶበታል” የሚለው ቃል አሉታዊ ለሆኑ ነገሮች እንጂ፣ “ፍቅርን ለሚያህል” አዎንታዊ ነገር አያገለግልም፡፡ ባሰበት፣ ጠናበት፣ በረታበት የሚባለው፣ አሉታዊ ለሆነ ነገር (ለምሳሌ ለበሽታ፣ ለችግር) የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ ቃላት ቊማዊ ትርጒማቸውን (denotation) ከአንድምታዊ ትርጒማቸው (cannotation) ጋር ሳያመሳክሩ፣ መጠቀም የሚያስከትለው ችግር ነው፡፡
[15] “ዐቃቢት” ነጠላ አንስታይ፣ “ዐቃብያት” አንስታይ ብዙ ነው፡፡ “ዐቃቢ” ነጠላ ተባእት፣ “ዐቃብያን” ተባእታይ ብዙ ነው፡፡
[16] አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ (ገጽ 704-705)፡፡ እንዲሁም ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ (ገጽ 950)፡፡
[17] አለቃ ኪዳ ወልድ ክፍሌ፤ (ገጽ 704)፡፡
[18] ዝኒ ከማሁ፤ (ገጽ 705)፡፡
[19] እንግዲያው ፋርማሲስቶችን ዐቃቤ ሥራይ በሏቸው፡፡
[20] ዝኒ ከማሁ፤ 705፡፡
[21] በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ “ዐቃቤ እምነት” (ለብዙ ቊጥር፣ “ዐቃብያነ እምነት”) ከሚለው ቃል ጋር አቻ ትርጒም ያለው ቃል እንዳለ፣ ትልቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ፣ አቶ እጅጉ ረታ ይገልጻሉ፡፡ ይኸውም፣ “ቀዋሚ ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ነው፡፡ ይህ ቃል በቀደምት የቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ውስጥ ግልጋሎት ላይ ይውል እንደ ነበር ያስረዳሉ፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “ቀዋሚ” (ቀዋሚት፤ ቀዋምያን፤ ቃዋምያት) የሚለው ቃል ትርጒሙ፣ “የሚቆም፤ ቋሚ፤ ጸንቶ የሚኖር”፤ ማለት እንደ ሆነ እንዲሁም፣ “ቀዋሚ” “ጠበቃ፤ የነገር አባት፤ መጋቢ ሹም” የሚል ትርጒም እንደሚጨምር ይገልጻሉ (ገጽ 785)፡፡ ስለዚህ ለክርስትና ጥብቅና የሚቈሙ የሙያው ባለቤቶች፣ “ዐቃብያነ እምነት” እንዲሁም፣ “ቀዋምያነ ቤተ ክርስቲያን” ለሙያው ደግሞ፣ “ዕቅበተ እምነት” ወይም “ዐቀብተ እምነት” የሚለውን ቃል ልንጠቀም እንችላለን፡፡
[22] አንዳንድ ኢትዮጵያውያን፣ “apologetics” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል፣ “ምካቴ እምነት” ብለው ተርጒመውታል፡፡ ነባሩ ትርጒም የግሪኩን ቃል፣ “ወንጌልን መመከት” ብሎታል፡፡ ጥሬ ቃሉ በዚህ መንገድ መተርጐሙ፣ ለሙያዊ ግልጋሎት የዋለው ቃል በዚህ መንገድ እንዲቀመር ምክንያት የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ምካቴ እምነት የሚለው ስያሜ አስተምህሮውን በትክክል የሚወክል አይደለም፡፡ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” እንዳሆን፡፡ በስፋት እየተሠራበት ያለው ዕቅበተ እምነት የሚለው ቃል፣ የጥናቱን ዘርፍ በትክክል የሚወክለው ከሆነ፣ ዐዲስ ቃል መቀመሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የዕቅበተ እምነት የጥናት ዘርፍ፣ የክርስትናን አስተምህሮ ከጥቃት መመከት ብቻ ሳይሆን፣ ከክርስትና ጋር የሚጻረሩ ከንቱ ምልከታዎችንም (አጸፋ መሰንዘር)፣ የጥናቱ ሌላው ክፍል ነው፡፡ ዕቅበተ እምነት በሁለት ገጽ (በወዲያና በወዲህ) የተሳለ ሰይፍ ነው፤ ሲሄም ሆነ ሲመለስ ይቈርጣል፡፡ የምካቴው ወገን፣ አሉታዊ ዕቅብተ እምነት፣ በእንግሊዝኛው “negative apologetics” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የማጥቃቱ ወገን ደግሞ፣ አዎንታዊ ዕቅበተ እምነት “positive apologetics” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ አንጻር ሲታይ፣ “ምካቴ እምነት” የሚለው ቃል፣ ዐሳቡን በግማሽ እንጂ፣ ሙሉ በሙሉ አመልካች አይደለም፡፡
“ዕቅበተ እምነት” የሚለው ቃል ግን፣ “ምካቴ እምነት” ከሚለው በብዙ ረገድ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም ዐቀበ የሚለው ቃል፣ አሉታዊውንም ሆነ አዎንታዊውን ግብር፣ የመወከል ዐቅም አለውና፡፡ በዚህ አንጻር፣ “ዐቀበ” የሚለው ቃል ምን ያህል ባለጸጋ እንደ ሆነ እዩልኝሳ:— “ዐቀበ፤ የሚጠብቅ፣ ጠባቂ፣ ተመልካች፣ ከልካይ … ጠንቅቆ ማየት፣ መመልከት፣ መጐብኘት፣ ማቆየት፣ ማዘግየት፣ መመልከት … አስጠበቀ፣ ዘበኛ አቆመ፣ ዐደራ ሰጠ”፡፡ ተገብሮ/ተደራጊ ግሥ ሲሆን ደግሞ፣ “አዕቀበ፤ አስጠበቀ፣ ዘበኛ አቆመ…ተጠነቀቀ” (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ ገጽ 703-704 ይመለከቷል)፡፡ ጥንታውያኑም ሊቃውንት ይህንኑ ቃል እንደሚጠቀሙ ልብ ይሏል፡፡ “ካህናት ዐቃብያነ ሕጉ ለእግዚ”፡፡
[23] አንዳንድ የግእዝ ቋንቋ ምሁራን፣ “ዕቅበተ እምነት” ከሚለው ስያሜ ይልቅ፣ “ዐቀብተ እምነት” የሚለው ቃል የተሻለ ነው፣ የሚል ዐሳብ አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ በግእዝ ቋንቋ ዐዋቂዎች ዘንድ የተወሰነ ክርክር አለ፡፡ እኛም በአንዳንድ ጽሑፎች ውስጥ ይህን ስያሜ መጠቀማችንን ልብ ይሏል፡፡ በዐጭሩ፣ “ዕቅበተ እምነት” ወይም፣ “ዐቀብተ እምነት” የሚለው ቃል፣ የሙያው መጠሪያ ነው ማለት ነው፡፡
[24] ቋንቋ ብዙ አፈንጋጭ ነገሮች አሉት፡፡ በዚህ ቦታ አፈንጋጭ ነገሮች የሉም ቢባል ማለት ነው፡፡
[25] James Swanson, Dictionary of Biblical Languages With Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
[26] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 18፡፡
[27] ዘመናዊው ዓለም ይህን መረጃ ያገኘው ከሦስት ምንጮች ነው፡፡ ከተማሪው ከአፍላጦን (Plato) እና ከሲኖፎን (Xenophon) ጽሑፎች፣ እንዲሁም ከጸሓፊ ተውኔት ከአርስቶፋነስ (Aristophanes) ለቲያት ባዘጋጀው ጸሑፍ ላይ ነው፡፡ Aristophanes, Clouds (Johnston, Ian, translator, Vancouver Island University, 2008). Xenophon, The Memorabilia: Recollections of Socrates, (Trans, Dakyns, Henry Graham, 1890-1909. Project Gutenberg, 2013). Plato, Apology (Trans: Jowett, Benjamin. Project Gutenberg, 2013).
[28] ይኸውም:— (1) የግሪካውያን ባህላዊ ሃይማኖት አልተቀበልህም፤ (2) የጀማው ጉባኤ አባል እንደ መሆንህ መጠን፣ ከሕዝቡ ፈቃድ ውጪ የሆነን ነገር አድርገሃል፤ (3) የምርጫን ዲሞክራሲያዊነት ተችተሃል፤ (4) በራስህ አስተሳሰብ ወጣቶችን ቀርጸሃል፡፡
[29] ዓለም ምርጥ ልጆችዋን በሞት ቀጥታለች፡፡ የሶቅራጥስን፣ ክርስቶስን ሐዋርያት እንዲሁ የክርስቶስን ሞት በአብነት ይመለከቷል፡፡
[30] “664 ἀπολογέομαι (apologeomai): vb.; ≡ Str 626—LN 33.435 defend oneself, speak a defense in one’s own behalf (Lk 12:11; 21:14; Ac 19:33; 24:10; 25:8; 26:1, 2, 24; Ro 2:15; 2Co 12:19+; Mk 16:15 v.r.). 665 ἀπολογία (apologia), ας (as), ἡ (hē): n.fem.; ≡ Str 627—1. LN 33.435 defend oneself, make a formal justification (Ac 25:16; 2Co 7:11; Php 1:7, 16; 2Ti 4:16; 1Pe 3:15+); 2. LN 33.436 defense, the content of the answer or reply (Ac 22:1; 1Co 9:3), note: these verses and entries may overlap. 666 ἀπολούω (apolouō): vb.; ≡ Str 628; TDNT 4.295—LN 88.30 make pure, formally, wash away (Ac 22:16; 1Co 6:11+)” James Swanson, Dictionary of Biblical Languages With Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
[31] ዐዲሱ መደበኛ ትርጒም የተጠቀምን ሲሆን፣ ሰዋስዋዊ ትንታውን በተመለከተ፣ የሚከተለውን የግሪክ መዝገበ ቃል ተከትለናል:— James Swanson, Dictionary of Biblical Languages With Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
[32] noun, genitive, singular, feminine.
[33] noun, accusative, singular, feminine.
[34] noun, dative, singular, feminine.
[35] noun, accusative, singular, feminine.
[36] noun, dative, singular, feminine.
[37] noun, accusative, singular, feminine.
[38] noun, genitive, singular, feminine.
[39] noun, nominative, singular, feminine.
[40] 1993 ትርጒም በመባልም ይታወቃል፡፡
[41] “ነባሩ ትርጒም” ወይም “1954 ትርጒም” ወይም ደግሞ፣ “ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ትርጒም” ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ መጽሐፍ፣ “ነባሩ ትጒም” የሚለውን ስያሜ ተከትለናል፡፡
[42] “ቊም ትርጒም” ወይም፣ “አባ ሮሚዮ ትርጒም” በመባልም ይጠራል፡፡
[43] “በቀላል ዐማርኛ” በመበልም ይጠራል፡፡
[44] ይህን ትርጒም ለነገረ መለኮት ጥናት መጠቀም ያስቸግራል፤ የትርጒሙ ቀዳማይ ዐላማ የክፍሉን ዐቢይ ዐሳብ በቀላል ዐማርኛ ለተደራስያኑ ማቅረብ ነውና፡፡
[45] Kenneth Boa and Robert Bowman, Faith Has Its Reasons: An Integrative Approach to Defending Christianity, 2nd ed. (Colorado Springs, CO: NavPress, 2015), 2.
[46] Kenneth D. Boa and Robert M. Mowman, Faith Has Its Reasons: An Integrative Approach to Defending Christianity, second ed. (Georgia, Waynesboro: Paternoster, 2005), 1-4.
[47] ዝኒ ከማሁ፡፡
[48] የኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ (ገጽ 645-646)፡፡
[49] ዝኒ ከማሁ፡፡
[50] ዝኒ ከማሁ፡፡
[51] Alan W. Gomes, Unmasking the Cults (Grand Rapids: Zondervan, 1995), ገጽ 9፡፡ ከCharlton T. Lewis and Charles Short, A Latin Dictionary (Oxford: Oxford University Press, 1879; impression of 1984), s.v. “colo,” 370. ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡
[52] ዝኒ ከማሁ፡፡
[53] ከላይ “ቃላት ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ ይሞታሉ” የሚለው አባባል በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ እውነትነቱ ጐልቶ ይወጣል፡፡ በዚሁ አግባብ ቃሉ፣ ተጨማሪ የትርጒም ቅርንጫፍ አብቅሎ ይሆናል፡፡
[54] αἵρεσις (hairesis), έσεως (eseōs), ἡ (hē): n.fem.; ≡ Str 139; TDNT 1.180—1. LN 11.50 religious party, sect (Ac 5:17; 15:5; 24:5, 14; 26:5; 28:22+); 2. LN 33.241 false teaching, heresy (2Pe 2:1+); 3. LN 63.27 division, faction, separate group (1Co 11:19; Gal 5:20+), note: some of these entries and verses may overlap. James Swanson, Dictionary of Biblical Languages With Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
[55] Robert M. Bowman, Jr., Orthodox and Heresy: A Biblical Guide to Doctrinal Discernment (Grand Rapids: Baker, 1992), 49.
[56] Alan W. Gomes, Unmasking the Cults (Grand Rapids: Zondervan, 1995), ገጽ 14፡፡ ከGeorge A. Mather and Larry A. Nichols, Dictionary of Cults, Sects, Religions and the Occult (Grand Rapis: Zondervan, 1993), 212 ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡
[57] ዝኒ ከማሁ፡፡
[58] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 14፡፡ ከAmerican Heritage Dictionary, Second Collage Edition (Boston: Houghton Mifflin, 1985), 1108 ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡
[59] ዝኒ ከማሁ፡፡
[60] አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ ገጽ 840፡፡
[61] evaluative term
[62] positive cannotation
[63] አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ (ገጽ 620)፡፡
[64] እርባታው እንደሚከተለው ነው—አንስታይ ነጠላ፣ “ነባዪት”፣ ተባዕት ብዙ “ነባይያን”፣ አንስታይ ብዙ፣ “ነባያት”፡፡
[65] “በቊሙ” ማለት በቀጥታ ትርጒሙ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው፣ “literal” የምንለውን ይጐዳኛል፡፡
[66] ዝኒ ከማሁ፡፡
[67] አንስታይ ነጠላ፣ “ነቢያዊት”፣ ተባዕታይ ብዙ፣ “ነቢያውያን” አንስታይ ብዙ፣ “ነቢያት”፡፡
[68] ዝኒ ከማሁ፡፡
[69] አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ ዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የካቲት 1993፤ ገጽ 280፡፡
[70] ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 832፡፡ ደስታ ተክለ ወልድና ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነባይ መሠረቱ ዐማርኛ ነው ወይስ ግእዝ በሚለው ጒዳይ ላይ ልዩነት ያላቸው ይመስላል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ፣ በቊርጥ ሥሪቱ ግእዝ ነው ባይሉም፣ ርባታውን ያዘጋጁት የግእዝን አካሄድ ተከትለው ነው፡፡ ደስታ ተክለ ወልድ ግን በግልጽ፣ “ነባይ ዐማርኛ፤ ነቢይ ግእዝ ነው” ብለውናል፡፡
[71] ዝኒ ከማሁ፡፡
[72] ዝኒ ከማሁ፡፡
[73] δόξα (doxa), ης (ēs), ἡ (hē): n.fem.; ≡ DBLHebr 3883; Str 1391; TDNT 2.233—1. LN 79.18 splendor, glory (1Pe 1:24); 2. LN 14.49 brightness, shining, radiance (Ac 22:11; Rev 15:8); 3. LN 76.13 amazing might, demonstration of power (Ro 6:4); 4. LN 33.357 praise, speak words of honor and glory (Lk 17:18; Jn 9:24); 5. LN 87.4 honor, give an assignment of status (Lk 14:10); 6. LN 87.23 greatness, the state of being wonderful (Mt 4:8; 12:27); 7. LN 12.49 glorious being, benevolent supernatural power (2Pe 2:10); 8. LN 1.15 heaven, a glorious place (1Ti 3:16); 9. LN 25.205 pride, the reason or basis for legitimate pride (1Th 2:20); 10. LN 33.468 δίδωμι δόξαν τῷ θεῷ (didōmi doxan tō theō), promise to tell truth, formally, give glory to God (Jn 9:24+), for another interp, see “praise”; 11. LN 12.6 μεγαλοπρεπὴς δόξα (megaloprepēs doxa), the Sublime Glory, the Majestic Glory (2Pe 1:17+). James Swanson, Dictionary of Biblical Languages With Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
[74] “οὗτός μου θεός καὶ δοξάσω αὐτόν”
[75] “διότι γνόντες τὸν θεὸν οὐχ ὡς θεὸν ἐδόξασαν”
[76] “ὅτι Ἰησοῦς οὐδέπω ἐδοξάσθη”
[77] Alan W. Gomes, Unmasking the Cults (Grand Rapids: Zondervan, 1995), ገጽ 7፡፡
[78] የነገረ መለኮት ትንተናው የተወሰደው፣ Alan W. Gomes, Unmasking the Cults (Grand Rapids: Zondervan, 1995), ገጽ 9-11 ላይ ነው፡፡

