ዐሥራ ሰባት ዓመት፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን”ባሪያ ነበርሁ

የመጋቢ ንጉሤ ኀይሌ የሕይወት ምስክርነት

ወደ እንቅስቃሴው መግባት

በዚያን ጊዜ እንቅስቃሴው፣ “የተባበሩት ጴንጤቈስጣውያን” በመባል ነበር የሚጠራው፡፡ “የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ስያሜ የመጣው ኋላ ነው፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር የነበረኝ ግንኙነት የጀመረው ድንገት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ጌታ የመጣሁት በ1963 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ አንድ ቀን ጓደኛዬ ወደ አንድ ስፍራ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይህ ሰው ከእኔ ቀደም ብሎ ጌታን ያውቅ ስለነበር፣ እንደ መንፈሳዊ አባት እንዲሁም እንደ ታላቅ ወንድም የምመለከተው ሰው ነበር፡፡ ከቄስ ተክሌ ጋር ረዘም ያለ ውይይት አደረጉ፡፡ (በዚያን ጊዜ ቄስ ተክሌ፣ ቄስ ሳይሆን ወንጌላዊ ነበር)፡፡ ውይይታቸው ረዥም ሰዓት የፈጀ ነበር፡፡ እኔ ግን በሚወያዩበት ርእሰ ጒዳይ ላይ ምንም ዐይነት ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ ከዚያ በፊትም ከቄስ ተክሌ ጋር ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ከውይይታቸው ዐልፎ ዐልፎ የተረዳሁት ግን፣ ውይይታቸው በትምህርተ ሥላሴ ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደ ነበር ነው፡፡

ይህ፣ እኔ ጌታን አግኝቼ ወይም ደግሞ ጌታ እኔን አግኝቶኝ ሕይወቴ በእግዚአብሔር ፍቅር እየተቀጣጠለ ያለበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ በነበርሁበት አካባቢ በክርስትናዬ ምክንያት ስደት አጋጥሞኝ፣ ከሥራም ሁሉ የተባረርሁበት ወቅት ነበር፡፡ ቢሆንም በእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር ውስጥ የነበርሁበት ወቅት ስለነበር፣ ችግሩ ብዙም አልተሰማኝም፤ አላሳሰበኝም፡፡ በመጨረሻ ባልንጀራዬ የነበረው ሰውና ወንጌላዊ ተክሌ በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፡፡ ሊያጠምቀውም ወደ አንድ ወንዝ ይዞት ሄደ፤ አጠመቀውም፡፡

ባልንጀራዬ በኢየሱስ ስም ተጠምቆ ሲመለስ፣ አንተስ ለምን አትጠመቅም የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ እኔ ስለ ጥምቀት የማውቀው አንዳች ነገር የለም፡፡ ጥምቀት ራሱ ይኑር አይኑር እንዲሁም መጠመቅ አስፈላጊ ጒዳይ ይሁን የማያስፈልግ፣ አንዳች የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ በአንጻሩ ግን ለጓደኛዬ ትልቅ ከበሬታ ስለነበረኝ፣ የእግዚአብሔርም ቃል ዕውቀት በሙላት አለው ብዬ የምገምተው ሰው ስለነበር፣ እርሱ ያደረገው ነገር ሁሉ ጥሩ ነው በሚል ዐስተሳሰብ፣ ተጠመቅ የሚለውን ግብዣ ተቀበልሁ፤ ቄስ ተክሌም አጠመቀኝ፡፡

ችግር ውስጥ እንደገባሁ የተረዳሁት ግን በነጋታው ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች የጓደኛዬንና የእኔን ስም በመጥራት “ኦንሊ ጂሰስ (Only Jesus) ሆነዋል፤ ሥላሴን ክደዋል”፤ የሚል ወሬ በስፋት ይወራ ጀመር፡፡ ቢሆንም ግን በቀጥታ መጥቶ ያነጋገረኝ ሰው አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመው ታዲያ በነጌሌ ቦረና ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ፣ ለሥራ ከሄድሁበት ከነጌሌ ቦረና ወደ ዐዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ዐዲስ አበባ ስመጣ የት አካባቢ ላይ እነርሱ የአምልኮ ስፍራ እንዳላቸው ተነግሮኝ ስለ ነበርና የዐዲስ አበባም ልጅ ስለነበርሁ፣ የሚያመልኩበትን አካባቢ አፈላልጎ ለመድረስ አላስቸገረኝም፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ አገኘኋቸው፡፡ ከጥምቀቱም በኋላም እንኳ በትምህርቱ ላይ፣ የጠለቀ ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በድርጅቱም ውስጥ ፍላጎት ኖሮኝ “እኔ ኦንሊ ጂሰስ ነኝ” በሚል ዐይነት መልክ የተመላለስሁበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

የአምልኮ ፕሮግራማቸውንም እካፈል ጀመር፡፡ በተጨማሪ በወቅቱ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን፣ በዐዲስ አበባ ናዝሬት ትምህርት ቤት አካባቢ ስለነበር፣ እዛም አዘውትሬ እሄድ ነበር፡፡ አብዝቼ የምሄደው፣ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ክፍል ስለነበራት፣ እኔ ደግሞ ቤቴ ውስጥ መጸለይ ስለማይመቸኝ፣ በየቀኑ ከሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አልለይም ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በቀን ውስጥ የተወሰነ ሰዓት በጸሎት አሳልፋለሁ፡፡ እዚም እዚያም ማለትም ሙሉ ወንጌልም ሆነ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን እያጣቀስሁ፣ ለተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡

ተክሌ ከሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን የወጣበት ዘመን ስለነበር፣ የእርሱ ጒዳይ በአብዛኞቹ የሙሉ ወንጌል ሰዎች ዘንድ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኖ ነበር፡፡ “እንዲህ እኮ ነው የሚለው”፤ “አይደለም እንደዚያ ነው የሚለው” ይባል ነበር፡፡ ነገር ግን የልዩነቱ ነጥብ ለእኔ ብዙም ግልጽ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ስለ ትምህርተ መለኮት የማውቀው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያው ጌታ አዳኝ መሆኑን ተረድቼ የመጣሁ ሰው ብቻ ነኝ፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሚሉት የትምህርተ መለኮት ጣጣ የማይገባኝ ርእሰ ጒዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ስሜት የሚሰጠኝም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ የመነጋገሪያ ርእስ የመሆኑ ጒዳይ፣ ቀስ በቀስ ነገሩ ምንድን ነው ብዬ እንድጠይቅ፣ ጒዳዩንም እንድመረምር ፍላጎት እያሳደረብኝ መጣ፡፡

በጊዜው ሚስተር ዊንድል የሚባሉ፣ “የተባበሩት ጴንጤቈስጣውያን”[1] ሚስዮናዊ ከነ ቤተሰቦቻቸው ዐዲስ አበባ ሲጃራ ፋብሪካ አካባቢ ይኖሩ ነበር፡፡ አንዳንድ ጽሑፎችን እንዲሰጡኝ ጠየቅኋቸው፤ በነበረችኝ ትንሽ የእንግሊዝኛ ችሎታ እየታገዝሁ የሰጡኝን መጽሐፍ እያነበብሁ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስቀመጧቸውን ጥቅሶች እያመሳከርሁ፣ ጒዳዩን ማጥናት ጀመርሁ፡፡ በተቃራኒው ግን የሥላሴ አስተምህሮ ምን ይመስላል የሚለውን ጥናት እንዳካሂድ የሚገፋፋኝም ሆነ፣ በርእሰ ጒዳዩ ላይ ጽሑፎችን የሚያቀብለኝ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህ በአንድ አቅጣጫ ብቻ፣ ያለ አንዳች ከልካይ የእነርሱን ትምህርት ብቻ ማስገባት ጀመርሁ፡፡ ቀስ በቀስም ከእነርሱ ጋር ያለኝ ኅብረት እየጠነከረ መጣ፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በወንጌል አገልግሎት እንዳገለግል ተጋበዝሁ፡፡ እኔም ደግሞ በልቤ ወንጌልን የማገልገል ትልቅ ሸክም ስለነበር፣ ያንን ጥሪ በደስታ በመቀበል ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ወንድም ጋር በመሆን ሰላሌ በሚገኝ አንድ ገጠር ውስጥ የድርጅቱን አስተምህሮ መስበክ ጀመርሁ፡፡ እንግዲህ በዚህ መልክ ነው ከድርጅቱ ጋር በመቀላቀል የድርጅቱ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ የሆንሁት፡፡

የእንቅስቃሴው አገልጋይ መሆን

አገልጋይ ከሆንሁ በኋላ ትምህርቱን ለሌሎች በስፋት ለማስረዳት እንዲሁም ለመስበክ፣ አስተምህሮአቸውን በትጋት ማጥናት ነበረብኝ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ቀስ በቀስ ትምህርቱን በወል እየተገነዘብሁ መጣሁ፡፡ በዚህ ጊዜ መተሐራና ወላይታ አካባቢ ለማገልገል የሄድሁባቸው ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በ1964 ዓ.ም ወላይታ አካባቢ ለአንድ ሳምንት ታስሬ ኋላ በዋስ ተለቅቄአለሁ፡፡

የመታሰሬ ዋነኛ ምክንያት፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ሰባኪ በመሆኔ ብቻ ሳይሆን፣ሙሉ ወንጌሎችን ጨምሮ የጴንጤቈስጤ አማንያን በሙሉ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ስደት ስለነበረባቸው እንዲሁም ሰባክያኑ እየታደኑ ይታሰሩ ስለነበር ነው፡፡ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ደግሞ በወቅቱ ትታወቅ የነበረው፣ “የተባበሩት ጴንጤቈስጣውያን” በሚለው ስም ስለነበር፣ የመሰደዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡ በዋስ ከተለቀቅሁ በኋላ፣ ፍርድ ቤት ሦስት ወር ፈረደብኝ፤ ነገር ግን እስራቱ በገንዘብ ስለተቀየረልኝ ገንዘብ ከፍዬ ልለቀቅ ቻልሁ፡፡ 

በእንቅስቃሴው ውስጥ የተፈጠረ እሰጣገባ

በ1964/65 ዓ.ም ላይ ተክለ ማርያም ዐዲስ ትምህርት ጀምሮ ነበር፡፡ ትምህርቱ የእሳት ጥምቀት የሚባል ሲሆን፣ ትምህርቱ ከምን ምንጭ እንደ መጣ ማንም አያውቅም፡፡ ኋላ ኋላ ግን ፍራንክሊን ሆል ከሚባለው ሐሰተኛ አስተማሪ የተገኘ ትምህርት መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ከዚህ የተነሣ በጊዜው ከነበሩት ሚስዮናውያን ጋር ችግር ተፈጠረ፡፡ እነሱም ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አይደለም ስለዚህ ተው አሉት፡፡ እርሱ ግን አሻፈረኝ በማለቱ ምክንያት ከሚስዮናውያኑ ጋር ተጋጨ፡፡ ቄስ ተክሌ በወቅቱ ያገለግል የነበረው በአዋሳ ነበር፡፡ በወቅቱ ያገለግሉ የነበሩት የድርጅቱ ሚስዮናውያን በመንግሥት ታውቀውና ተመዝግበው የገቡ ስለነበር፣ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤቶች ሁሉ ዕውቅና ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ቄስ ተክሌ በዐዲሱ ትምህርት ምክንያት ከድርጅቱ ተወግዞ ሳለ፣ ሚስዮናውያኑ በድርጅቱ ጸሎት ቤቶች ሁሉ ቄስ ተክሌ እንዳይሰብክ ዐገዱ፡፡ ቄስ ተክሌ ዕገዳውን አሻፈረኝ በማለቱ ምክንያት ሚስዮናውያኑ ጒዳዩን በወቅቱ ለነበሩት የአዋሳ ፖሊስ አዛዥ (ጀነራል ቀልቤሳ ይመስሉኛል) አመለከቱ፡፡ በዚህ ምክንያት ቄስ ተክሌና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ብዙ ተደበደቡ፤ ይሰብኩ የነበረበት ቤተ ክርስቲያንም እንዲዘጋ ተደረገ፡፡

ቄስ ተክሌ አልመለስም በማለቱ ምክንያት ተወገዘ፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ኅብረት ተወግዞ ተለየ፡፡ ነገሮች በዚህ መልኩ በመሄድ ላይ እንዳሉ፣ በ1966 ዓ.ም ደርግ መጣ፡፡ ደርግ የሚስዮናውያኑን ፈቃድ በመሰረዝ ሚስዮናውያኑ በፍጥነት አገር ለቅቀው እንዲሄዱ አስቸኳይ ትእዛዝ አወጣ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሚስዮናውያኑ በጊዜው ለነበርነው ሰዎች ኀላፊነቱን ሰጥተው ሄዱ፡፡ ቄስ ተክሌ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለሦስት ዓመት ታግዶ ቢቆይም፣ በወቅቱ ከነበርነው ሰዎች ሁሉ በፊት በእምነቱ አንጋፋ ስለሆነ፣ ከእኛ ለምን ይለያል በሚል ትምህርቱን በማስተካከል ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲያደርግ ግብዣ አቀረብንለት፡፡ ነገሩን እንዲሸመግሉም ሽማግሌዎችን ላክን፡፡ ከድርድሩም በኋላ ቄስ ተክሌ (ያን ጊዜ ወንጌላዊ ነበር) ዳግም ከድርጅቱ ጋር ኅብረት ማድረግ ጀመረ፡፡

በወቅቱ ሚስዮናውያኑ ኀላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ የሰጡት፣ ለቄስ አማረ ዋቅቶላ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የቄስ አማረ ሁለተኛ ሰው ሆኜ እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ቄስ ተክሌ በዕድሜም ሆነ በድርጅቱ አንጋፋ ስለነበር፣ የቤተ እምነቱ የበላይ ተጠሪ እንዲሆን ስለተስማማን ቦታው እንዲሰጠው ተደረገ፡፡ ቄስ አማረ (በዚያን ጊዜ ወንጌላዊ ነበር) የቄስ ተክሌ ምክትል ሆኖ የዐዲስ አበባ ዋና ተጠሪ በሚሆን ጊዜ፣ እኔ ደግሞ የቄስ አማረ ምክትል ሆኜ እንድሠራ ተወሰነ፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅስቃሴ፣ በዐዲስ አበባ፣ በወላይታ፣ በከንባታና በናዝሬት የተወሰነ ነበር፡፡ በወቅቱ ድርጅቱ ከእነዚህ ቦታዎች ውጪ አልተስፋፋም ነበር፡፡

ውሎ ሳያድር ቄስ ተክሌ ሌላ ዐዲስ ትምህርት ጀመረ፤ ይኸውም፣ “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የጠቀሳት ትምህርት ነች፡፡ ይኸውም፣ “አዳም ሲፈጠር መንፈስ ቅዱስ ነበረው” የሚል ትምህርት ነው፡፡ ይህን ትምህርት ከቀድሞ ከተወገዘበት ከፍራንክሊን ትምህርት ጋር በማቀናጀት ማስተማር ጀመረ፡፡ እኛም ማለትም ቄስ አማረ ዋቅቶላ፣ ቄስ ወርቁ ገብረ ማርያም፣ ቄስ አሸናፊ፣ ቄስ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሳይ፣ አቶ ሰሎሞን ሎዳሞና[2] እኔ (ከአቶ ሰሎሞን ሎዳሞ በስተቀር በዚያን ጊዜ እነዚህ ሁሉ ወንጌላውያን ነበሩ)፡፡ አዳም ሲፈጠር መንፈስ ቅዱስ ነበረው የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ስለማይገኝ፣ ትምህርቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ባዕድ ነው በሚል፣ ዳግም ከቄስ ተክሌ ጋር የነገረ መለኮት አንጃ ግራንጃ ተፈጠረ፡፡ ቄስ ተክሌ ደግሞ ይህን ትምህርት ደጋግሞ ከማስተማርም በላይ፣ በበራሪ ጽሑፍ አወጣ፡፡ ቀድሞ ትቼዋለሁ ያለውን የፍራንክሊን ሆልን ትምህርት ውስጥ ለውስጥ ማስተማርም ቀጠለ፡፡ ኋላ ግን የተሰጠውን ድርጅቱን የመምራት ኀላፊነት በመጠቀም፣ በኬንያ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና ኀላፊና የሚስዮናውያን ተወካይ ለሆኑት ለሚስተር ሔሪስ፣ “አገልግሎቴን እየተቃወሙ ነው” በማለት የተለያየ ደብዳቤ ይጽፍብን ጀመር፡፡

በዚህ ምክንያት በኬንያ የነበረው የሚስዮናውያን ተወካይ የነበረው ሚስተር ሔሪስ፣ ከኬንያ ወደ ዐዲስ አበባ መልእክተኛ በመላክ በጒዳዩ ላይ ስብሰባ እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ በመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ላይ ሁኔታዎች ጥሩ ስላልነበሩ፣ ለጊዜው ስብሰባው ከጸሎት ቤቱ ውጪ ቄስ ተክለ ማርያም ቤት እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ እርሱ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በደንብ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በተለይ ከወላይታና ከከንባታ አካባቢ እርሱ ወንጌላውያን ያላቸውን ሰዎች ለድጋፍ በብዛት አሰባስቦ ነበር፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስሁት እኛ ግን ስድስት ብቻ ነበርን፡፡ እኛም ቀድሞ ያስተምረው የነበረውንና ሚስዮናውያኑም ሆኑ እኛ ያወገዝነውን ትምህርት እንዳልተወ ገለጽን፡፡

በመጨረሻም ሚስዮናዊው ቄስ ተክሌ ደብዳቤውን በሚጽፍበት ወቅት፣ ደብዳቤውን እነርሱ ዘንድ ከመላኩ በፊት ለእኛ ማሳየት እንደ ነበረበት እንዲሁም የተወገዘበትን የቀድሞ ትምህርት ማስተማሩ ስሕተት እንደ ሆነ ይፋ አደረገ፡፡ ቄስ ተክሌ በዚህ መልኩ በመወገዙ ምክንያት ደጋፊዎቹን እርሱ በስብሰባው ቦታ ከፍተኛ ሁከት ፈጠሩ፡፡ በልሳን እየተናገሩ፣ “እናንተ ሰይጣኖች! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ውጡ” ብለው አዋከቡን፡፡ ቤቱም በከፍተኛ ሁከት ተሞላ፤ እኛም ቤቱን ጥለን ወጣን፡፡

ችግሩ እርሱ ዘንድ እንጂ እኛ ዘንድ እንዳልሆነ ታውቆአል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ እኛ እውነተኞች ሆነን ብንገኝም ከወጣን በኋላ፣ ከዩናይትድ ፔንቲኮስታል (United Pentecostal) ኅብረት እንድንለይ በድምፅ ብልጫ ተበየነብን፡፡ የሚስዮን ድርጅቱን ስናነጋግር ቄስ ተክሌ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስለሚያውቅ ለእኛ እርሱ ያስፈልገናል፡፡ ነገር ግን እናንተ ትክክል መሆናችሁን ደርሰንበታል ወደሚል ድምዳሜ ተደረሰ፡፡ እኛም “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ስያሜ መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ በዚህ ምክንያት ቄስ ተክሌ፣ “የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ስያሜ፣ እኛ (ማለትም ቄስ ወርቁ ገብረ ማርያም፣ ቄስ አሸናፊ፣ ቄስ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሳይ፣ ቄስ አማረ ዋቅቶላ፣ አቶ ሰሎሞን ሎዳሞ[3] እንዲሁም እኔ ደግሞ፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ስያሜ ለሁለት ተከፈልን፡፡

የእግዚአብሔር ምሪት

በዚህ መልኩ ጥቂት ዓመታት ዐብረን ከተጓዝን በኋላ፣ የቄስ ተክሌ ወገን ቄስ አሸናፊን ያዘ፡፡ እርሱ ደግሞ ከእኛ ጋር የነበሩ ጥቂት አማንያንን በመያዝ፣ ከእኛ በመገንጠል ከቄስ ተክሌ ኅብረት ጋር ተቀላቀለ፡፡ በዚህ መልኩ የእኛ ኅብረት እየተመናመነ መጣ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የቄስ ተክሌ ወገን፣ ቄስ ወርቁንና ቄስ ወልደጊዮርጊስን ያዘ፡፡ እነዚህም ሰዎች የተወሰኑ ሰዎችን ይዘው ከቄስ ተክሌ ኅብረት ጋር ተቀላቀሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔና ቄስ አማረ እንዲሁም ጥቂት ሰዎች ብቻ ቀረን፡፡ ሁኔታው ከዐቅማችን በላይ ስለሆነብን፣ ቄስ አማረ ሌላ ሥራ ፈልጎ ተቀጠረ፤ እኔም ሥራ ፈልጌ ገባሁ፡፡

በእግዚአብሔር አመራር ሂደት ውስጥ ነው እንግዲህ እኔ አሁን ወዳለሁበት ደረጃ ልመጣ የቻልሁት፡፡ ለጥቂት ጊዜ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ የካፍቴሪያ አስተዳዳሪ ሆኜ እሠራ ስለነበር፣ ወርልድ ቪዥን ደግሞ በወቅቱ የፋሲሊቲ አስተዳደር ይፈልጉ ስለነበር፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ያገኘሁትን ሰርተፊኬት በመጠቀም ወርልድ ቪዥን ተቀጠርሁ፡፡

ከዩናይትድ ፔንቲኮስታል ወይም “ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አስተምህሮ ጋር መለያየት የጀመርሁት በዚህ ታሪካዊ ቦታና በዚህ ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ እኔ ወርልድ ቪዥን የተቀጠርሁት በቀድሞ የትምህርተ መለኮት አቋሜ ነው፡፡ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ትምህርት ትክክለኛ ነው የሚል ጽኑ እምነትም ነበረኝ፡፡ ስለዚህ ነገሮች እስከሚስተካከሉ ጊዜ ድረስ እዚህ እሠራለሁ፤ ነገሮች ሲመቻቹ ግን ተመልሼ ወደ አገልግሎቴ እገባለሁ የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ በአጠቃላይ እሠራ የነበረው ለመኖር የሚያስፈልገኝን ነገር ለማግኘት ብቻ ነበር፡፡

ወርልድ ቪዥን ክርስቲያናዊ ድርጅት ስለሆነ፣ በነበርሁበት ፕሮጀክት በየቀኑ የጧት አምልኮ ፕሮግራም እንዲሁም በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የሰንበት አምልኮ እንዲሁም የማለዳ ጸሎት አለ፡፡ በዚያ ስፍራ የነበሩ ክርስቲያኖች የነበራቸው ሕይወት እጅግ በጣም የሚማርክ፣ ፈሪሓ እግዚአብሔር ያላቸው፣ እግዚአብሔርን ከልብ የሚወዱ፣ በአጠቃላይ የእኔን ሕይወት በአያሌው የሚማርክ ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች አስደናቂ ሕይወት ከፍተኛ ጥያቄ እየፈጠረብኝ መጣ፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች ድነት የላቸውም ማለት ነው? ካልዳኑ መንፈስ ቅዱስን እንዴት ሊሞሉ ቻሉ? ይህ ዐይነቱ ማራኪ ሕይወት እንዴት ሊኖራቸው ይችላል? ይህ ዐይነቱ ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ከሆነ ደግሞ ድነት ሳያገኙ ይህ እውን ሊሆን እንዴት ይችላል? በውኑ እነዚህን ሰዎች በኢየሱስ ስም ካልተጠመቃችሁ ድነት አላገኛችሁም ማለት ተገቢ ነው? የሚለው ጒዳይ ልቤንና አእምሮዬን ወጥሮ ያዘው፡፡

እነዚህ ሰዎች ከነበሯቸው ጽሑፎች ያላቸውን ያህል፣ እኔም ማንበብ የምችለውን ያህል ሰጥጠውኛል፡፡ ነገር ግን መሥሪያ ቤቱ በወቅቱ የዳበረ ቤተ መጻሕፍት አልነበረውም፡፡ በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ ጽሑፎች በራሪ ወረቀቶች እንዲሁም መለስተኛ ጥራዝ ያላቸው መጻሕፍት ብቻ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ያላቸውን፣ እኔም የምፈልገውን ያህል መረጃ ሰጥተውኛል፡፡

“ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” በነበርሁበት ጊዜ፣ “የሥላሴ ስም ጥምቀት የተጀመረው ከአንድ መቶ ዓመተ ምሕረት ማለትም ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ነው፤ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት በኢየሱስ ስም እንጂ በሥላሴ ስም አልነበረም፤ የሥላሴ ስም ጥምቀት የተጀመረው ከዚያ በኋላ ነው” የሚል ትምህርት ነበር፡፡ ለዚህ አስተሳሰብ በማስረጃነት የሚያቀርበውም የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፣ 8፣ 10፣ 19፣ 21 ላይ የምናገኘው የጥምቀት ቀመር በኢየሱስ ስም ነው፡፡ በሐዋርያቱ እግር ሥር ከተማሩት ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አበው ራሳቸው ሥርዐተ ጥምቀት ያካሂዱ የነበረው በኢየሱስ ስም ነበር ባዮች ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሥላሴ ስም ጥምቀት ቦታውን ያዘ ይባላል፡፡

በ1905 ዓ.ም አካባቢ በአሜሪካን አገር አዙሳ በተጀመረው የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ወቅት፣ “እግዚአብሔር ለአንድ ሰው በኢየሱስ ስም ጥምቀት ትክክለኛው የጥምቀት ቀመር እንደ ሆነ ገለጸለት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዳግም በኢየሱስ ስም ማጥመቅ ተጀመረ” የሚል ትምህርት አላቸው፡፡ ይህ ጒዳይ ጥያቄ ፈጠረብኝ፣ ይኸውም ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ፣ ቢያንስ ለአንድ ሺሕ ስምንት መቶ ዓመት፣ ሰዎች በኢየሱስ ስም ካልተጠመቁ በዚህ ጊዜ ሰዎች ድነት አያገኙም ነበር ማለት ነው? በእነዚህ አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ዓመታት ክርስቶስ አልተሰበከም ነበር ማለት ነው? በዚህ ወቅት እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር ትቶ ነበር ማለት ነው? በአጠቃላይ በእነዚህ ዘመናት ምን እየተካሄደ ነበር? እኔ እንኳ እስከማውቀው ድረስ በእነዚህ አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ዓመታት ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ስደቶች በተለያዩ ቦታዎች ተከሥተው እንደ ነበር፣ በርካታ ሰማዕታት ለእምነታቸውም ሆነ ለወንጌል የሕይወት መሥዋዕት እንደ ከፈሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም የተስፋፋችበት ዘመን እንደ ነበር ዐውቃለሁ፡፡ በምንም ሚዛን ቢታይ ወንጌል አልተሰበከም፣ ሰዎች ድነት አላገኙም ማለት በፍጹም አይቻልም፡፡ ታዲያ በእነዚህ ዘመናት የነበሩ ሰዎች እግዚአብሔር አያውቃቸውም ነበር ማለት ነው? ለከርስቶስ ሰማዕት የሆኑ ሰዎች ሁሉ ደማቸው የፈሰሰው በከንቱ ነበር ማለት ነው? የሚለው ጒዳይ ትልቅ ጥያቄ በውስጤ ፈጠረ፡፡ ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ አካሄድ የክርስቶስን ተልዕኮ መና የሚያስቀር ነውና፡፡ ጌታ ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ሲል፣ በእነዚህ ዓመታት ይህ እውን አልሆነም ነበር ማለት አይቻልም፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ዘመናት የነበሩ ሰዎች እንዲጠፉ በይኖባቸው ነበር ማለት የሚቻል አይደለም፡፡

በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ አንድ ነገር ፍንትው ብሎ ታየኝ፤ ይኸውም በስሕተት ውስጥ መሆኔ፡፡ ይህ ጒዳይ ሲገለጥልኝ ያማረርሁት እግዚአብሔርን ነው፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንዳልሁት ወደዚህ እንቅስቃሴ የገባሁት ሃይማኖቶችን በማወዳደር በራሴ ውሳኔ አይደለም፡፡ ዝም ብዬ ያለ ዕውቀት ነው የገባሁት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ዐይነቱ ውሸት ውስጥ እንድገባ ለምን ፈቀደ? በተጨማሪም ከላይ እንደ ገለጽሁት “በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ውስጥ በተፈጠረው እሰጣገባ ስድስታችን[4] በአንድ ወገን ሌሎቹ ደግሞ በሌላ ወገን በነበርንበት ሂደት ውስጥ፣ ያጋጠሙኝ ሁኔታዎች ቀላል አልነበሩም፡፡ ባለትዳር ነኝ፤ ልጆች አሉኝ፤ የነበረው ቤተ ክርስቲያን በጣም ደካማ ስለነበር ኑሮአችን ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ብቻ ሳይሆን፣ ምንም ሊባልለት እስከማይችል ድረስ፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሳለፍነው፡፡ እኔ፣ ልጆቼና ባለቤቴ የምንበላው ምግብ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጫማው ጫማ እስከምናጣ ድረስ፣ በከፍተኛ ጒስቊልና ውስጥ ነው የገባነው፡፡ በእኛ መረዳት ይህን ሁሉ ዋጋ የከፈልነው ስለ ወንጌልና ስለ ክርስቶስ ብለን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ነገር በሕይወታችን ዐልፎ ነገሮቹ ሁሉ ባዶ ሆነው መገኘታቸው እጅግ በጣም አሳዘነኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እኔ ወደ እንቅስቃሴው የገባሁት የሃያዎቹ የዕድሜዬ ክልል ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ረጅም ዓመታት “ሀ” ብዬ ፊደል በመቊጠር ትምህርት ብጀምር እንኳ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቼ ትምህርቴን የማጠናቅቅበት ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ 17 ዓመታት በከንቱ መቃጠላቸው እጅግ በጣም አሳዘነኝ፡፡ ምክንያቱም ወደዚያ እንቅስቃሴ ያስገባኝ ተክለ ማርያም አይደለም፤ ጓደኛዬም አይደለም፡፡ ስለዚህ የችግሩ ተወቃሽ ማንም አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ ክፉኛ ተማረርሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁኔታዎች በመመልከት በግትርነት በቀድሞው አቋሜ መቀጠል አለብኝ የሚለውን ጒዳይ ውስጤ በፍጹም ሊቀበለው አልቻለም፡፡ ልቤ ተይዞአል፤ ተማርኳል፡፡

ከእውነት ጋር መገናኘት

ስለ ሥላሴ ባላውቅም እንኳን በዘመኔ ሁሉ የሥላሴን ትምህርት ስቃወም፣ ሰዎችን ከዚህ አስተምህሮ ሳፈናቅል ነው የቈየሁት፡፡ በወቅቱ ብቸኛ አማራጭ ነው ብዬ ያሰብሁት፣ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት በመቅረብ፣ እግዚአብሔር ራሱ እውነቱን እንዲገልጽልኝ መጠየቅ ነበረ፡፡ ይህን አቋም ወስጄ ያላንዳች የሥላሴም ሆነ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ተሳቢ ሳላደርግ፣ መጽሐፍ ቅዱሴን ለማንበብ ወሰንሁ፡፡ በሥላሴአውያንም ሆነ፣ “በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አተያይ ሳይሆን፣ ቃሉን ሌጣውን በማጥናት እኔ የማገኘውን መረዳት ለመውሰድ ራሴን አሳመንሁ፡፡

ጥናቴን የጀመርሁት የዮሐንስን ወንጌልና የዮሐንስን መልእክቶች በማጥናት ነበር፡፡ የማታ ማታ አንድ ነገር ለውስጤ ሰላም ሰጠው፡፡ ይኸውም:— ሥላሴ የሚለው ጒዳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ፡፡

ምናልባት ያን ጊዜ ስለ ሥላሴ አብራራ ቢሉኝ ላብራራ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ የሥላሴ አስተምህሮ አንደኛ ለልቤ ሰላም ሰጥቶታል፤ ሁለተኛ፣ “በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ውስጥ በነበርሁበት ጊዜ የድርጅቱን አስተምህሮ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ የሚል የራሴ የሆነ መረዳት ቢኖረኝም፣ የሚፈታተኑኝ ልረዳቸው የሚያስቸግሩኝ፣ የሚያውኩኝ ክፍሎች ነበሩ፡፡ በተለይ ሦስት ክፍሎች፤ አንደኛው የዮሐንስ ወንጌል 14 ላይ ያለው ክፍል “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ ወደ አባቴ እሄዳለሁ”፣ የሚለው ዐሳብ ላይ፣ ተናጋሪው የሚናገረው አባቴ እያለ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አብም ወልድም እሱ ነው ስል ነው የከረምሁት፤ አብ ነው ያልሁት ኢየሱስ አባቴ ብሎ ሲናገር፣ እርሱ ራሱ ተመልሶ እንዴት አብ ሊሆን ይችላል? ይህ ጒዳይ ወልድ ከአብ የተለየ ማንነት ያለው ነው ወደሚለው ድምዳሜ እንዳልደርስ፣ በወቅቱ የነበርሁበት ትምህርት ሥላሴን እንድቀበል ዐይኔን ሸብቦ አስሮት ስለነበር፣ ነገሩን አናንቄ ማለፍ ነው የምመርጠው፡፡

21ኛው ቊጥር ላይ ደግሞ፣ “የሚወደኝን አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ…ወደ እርሱ እንመጣለን፣ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” የሚለው ክፍል፣ ኢየሱስ በብዙ ቊጥር ነው ስለ እርሱና ስለ አባቱ የሚናገረው፡፡ ምዕራፍ 17 ላይ ስለ እርሱና ስለ አባቱ “እኛ” እያለ የሚናገረው፡፡ እነዚህ ክፍሎ ምንም ዐይነት ማስረጃ ላገኝላቸው የማልችላቸው ክፍሎች ነበሩ፡፡ የሚገርመው ይህ ጥያቄ የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የባለቤቴ ጥያቄም መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ይህን ጥያቄ ስትጠይቀኝ፣ እኔም ራሴ ጥያቄ የፈጠረብኝ ክፍል ነው ከማለት ይልቅ፣ ብዙ ጊዜ የምሰጠው መልስ፣ “ዝም ብለሽ መጽሐፍ ቅዱስሽን አጥኚ” የሚል ነበር፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ላይ እኔ ራሴ ጥያቄ እንዳለኝ ገልጬላት አላውቅም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት “ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ጋር የነበረን ኅብረት በብዙ አሸንፎን ስለነበር፣ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከመንገዳችን እንድንመለስ አላደረገንም ነበር፡፡ ይህም ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የኖረ ጒዳይ ስለነበር አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ብሎ ማመኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን በግልጥ መረዳት ቻልሁ፡፡

ኦንሊ ጂሰስ በነበርሁበት ጊዜ እንደምለው አብም፣ ወልድም፣ መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስ ነው ብዬ ቀጣጥዬ እንደማወራው ትምህርተ ሥላሴን ማብራራት ባልችልም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያየ ማንነት እንደ ነበራቸው ግን መረዳት ቻልሁ፡፡

የዮሐንስ ወንጌልንና የዮሐንስ መልእክቶችን አንብቤ እንደጨረስሁ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተንበርክኬ ጸለይሁ፡፡ በመጀመሪያ ውስጤ ስላለመደው ፈርቶታል፤ በጸሎቴም ፈራ ተባ ብያለሁ፡፡ ነገር ግን ደጋግሜ ስጸልይ በውስጤ ትልቅ ደስታና ሐሴት ነው የፈሰሰው፡፡

ብዙ ጊዜ ለሰዎች ተናግሬአለሁ፡፡ በዚህ ጒዳይ ላይ አንዳንድ ሰዎች ምስክርነት ስጥ ሲሉኝ፣ ስለ ሥላሴ ለመረዳት ለእኔና ለእናንተ አንድ አይደለም፤ እኔ የሥላሴን እውነት በተቀበልሁበት ዕለት፣ እግዚአብሔር በውስጤ በመንፈሱ ያስቀመጠው ትልቅ ደስታና ሐሴት እናንተ እንደ እኔ ስላልነበራችሁ ልትረዱኝ አትችሉም፤ ስለዚህ ይህ እውነት በቃሌ ከማስረዳው ይልቅ በውስጤ እውነት ነው የሚለውን ነገር እነግራቸዋለሁ፡፡ በዚያን ቀን መንፈስ ቅዱስ በውስጤ ያደረገው ነገር ትልቅ ማረጋገጫ ሆኖኛል ብዬ የተናገርሁባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ምን ጊዜም ከልቤ የማይደመሰስ ትልቅ ደስታና ሐሴት ነው በልቤ አስቀምጦ ያለፈው፡፡

መሠረተ እምነታችንን እንወቅ

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ዐልፌ ከዓመታት በኋላ፣ አንዳንድ ሰዎች “ከኦንሊ ጂሰስ” ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ፣ የምነግራቸው የራሴን የግል ምስክርነት ነው፡፡ በምን ሁኔታ ውስጥ ዐልፌ ወደዚህ ደረጃ እንደደረስሁ እተርክላቸዋለሁ፡፡ ያለፍሁባቸውን ጐዳናዎች ሁሉ አስቃኛቸዋለሁ፡፡ ከትምህርተ መለኮት ውይይቱ ይልቅ ይህ የብዙዎችን ሕይወት ሲነካ አይቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ትምህርት የሚቀበሉበት ምክንያት፣ ሰዎች ትምህርተ ሥላሴን መረዳት ስለሚቸግራቸው፣ ርእሰ ጒዳዩንም ጊዜ ሰጥቶ ለማጥናት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው፡፡ በርካታ የሥላሴ አስተምህሮ አማንያንም በአስተምህሮው ላይ የጠለቀ መረዳት ስለሌላቸው፣ “ከኦንሊ ጂሰስ” የሚመጡትን ማነጋገር አይችሉም[5]፡፡

አንድ የማስታውሰው ታሪክ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ወዳጄ የሆነ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ ነው፡፡ አንዲት የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልጅ ጐረቤቷ የነበሩ አንዲት እናት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድትጠመቅ ነግረዋት ከእኔ ጋር ያገናኟታል፡፡ እኔም ጥምቀት በኢየሱስ ስም ብቻ መካሄድ እንዳለበት፣ በኢየሱስ ስም ያልተጠመቀም ሰው ድነት እንደማያገኝ ነገርኋት፡፡ ነገሩን ብትቀበለውም እንኳ፣ ቀድሞ የነበረውን የሥላሴ እምነቷን ጥላ ወደዚህ እምነት ለመምጣት ተቸገረች፡፡ ከዚህ የተነሣ ወደሚከተለው አቋም ላይ ደረሰች፣ “የእኔን ቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ወንጌላዊ እጠራለሁ፤ አንተና እርሱ በርእሰ ጒዳዩ ላይ ትነጋገራላችሁ፤ ከሁለታችሁ ያሸነፈው ወገን ይወስደኛል” አለች፡፡ እኔም ጒዳዩን በደስታ ተቀበልሁት፡፡ ያም ወንድም ተጠርቶ መጣ፤ በጊዜው የታወቀ ወንጌላዊ ነው፤ እኔም በርቀት የማውቀው ሰው ነበር፡፡ እኔ በጒዳዩ ላይ ተዘጋጅቼ፣ እንዳያመልጥ አድርጌ ለመያዝ እንዲመቸኝ በጣም ትሑት ሆኜ ተቀበልሁት፡፡ ጸሎት እንዲጸልይም ቅድሚያውን ለእርሱ ሰጠሁት፡፡ እርሱም ውይይቱን በጸሎት ጀመረ፡፡ አሁን ወግ ባለው መንገድ ውይይታችንን ለማካሄድ እኔ ንግግሬን ስጨርስ እርሱ ይናገራል፤ እርሱ ሲጨርስ ደግሞ እኔ እናገራለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ትርምስ እንዳይኖር እንዲሁም ሰዎች ጒዳዩን በትክክል እንዲረዱ ያደርጋቸዋል ወደሚለው መግባባት ላይ ደረስን፡፡

ብዙ እየተነጋገርን መጣን፤ ነገር ግን ግለሰቡ የሥላሴ አማኝ ይሁን እንጂ፣ በሥላሴ ትምህርት ላይ ጥልቀት ያለው ዕውቀት ስላልነበረው፣ እኔ ደግሞ አለኝ በምለው በቀድሞ ትምህርት ላይ ጥሩ መረዳት ስለነበረኝ፣ ቀስ እያልሁ እያደበላለቅሁበት መጣሁና በመጨረሻም ይህ ስመ ጥር ወንጌላዊ ትምህርቱ ጠፋበት፡፡ እርሱ መልስ እያጠረው ሲመጣ፣ እኔ ደግሞ የልብ ልብ እየተሰማኝ፣ “ዐዋቂ ነህ” የሚል ብርታት እያገኘሁ መጣሁ፡፡ በአሸናፊነት ስሜት ተሞላሁኝ፡፡ ከዚህ የተነሣ ከበፊቱ ይልቅ እጅግ ትሑት ሆንሁ፡፡ በመጨረሻ እርሱ መልስ እያጠረውና ዐውቀዋለሁ የሚለው ትምህርት እየተደበላለቀበት ሲመጣ፣ ቊጣ ቊጣ ይለው ጀመር፤ ተናደደ፤ ተነሥቼ እሄዳለሁ አለ፡፡ እኔ ደግሞ በፍጹም ይህ መሆን የለበትም ውይይታችንን በጸሎት ስለጀመርን በጸሎት መጨረስ ይኖርብናል አልሁት፡፡ ነገር ግን ለመቆየት ፍጹም ፈቃደኛ ስላልሆነ ተነሥቶ ሄደ፡፡ ልጅቷን ትቷት መሄዱን ግን አልተገነዘበውም ነበር፡፡

በሥላሴ ትምህርት ላይ አብዛኞቹ የሥላሴ አማንያን፣ ራሳቸው አጥጋቢ የሆነ መረዳት አላቸው ማለት አያስደፍርም፡፡ በርካታ አገልጋዮች፣ “ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” የሚመጡትን ሰዎች ራሳቸው ከማነጋገር ይልቅ ወደ እኔ የሚልኩበት ዐቢይ ምክንያት “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን” አስተምህሮ ያለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ምናልባት በሥላሴ አስተምህሮ ላይ ጠንካራ ዕውቀት ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፡፡

“ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” እኔ ዘንድ የሚመጡትን ሰዎች በቅድሚያ የምነግራቸው ከድርጅቱ ጋር የነበረኝ የራሴን የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ የእኔን ተሞክሮ ካሳየሁአቸው በኋላ የዮሐንስ ወንጌልን እንዲያነቡ፣ እንዲጸልዩ፣ የእግዚአብሔርን ርዳታ እንዲሹ እመክራቸዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ነገረ መለኮቱ ትንታኔ በስፋት የምገባው፡፡ በዚህ ዐይነቱ አካሄድ ብዙ ሰዎች ተመልሰዋል፡፡ በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ረድቷቸው በኋላ አገልጋይ የሆኑ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ ሙስሊሞችንና እነርሱን መርታት የሚችለው ጸሎት፣ ፍቅርና መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡

“በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አካባቢ ያስሄደኛል፣ መሠረተ እምነቴን ያጸናልኛል በሚሏቸው ጥቅሶች ላይ ክርክር ስለሚያስተምሯቸው ብዙዎቹ፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አማንያን ክርክር ይወዳሉ፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ለክርክሩ መልስ የለውም፡፡ ይህ የሚሆነው ግን፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አማንያንና የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች በቃለ እግዚአብሔር ላይ ጠንካራ ዕውቀት ስላላቸው ሳይሆን፣ በጣት የሚቈጠሩ ጥቅሶችን በቃል በማስጠናትና ክፍሎቹን በድርጅቱ አስተምህሮ መሠረት በመተንተን ተከታዮቻቸውን ስለሚያሠለጥኑ ነው፡፡ ስለዚህ የድርጅቱ ሰዎች መከራከር ይወዳሉ፡፡ የሥላሴ አማንያኑ ግን ለአስተምህሮው ከፍተኛ ትኲረት ስለማይሰጡ እንዲሁም በሌላ ድርጅት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ከአካሄዳቸው እንዲመለሱ በሌላ ወገን ያለውን ትምህርት ስለማያጠኑ እንዲሁም ቀዳሚ ላልሆኑ ነገሮች ከፍተኛ ትኲረት ስለሚሰጡ እነሱ የሚያቀርቡላቸውን ጥያቄና ትንተና መልስ ለመስጠት ይቸግራቸዋል”፡፡

የእኔና የቤተሰቤ ቀጣይ ታሪክ

እንግዲህ በዚህ ዐይነት መንገድ ነው፣ እግዚአብሔር እኔን ያሸነፈኝ፡፡ ከነበርሁበት አስተምህሮ የአቋም ለውጥ ሳደርግ፣ ከአሁን በኋላ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚው ጥያቄዬ ሆነ፡፡ አቋሜን መግለጥ ይፋ ማድረግ አለብኝ በሚለው ጒዳይ ላይ ውሳኔ አደረግሁ፡፡ እኔና አምስት ሰዎች ከነ ቄስ ተክሌ በተለየን ጊዜ፣ የእኛ ኅብረት ቄስ አማረ ዋቅቶላን የበላይ ኀላፊ አድርጎ እኔን ደግሞ የዐዲስ አበባ ኀላፊ አድርጎኝ ነበር፡፡ ስለዚህ የእኔ አለቃ ቄስ አማረ ዋቅቶላ ስለነበር፣ ቄስ አማረን እና አቶ ሰሎሞን ሎዳሞን በመጥራት አቋሜን አስታወቅኋቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቁትን ሰዎች አልዳናችሁም ማለቴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ንስሓ ገብቻለሁ፡፡ ሰዎች በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀው ይድናሉ፡፡ ስለዚህ እኔ በዚህ መንገድ የተናገርሁት የሰበክሁትም ትምህርት ሁሉ ትክክል አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ያሰናከልሁአቸውና ከእምነታቸው ስላወጣሁአቸው ሰዎች ንስሓ ገብቻለሁ፡፡ እግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቄአለሁ፡፡ እኔ እንግዲህ ከአሁን በኋላ ከእናንተ ጋር አይደለሁም፤ ልሆንም አልችልም አልኋቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች ግን ለዚህ ጒዳይ ብዙም ትኲረት የሰጡት አልመሰለኝም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ቀድሞ በነበረው እሰጣገባ እንዲሁም በደረሰበት የኢኮኖሚ ችግር አእምሮው ተነክቶ ሊሆን ይችላል በማለታቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ንጉሤ ከማንም፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ሰዎች ይልቅ አስተምህሮውን ይተነትናል የምባልና ለብዙዎች እንደ ተምሳሌት የምታይ ሰው ነበርሁ፡፡ እነርሱ ራሳቸው በጣም ኀይለኛ ተከራካሪዎች ሲመጡባቸው የሚልኳቸው እኔ ዘንድ ነበር፡፡ ወደ እኔ የመጡትን ደግሞ፣ ቢሆን ቢሆን የሥላሴ እምነታቸውን አስጥላቸዋለሁ ወይም ደግሞ ክፉኛ አደናግራቸዋለሁ፡፡ ከሁለት አንዱ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በደርግ ዘመን ወደ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ነፍሳትን ለመስረቅ እሄድም ነበር፡፡ በአጠቃላይ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች ዘንድ እንኳ የታወቅሁ ነበርሁ፡፡ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው፣ የድርጅቱን አስተምህሮ ለቅቆ ይሄዳል ብሎ ማሰብ በፍጹም የሚከብድ ነበር፡፡

በ1979/80 ዓ.ም የቄስ ተክለ ማርያም ሚስት ወይዘሮ እርቅነሽ እናንተ ወደ እኛ እንድትመለሱ እግዚአብሔር ልኮናል ብላ በመምጣት ከእነርሱ ጋር የእርቅ ድርድር ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ምንም እንኳ እኔ አቋሜን ባሳውቃቸውም፣ ከላይ በጠቀስሁት ምክንያት በድርድሩ ወቅት ዐብሬአቸው እንድሆን እነ ቄስ አማረ ስለጠየቁኝ፣ በድርድሩ ወቅት አብሬአቸው ነበርሁ፡፡ በድርድሩም ወቅት ከተነሡት የትምህርተ መለኮት ውይይቶች መኻል አንዱ፣ “ሰማያዊ ሥጋ” የሚለው የቄስ ተክሌ ትምህርት ነበር[6]፡፡ ምክንያቱም ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ፣ ብዙ ሰዎች ይህን ትምህርት ተቃውመው ነበርና ነው፡፡

ከቄስ ተክሌ ከተለየን በኋላ እንኳ ከቄስ ተክሌ ጋር ኅብረት አንፈጥርም ካልንባቸው ምክንያቶች መኻል አንዱ ቄስ ተክሌ፣ “ሰማያዊ ሥጋ” የሚባል የኑፋቄ ትምህርት ያስተምራል የሚባለው ጒዳይ የመከራከሪያ ነጥባችን ነበር፡፡ በዚህ ጒዳይ ላይ ሰፊ ክርክር አደረጉ፡፡ እኔ ግን በክርክሩ ውስጥ አልነበርሁም፡፡ ምክንያቱም እኔ ከእርሱ ጋር ስለማልቀጥል፣ ነውም አይደለምም የሚለው ጒዳይ ለእኔ መሠረታዊ ጒዳይ አልነበረም፡፡ ቄስ ተክለ ማርያም ግን፣ “ይህን ትምህርት የገለጠልኝ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ለእናንተም አንድ ቀን ሊገልጥላችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን መሠረታዊው በሆነው ትምህርት ላይ ተመሳሳይ አቋም ስላለን፣ ይህ ትምህርት ሊለያየን የሚችል ጒዳይ አይደለም” በማለቱ ስምምነቱ እንዲካሄድ ተደረገ፡፡[7]

እንግዲህ በዚህ መልክ እኔ ከእነርሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ አቋረጥሁ፡፡ ከዚህ በኋላ የእኔ ትልቁ ጥያቄ፣ የእኔ ውሳኔ በእኔና በቤተሰቤ ቀጣይ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ስለሚያመጣ፣ ምን ማድረግ አለብኝ በሚለው ነጥብ ላይ ያተኰረ ነበር፡፡ ልጆቼ ጐፋ ሰፈር ወደሚገኘው፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ይሄዱ ስለነበር፣ እነርሱንስ ምን ማድረግ አለብኝ? ይህ ሁሉ ሲሆን ባለቤቴ በቀድሞ እምነት ውስጥ ስላለች እርሷንስ በተመለከተ ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው? ጒዳዩን እንዴት ነው ላስረዳት የምችለው? ልጆቼ በቀድሞው ትምህርት እንቈያለን ቢሉ፣ ባለቤቴ የድርጅቱን ትምህርት ስሕተት መሆኑን ባትገነዘብ የማደርገው ምንድን ነው? የሚለው ጒዳይ በብዙ ያሳስበኝ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ አስቀድሞ ሠርቶአቸው ስለነበረ፣ ጒዳዩ እንዳሰብሁት አስቸጋሪ አልሆነብኝም፡፡ አንድ ቀን ለባለቤቴ ያለኝን አቋም ነገርኋት፡፡ እርሷም፣ “አብና ወልድ የተለያዩ መሆናችውን በተደጋጋሚ ነግሬህ ነበር፡፡ እኔ ራሴ በድርጅቱ ትምህርት ላይ ብዙ ጥያቄ አለኝ” አለችኝ፡፡ እንግዲያውስ ይህ የእኔ አቋም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከቀድሞ ድርጅትና እምነት ለመልቀቅ ወስኛለሁ አልኋት፡፡ እርሷም በአቋሜ ተስማማች፡፡ በአጠገባችን ቂርቈስ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ስለነበር፣ ወደዚያ ሄደው ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ለልጆቻችን ስንገልጽላቸው ያላንዳች ቅሬታ ጒዳዩን ተቀብለው፣ ቂርቈስ መካነ ኢየሱስ በመሄድ ቃለ እግዚአብሔርን መማር ጀመሩ፡፡ በዚህ ዐይነት መልክ ለቤተ ሰቤ የነበረኝ ጭንቀት በአስደናቂ ሁኔታ ዕልባት አገኘ፡፡

በቅዱሳን ኅብረት መታቀፍ

የእኔና የቤተሰቤ ቀጣዩ ጒዳይ የትኛው ቤተ ክርስቲያን እንሂድ የሚለው ሆነ፡፡ የእኔ ምርጫ እምብዛም የማትታወቅ አንዲት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን በአባልነት መታቀፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ያቺ ቤተ ክርስቲያን የት እንዳለች፣ እንዴትስ እንደምትገኝ፣ እንዴትስ አባል ሊሆኗት እንደሚቻል የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ በማንታወቅበት ቦታ ተጠልለን እግዚአብሔርን እያመለክን እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሥራችንን እየሠራን እንኖራለን አልን፡፡ እግዚአብሔር በዚህ መልኩ እንዲመራን ጸሎታችንን እናደርስ ነበር፡፡ ይህ መሻታችን እውን እንዲሆን፣ እኔና ቤተሰቤ አጥብቀን በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንቀርብ ነበር፡፡

አንድ ቀን ሁለት እናቶች ቤታችን መጡ፡፡ አንደኛዋ እናት ከእኔ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ እኔ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ሰባኪ እንደሆንሁ ያውቃሉ፡፡ እርሳቸው ሰፈር አንዲት ታዋቂ የሆኑ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አባል፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” መሠረተ እምነት ውስጥ ሳለሁ አጥምቄአቸዋለሁ፡፡ እርሳቸው ደግሞ ይህን ያውቃሉ፡፡ በተጨማሪም የእርሳቸው ሰፈር ሴት የሆኑና፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አማኒ የነበሩ ታዋቂ ሴት ዘንድ በመሄድ እንደማገለግላቸው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን እኝህ ሴት የፍቅር ሰው ስለነበሩ፣ መንገድ ላይ ሲያገኙኝ ሳይስሙኝ ዐልፈው አያውቁም፡፡ ልክ እንደ ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አድርገው ጤናዬን እንዲሁም ቤተሰቤን ጠይቀውኝ ነው የሚያልፉት፡፡ እንግዲህ እርሳቸውና አንድ ሌላ እናት ናቸው እኔ ቤት በድንገት የመጡት፡፡ በጣም ገረመን፡፡ የት ቤተ ክርስቲያን ነው የምትሄዱት ብለው ጠየቁን፡፡ ነገሩ አስደነቀን፤ ምክንያቱም አሁን ስላለን አቋም ከሰው ይረዱ ወይስ እግዚአብሔር ራሱ ይንገራቸው አልጠየቅናቸውም፡፡ ነገር ግን የትም ቤተ ክርስቲያን እንደማንሄድ ገለጽንላቸው፡፡ እነርሱም “ሙሉ ወንጌል ኑ” ብለውን ተነሥተው ከቤት ወጡ፡፡ እነዚህን ሰዎች የላካቸው እግዚአብሔር ይሆንን? የሚለው ጥያቀ እንዳለ ሆኖ፣ እኔና ባለቤቴ በአባልነት ጒዳይ ላይ መጸለይ ጀመርን፡፡ አገልግሎት የሚለው ነገር ግን ብዙ ዋጋ ስላስከፈለን፣ አገልጋይ የመሆኑን ጒዳይ ሙሉ ለሙሉ ሰርዘናል፤ የት ቤተ ክርስቲያን አባል እንሁን በሚለው ጒዳይ ብቻ ጸሎታችንን በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብ ጀመርን፡፡

በነገራችን ላይ አባል ልሆንበት ከማልፈልጋቸው ቤተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ለምን እንደዚያ እንዳሰብሁ ግን አላውቅም፡፡ ኋላ ግን ወደ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ የእግዚአብሔር ዐሳብ ነው የሚል እምነት በልባችን እየተፈጠረ መጣ፡፡ እቤታችን ከመጡት እናቶች በስተቀር፣ ከሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ጋር ትውውቅ የለንም፡፡ አካባቢያችን የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ እንዲሁም በደንብ የሚያውቀን ሰው አለ፡፡ እርሱ ዘንድ በመሄድ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን እንደምፈልግ ነገርሁት፡፡ እርሱ ግን ደነገጠ፡፡ ይህ ሰው መስሎ ገብቶ ቤተ ክርስቲያን ሊበጠብጥ ነው የሚል እምነት እንዳደረበት ኋላ አጫውቶኛል፡፡ እሺ ብሎ አንዳችም ርምጃ ሳይወስድ ተወን፡፡ ከዚያ በኋላ ቤታችን ከመጡት ከአንደኛዋ እናት ጋር ግንኙነት ማድረግ ጀመርን፡፡ እኔ እሳቸው ቤት መሄድ ጀመርሁ፤ ቤተሰብ ሆንን፡፡ ዐብረን ቃለ እግዚአብሔርን እየተማማርን፣ በኅብረት እየጸለይን ቆየን፤ ምናልባትም የእርሳቸው አገልጋይ ሆንሁ ማለት ይቻላል፡፡ ጒዳዩን ለእከሌ ነገርሁት አልሁአቸው፡፡ እኚህ እናት ከቀድሞዎቹ የሙሉ ወንጌል አባላት መካከል አንዷ ስለነበሩ፣ መጋቢ መርዕድን በአካል ያውቁታል፤ ስለዚህ እኔ ራሴ ለመርዕድ እነግረዋለሁ አሉ፡፡ ደውለውም ስለ ጒዳዩ አጫወቱት፡፡ እርሱ ደግሞ ደውሎ አካባቢዬ ለሚገኘው ለዚያ ወንድም እንዲቀበለኝ ነገረው፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ወንጌላዊ እኔ ዘንድ ይልካሉ፡፡ ይህ ወንጌላዊም በእኚህ እናት ቤት ውስጥ ስለ ጒዳዩ ያነጋግረኛል፡፡ ጒዳዩን በግልጽ ባሳውቀውም እንኳ ሊያምነኝ ግን ይቸገራል፡፡ በሌላ ቀን እኒያ እናት ጒዳዩ ምን ላይ ደረሰ ሲሉ ጠየቁኝ፤ እኔም እስካሁን ምንም ዐዲስ ነገር እንደሌለ ገለጽሁላቸው፡፡ ቆይ እኔ አሁንም ለመርዕድ እነግረዋለሁ አሉ፡፡ ለመጋቢ መርዕድ ሲነግሩት፣ በቤት ኅብረት ውስጥ ይግባ ይላል፡፡ በዚያ ወንድም ቤት ውስጥ የቤት ለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይካሄድ ስለነበር፣ ግለሰቡ ብዙም ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ፣ ጒዳዩ ከፓስተር መርዕድ ስለመጣ ብቻ ሊቀበለኝ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ መንገድ በኅብረቱ ውስጥ በመቀላቀል የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ሆንሁ፡፡

አሁን ወደ ደረስሁበት የአገልግሎት ደረጃ የመጣሁት ቀስ በቀስ ነው፡፡ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በድቁና እያገለገልሁ ወርልድ ቪዥን እሠራ ነበር፡፡ ጐተራ በሚገኘው ጸሎት ቤት ደግሞ የዲያቆናት ሰብሳቢ ሆኜ ማገልገል ጀመርሁ፡፡ ቀድሞም በአገልግሎት ረጅም ጊዜ ስለቆየሁ በተጨማሪም ለማገልገል ትልቅ ሸክም ስለነበረኝ ንቊ አገልጋይ ሆኜ ነው የቀጠልሁት፡፡ በእግዚአብሔር ርዳታ የሰፋ የአገልግሎት በር ነበረኝ፡፡

“የወንጌሉ አገልጋይ ሆንሁለት”    

በዚህ ሁኔታ እያለሁ እግዚአብሔር አገልግሎት መጀመር እንዳለብኝ ተናገረኝ፡፡ ቀድሞ ሕይወቴን ሰጥቼው የነበረው ትምህርት ኋላ ስሕተት ሆኖ ባገኘሁት ጊዜ እንዳዘንሁ ሁሉ፣ አሁንም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንድሆን ጌታ ሲናገረኝ ቅሬታ ተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም ከአገልግሎት አምልጬ እንደ ማንኛውም ሰው ንቊ የቤተ ክርስቲያን አባል ሆኜ እኖራለሁ የሚል አቋም ባለኝ ጊዜ፣ ይህ ጒዳይ ወደ እኔ መምጣቱ አሳዘነኝ፡፡

ወርልድ ቪዥን ውስጥ ሰባት ዓመት ካገለገልሁ በኋላ በ1989 ዓ.ም ላይ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ወጣሁ፡፡ ለአገልግሎት መጠራቴን ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አሳወቅሁ፡፡ እነርሱም በጒዳዩ ላይ ችግር አልነበረባቸውም፤ ምክንያቱም ከሚያዩት ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ጒዳይ እንዳለው፣ ለወንጌል ሥራ የተጠራሁ ሰው መሆኔን ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና ምዕመናን ያውቀው ስለነበር ነው፡፡ በአንዳንድ አገልጋዮች ላይ ደረሰ የሚባለው፣ “መታሸት” (መጒላላት) በእኔ ላይ አልደረሰም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለጊዜው የትራንስፖርት ገንዘብ ሰጥታ፣ በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ተቀብላ አሠማራችኝ፡፡ መጀመሪያ በወንጌላዊነት ቀጥሎም በመጋቢነት አገልግሎት ተሹሜ ሳገለግል ከቆየሁ በኋላ፣ ተቀዳሚ መጋቢው ሲለቁ አሁን በዋና መጋቢነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡

የታሪካችን ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ባለፍንባቸው ጐዳናዎች ሁሉ ያልተለየን በድካማችን የተሸከመን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡


[1] በአሜሪካን አገር “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን” መሠረተ እምነት የሚከተሉ በርካታ ቤተ እምነቶች ቢኖሩም እንኳ፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚስዮናዊ የላከው፣ “የተባበሩት ጴንጤቈስጣውያን” (United Pentecostal Church International–UPCI) የተባለው ቤተ እምነት ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም (UPCI) በኢትዮጵያ ከሚገኘው “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ጋር ዐብሮ ይሠራ ነበር፡፡ ለበለጠ ማብራሪያ፣ የዚህን መጽሐፍ የመጀመሪያ ቅጽ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ዳራ” የሚለውን ክፍል ይመለከቷል፡፡

[2] በአሁኑ ወቅት ከመጋቢ ንጉሤ ኀይሌ በስተቀር እነዚህ ሰዎች በሙሉ በከፍተኛ የኀላፊነት ቦታ በድርጅቱ ውስጥ በመሥራት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሰሎሞን ሎዳሞ ከቄስ ተክሌ ኅብረት ውጪ ከዓለም ዐቀፉ ቢሮ ጋር የሚሠራ ቢሆንም እንኳ፣ ሰማያዊ ሥጋ ከሚባለው ከቄስ ተክሌ ትምህርት በስተቀር የድርጅቱን አስተምህሮ ሙሉ በሙሉ ይቀበላል፡፡

[3] ሰሎሞን ሎዳሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የቄስ ተክሌን “ሰማያዊ ሥጋ” ትምህርት በመቃወም በርካታ፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያናትን” ከጐኑ በማሰለፍ፣ ከዩናይትድ ፔንቲኮስታል ጋር የሚሠራ ሰው ነው፡፡  

[4] እንቅስቃሴውን የምንመራው ስድስታችን እንሁን እንጂ፣ የእኛን አካሄድና አስተምህሮ የሚደግፉ በርካታ ሰዎች ከእኛ ጋር ዐብረው ነበሩ፡፡

[5] ስለ ትህርተ ሥላሴ ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ የዚህን መጽሐፍ የመጀመሪያ ቅጽ እንዲሁም የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “የአስተምህሮተ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት” በሚል ርእስ ያዘጋጀውን መለስተኛ መጽሐፍ ይመለከቷል፡፡

[6] “ሰማያዊ ሥጋ” በመባል የሚታወቀው የቄስ ተክሌ አስተምህሮ፣ በቄስ ተክሌ የበላይ ጠባቂነት ሥር ባለችው ቤተ ክርስቲያንና በዓለም ዐቀፉ ቢሮ ዘንድ ትልቅ ልዩነት የፈጠረ እንዲሁም ቄስ ተክሌ በዓለም ዐቀፉ ቢሮ “መናፍቅ” ተብለው እንዲወገዙ ያደረገ፣ የቄስ ተክሌ መጽሐፍ ድርጅት በሚገኝባቸው በሌሎች አገሮች እንዳይሸጥ በዓለም ዐቀፉ ቢሮ የበላይ ጠባቂ እንዲታገድ ያስደረገ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ ትምህርት ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ የዚህን መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍል ይመልከቱ፡፡

[7] ቄስ ተክሌ ይህን ትምህርት ማስተማር የጀመረው 1970 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ነገሩን ስንሰማ ትምህርቱ ትክክለኛ አይደለም ብለን ተቃውመናል፡፡ ሲጀመር ግን ጥቃቅን መገለጥ እንጂ፣ መሠረታዊ የነገረ መለኮት ትምህርት አልተወሰደም፡፡ የቄስ ተክሌን ስብከት ወይም ትምህርት የሚከታተል ሰው በግልጽ የሚረዳው ጒዳይ፣ ትምህርቶቹን ሁሉ ከእግዚአብሔር በቀጥታ እንደተቀበለው አድርጎ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ዐዳዲስ መገለጦችን የመሻት ናፍቆት ያለው ሰው ነው፡፡ በመጀመሪያ ትምህርቱን የገለጸው እግዚአብሔር ይህንን ጒዳይ ገለጠልኝ በሚል መልኩ ነው፡፡ ይህን የቄስ ተክሌን ትምህርት ለዓለም ዐቀፉ ቢሮ ይፋ ያደረገው ሰው፣ አሁን ከዓለም ዐቀፉ ቢሮ ጋር ተመሳሳይ አስተምህሮ በመያዝ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራውና ከቄስ ተክሌ ኅብረት የተለየው ሰሎሞን ሎዳሞ ነው፡፡ ይህ የሆነውም ባለቤቱን ዐይኗን ለማሳከም አሜሪካን አገር በተጓዘበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ሰው በዚያን ጊዜ ቄስ ተክሌ ሲያወግዘን ዐብሮን የነበረ ሰው ነው፡፡ ምናልባት ይህን ትምህርት በጥልቀት የሚያውቀው ሰሎሞን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ትምህርት ስሕተት እንደ ሆነም በርካታ ጊዜ አስተምሮአል፡፡

Share the Post:

Related Posts