ጥያቄዎቻችሁና መልሶቻቸው

የምዕራፉ ትልም  

              በዚህ ምዕራፍ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” አባላት ትምህርተ ሥላሴን አስመልክተው ለሚጠይቋቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መልስ እንሰጣለን፡፡

ሀ. መግቢያ

              ትምህርተ ሥላሴን አስመልክቶ፣ ሰዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄዎቹ የሚመነጩት ግን ቢያንስ ከሦስት የተለያዩ ምንጮች ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች በጥሩ ማብራሪያና በአጥጋቢማስረጃ እልባት ሊበጅላቸው የሚችሉ፣ ከዕውቀት ማነስ ችግር የመጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከተሳሳተ መቅድመ ልባዌ የሚመነጩ ናቸው፡፡ ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ ብዙ የተሳሳተ መረጃ፣ በአርዮሳውያንና በሰባልዮሳውያን አማካይነት ይናፈሳል፡፡ ብዙዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የዚህ ስሑት መረጃ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እውነቱን እያወቁ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት እውነቱን ለመቀበል እንዲሁም እውነቱን ለመሸፈን የሚፈልጉ ሰዎች፣ የሚያነሷቸው አዋራዎች ናቸው፡፡ ዐውቆ አጥፊን መመለስ ባይቻልም፣ በተሳሳተ መረጃና በመረጃ ዕጥረት የተሳሳቱትን ሰዎች ማቅናት ግን አግባብ ነው፡፡ እንግዲያው ከላይ ካቀረብነው ትንታኔ ባሻገር ለሚከተሉት ሰባት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተናል፡፡

ለ. ጥያቄዎቹና መልሶቻቸው

፩. “በቅዱሳት መጻሕፍት ሥላሴን አስመልክቶ በቂ መረጃ አልቀረበም”

              አንዳንድ ሰዎች፣ “መጽሐፍ ቅዱስ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የሚሉት ስሞች በአንድ ዐውድ ውስጥ የተጠቀሱት በጣት የሚቈጠሩ ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው፤ ከእነዚህ ምንባባት በመነሣት ትምህርተ ሥላሴን ማስተማር ስሕተት አይሆንምን?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡

              ይህ ፍጹም ነው፡፡ ቢያንስ 55 የዐዲስ ኪዳን ምንባባት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስን በአንድ ዐውድ ውስጥ በጥምረት ተጠቅሰው እናገኛለን[1]፡፡ ይህ እንግዲህ አብና ወልድ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ወይም ደግሞ እያንዳንዱ አካላት በተናጠል የተጠቀሱበትን ክፍሎች አይጨምርም፡፡ ታዲያ እነዚህ፣ “በጣት የሚቈጠሩ ምንባባት” ናቸውን?

፪. “ብሉያት ስለ ትምህርተ ሥላሴ በቂ መረጃ አላቀረቡም”

              አንዳንድ ሰዎች ደግሞ፣ “እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባባት ሁሉ ከዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብቻ የተገኙ ናቸው፤ ብሉይ ኪዳንን ሳይጨምር፡፡ ይህ ለምን እንደ ሆነ አጥጋቢ ማብራሪያ እስካልቀረበ ድረስ፣ ትምህርተ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብለን መቀበል ይቸግረናል” ይላሉ፡፡

              “የይሖዋ ምስክሮች”፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” እንዲሁም የሥላሴን ትምህርት የማይቀበሉ ሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች፣ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንዳችም ትምህርት በማያቀርቡባቸው ወይም ብሉያት እጅግ በጣም አናሳ ማብራሪያ በሰጡባቸው አስተምህሮዎች ላይ አቋም ወስደዋል፡፡ ለምሳሌ:— የውሃ ጥምቀት፣ የጌታ ራት፣ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት፣ የቅዱሳን ትንሣኤ፣ ክርስቶስ የዓለማት ፈጣሪ መሆኑ፣ ክርስቶስ ከሙታን እንደሚነሣ፣ የክርስቶስ ዕርገት፣ ክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጡ፣ ኢየሱስ እስራኤላውያንን፣ “በምድረ በዳ ሲከተላቸው የነበረ ዐለት መሆኑ” ወዘተ በብሉይ ኪዳን አንዳችም ማብራሪያ ያልቀረበባቸው ወይም እጅግ አናሳ መረጃ የተሰጠባቸው ትምህርቶች ናቸው፡፡

              ብሉያት አንዳችም ፍንጭ ባልሰጡባቸው ወይም አጥጋቢ ማብራሪያ ባላቀረቡባቸው በእነዚህ ጒዳዮች ላይ ክርስቲያናዊ ድርጅት ነን የሚሉ ሁሉ አቋም ወስደዋል፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ ዐዲስ ኪዳን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ላይ እጅግ ሰፊ ማብራሪያ አቅርቦ ሳለ፣ ብሉያት ማብራሪያ ስላላቀረቡ እነዚህን ትምህርቶችና መረጃዎች አልቀበልም ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ቢያንስ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንከን አልባ የሆኑ የአምላክ እስትንፋሰ (አፊዎተ) ቃል ናቸው ብሎ ከሚያምን ሰው፣ ይህ ዐይነቱ አቋም ሊኖረው አይገባም፡፡   

              ልብ ልንለው የሚገባን ሌላው ነጥብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት መንገድ ርምደታዊ ነው ከሚባልባቸው ምክንያቶች መኻል ዋነኛው፣ ብሉይ ኪዳን ሰፊ ማብራሪያ ያላቀረበባቸው ትምህርቶች፣ በዐዲስ ኪዳን በማያሻማ መንገድ ሰፊ ትንታኔ ተሰጥቶአቸው መገኘቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ እግዚአብሔር ለዘመናት ተሰውሮ (ምስጢር ሆኖ) የኖረውን ነገር፣ በዘመኑ መጨረሻ ላይ ሁሉን አፍታትቶ እንደ ገለጠው የሚናገሩት (ዕብራውያን 1÷1-3፤ ማርቆስ 4÷11፤ ማቴዎስ 13÷11፤ ሉቃስ 8÷0፤ ሮሜ 16÷25-27፤ 1ቆሮንቶስ 2÷1-10፤ 1ቆሮንቶስ 4÷1፤ ኤፌሶን 1÷8-10፤ 3÷1-10፤ ቈላስይስ 1÷25-27፤ 2÷2-3፤ 1ጢሞቴዎስ 3÷16)፡፡ ስለዚህ ብሉይ ኪዳን ማብራሪያ አላቀረበም ወይም ሰፊ ማብራሪያ አልሰጠም በሚል፣ የዐዲስ ኪዳንን አስተምህሮ አልቀበልም ማለት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወቴና የአስተምህሮዬ መመሪያ ነው ከሚል ክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም፡፡

፫. “ዐዲስ ኪዳን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሰፊ ማብራሪያ አይሰጥም”

            ቅዱሳት መጻሕፍት የአብና የወልድ ያህል፣ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሰፊ የሆነ ማብራሪያ ያላቀረቡት ለምንድን ነው? ይህ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ሕልውና እንደ ሌለው ወይም አምላክ እንዳልሆነ አመላካች ነውን?

              መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ስለ መንፈስ ቅዱስ አጥጋቢ የሆነ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ ይህ መጽሐፍ ብቻ እንኳ ከዮሐንስ ወንጌል አራት ምዕራፎችን መሠረት አድርገን ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ህልውና እጅግ በርካታ መረጃዎችን ተመልክተናል (ከክርስቶስ ጋር በተነጻጸረ መንገድ)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት እንዲሁም ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ፣ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ትምህርት ያላት፣ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መሠረት ስለሆኗት ነው፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ የቀረበው ገለጻ፣ ከአብና ከወልድ ጋር ሲነጻጸር አንሷል የሚባል ከሆነ፣ አስፈላጊ መረጃዎች ሁሉ እስከ ተሰጡን ድረስ አንሷል የሚለው አስተያየት፣ “ከምን አንጻር ታይቶ ነው አንሷል ሊባል የቻለው?” የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ ምክንያቱም የተነገረን ነገር የተሟላ እንዲሁም አስተምህሮአችንን ለመቅረጽ በቂ ነውና፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ፣ አምላክ የበለጠ ማብራሪያ ይሰጠን ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ትችት በተወሰነ መልኩ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የቀረበ ኂስ ሳይሆን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ሙሉዕነት ላይ የቀረበ ትችት ነው፡፡

              ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስለሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ አብንና ወልድን ማክበር እንዲሁም የክርስቶስን ቤዛዊ ሥራ እውን ይሆን ዘንድ ዓለምን ስለ ኀጢአት መውቀስ እንጂ፣ ራሱን ማክበር ስላልሆነ፣ የሥራውን ያህል ለማንነቱ ሰፊ ቦታ ተሰጥቶት ላናይ እንችላለን፡፡ ይህ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተለየ ገለጻ እንዲኖረን የሚያደርገን አይደለም፡፡ ለምሳሌ:— ቤተሰቤን ፎቶ ግራፍ ማንሣት እወዳለሁ፡፡ ከዚህ የተነሣም፣ ልጆቼና ባለቤቴ እጅግ በርካታ ፎቶ ሲኖራቸው፣ እኔ የምገኝባቸው ፎቶዎች ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ምክንያቱም እኔ አብዛኛውን ጊዜ ፎቶ አንሺ እንጂ፣ ፎቶ ተነሺ አይደለሁምና፡፡ ነገር ግን በብዙ ፎቶዎች ላይ አለመታየቴ የለም ወይም የቤተ ሰቡ አባል አይደለም እንድባል አያደርገኝም፡፡ እንዲያውም በፎቶግራፉ እውን መሆን ትልቁን ድርሻ የምወስደው እኔ ነኝ፡፡ 

              ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፋቸው በግልጽ እስከ ተነገረን ድረስ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ዐቢይ ሥራ ኢየሱስን ማክበር ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ስለ ራሱ በብዛት ለምን አልነገረንም የሚለው ክርክር ብዙ አሳማኝ አይሆንም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥም የሚያረካ ሰፊ ትምህርት እንዳለን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ይህ ጥያቄ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት ላይ የሚቀርብ  ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ በቅሳት መጻሕፍት በቂነት (ሙሉዕነት) ላይ የሚነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮአችንን ለመቅረጽ በቂ መረጃ አላቸው እንዲል ይጠበቃል፡፡  

፬. “የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ወስዷችኋል”

“የሥላሴ አማንያን ትምህርተ ሥላሴ ትክክል ነው የሚለውን ቅድመ ግንዛቤ (መቅድመ ልባዌ) በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸው፣ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል” የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ የተሳሳተ ሙግት ነው፡፡ የሥላሴ አማንያን ትምህርተ ሥላሴ ትክክል ነው የሚለውን ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ማጥናታቸው እሙን ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፣ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ሰዎች ወይም “የይሖዋ ምስክሮች”፣ ሰባልዮሳዊና አርዮሳዊ በሆነ እይታ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን መመልከታቸውም የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁሉ የራሱ የሆነ መቅድመ ልባዌ (ቅድመ ግንዛቤ)[2] አለውና፡፡ ስለዚህ እኔ አንዳችም መቅድመ ልባዌ የሌለኝ ወና ቤት ነኝ ማለት የሚችል አንዳችም ፍጥረት (ዘረ አዳም) የለም፡፡ መቅድመ ልባዌን መናቅ፣ የመቅድመ ልባዌን ምንነት በውል ያለመገንዘብ ነው፡፡ እንዲያው ቍም ነገሩ፣ መቅድመ ልባዌ አለን ወይስ የለንም የሚለው ሳይሆን፣ “መቅድመ ልባዌአችን በአጥጋቢ የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ ላይ የተደገፈ ነው ወይስ አይደለም” የሚለው ጥያቄ፣ መቅድመ ልባዌአችን እየባረቀ እንዳይገድለን ቃታ የሚጠብቅልን ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ መቅድመ ልባዌ አላችሁ የሚለው ክስ በከሳሾቹም ላይ የሚወድቅ ስለሆነ፣ በመረጃ ላይ መነጋገራችን የትኛው መቅድመ ልባዌ ትክክል ነው የትኛው ደግሞ ተሳስቷል የሚለውን እንድንወስን ያስችለናል፡፡

. “መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ህልውና ካለው፣ በግዑዝ ተውላጠ ስም ለምን ቀረበ?”

አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ፣ “አብና ወልድ በተባዕት (በወንዴ) ጾታ ሲገለጹ፣ መንፈስ ቅዱስ ግን በግዑዝ ጾታ መቅረቡ፣ አካላዊ ህልውና እንደሌለው የሚያመለክት ነው”፣ የሚል የሙግት ነጥብ አላቸው[3]፡፡ በተለይ ኪንግ ጀምስ የሚባለውን የእንግሊዝኛ ትርጒም ያነበቡ ሰዎች፣ ይህ ጥያቄ በቀላሉ ሲፈጠርባቸው ይታያል—“The Spirit itself beareth witness with our spirit, that we are the children of God” (Rom. 8:16 KJV)— “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል”፡፡ ይህ የግሪክን ሰዋስው ካለማወቅ የሚከሠት ግራ መጋባት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰዋሰዋዊ ጾታና ተፈጥሮአዊ ጾታ አንድ ናቸው፤ ለምሳሌ “ወንድ” የሚለው ተባዕት፣ “ሴት” የሚለው አንስታይ እንዲሁም “መኪና” የሚለው ደግሞ የግዑዝ ጾታን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለእነዚህም ስሞች የምንጠቀመው ምድብ ተውላጠ ስም (pronoun) ትክክለኛውን ጾታ የሚያጣቅስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ነው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰዋስው ተፈጥሯዊ ጾታና የሰዋስው ጾታ አንድ ናቸው ያልነው፡፡ ሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በእንግሊዝኛ ወይም በግእዝ ወይም ደግሞ በሌላ ቋንቋ ሳይሆን፣ ኮይኔ በሚባለው የግሪክ ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ ኮይኔ ግሪክ ከእንግሊዝኛ ሰዋስው በእጅጉ የሚለይበት የራሱ የሆነ ጠባይ አለው፡፡ በኮይኔ ግሪክ ማናቸውም ዐይነት ስሞች፣ በሦስት መደብ ይከፈላሉ፡፡ ይኸውም አንስታይ (ሴቴ)፣ ተባዕታይ (ወንዴ) እና ግዑዝ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን በተባዕታይ ጾታ የቀረበው አካል ወንድ ነው፣ በአነስታይ ጾታ የተገለጠው ሴት ነው እንዲሁም በግዑዝ ጾታ የቀረበው ግዑዝ ነው ማለት አይደለም፡፡ የሰዋስው ጾታና ተፈጥሯዊ ጾታ የተለያዩ ናቸው ያልነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ለምሳሌ:— “ሞት” (ግሪክ ታናቶስ θάνατος) ተባዕታይ ጾታ ሲኖረው፣ “ኀጢአት” (ግሪክ ሀማርትያ ἁμαρτία) ደግሞ አነስታይ ጾታ አለው፡፡ “ልጅ” (ቴክኖን τέκνον) እንዲሁም “ሕፃን” (ፓይዲዮን παιδίον) የሚሉት ቃላት የግዑዝ ጾታ አላቸው፡፡

              “ሕፃን” (ፓይዲዮን παιδίον) የሚለው የግሪክ ቃል ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡፡ ቃሉ ዐዲስ ኪዳን ግሪክ 52 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሰብዐ ሊቃናት ትርጒም ደግሞ 168 ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የቃሉ ሰዋስዋዊ ጾታ ግዑዝ ይሁን እንጂ፣ ሕፃን ልጅ ግዑዝ አይደለም፡፡ የግድ ተባዕታይ አለያም አንስታይ ጾታ አለው፡፡ ለምሳሌ:— ኢየሱስ በዐዲስ ኪዳን ግሪክ 11 ጊዜ ሕፃን ተብሏል፤ ቃሉ የግዑዝ ጾታን ከማመልከቱም ባሻገር፣ ምድብ ተውላጠ ስሞቹ ግዑዝ ጾታን አመላካች ናቸው (ማቴዎስ 2÷8፤ 9÷11፣ 13 [2 ጊዜ]፤ 14÷20 [2 ጊዜ]፤ ሉቃስ 2÷17:27:40)፡፡ ነገር ግን እንዲያው የለየለት ወፈፌ ካልሆነ በቀር፣ ጌታ ሕፃንነቱ ወቅት ግዑዝ ነበር የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም (ከዚህ ሰዋሰዋዊ ጾታ በመነሣት)፡፡ ለዚህም ነው በግሪክ ሰዋስው ተፈጥሯዊ ጾታና ሰዋስዋዊ ጾታ ለየቅል ናቸው የሚባለው፡፡

               በግሪክ ሰዋስው ጾታ ምን ዐይነት ባሕርይ እንዳለው የዚህን ያህል ከተመለከትን ጥያቄውን መመለስ እንችላለን፡፡ በግሪክና “መንፈስ” (ኒውማ πνεῦμα) የሚለው ስም መንፈሳዊ አካላትንም ሆነ (ርኲሳንንም ሆነ ቅዱሳን መላእክትን[4]) መንፈስ ቅዱስን ለማሳየት ጥቅም ላይ ቢውልም፣ ቃሉ በሰዋስው አካሄዱ የግዑዝ ጾታን ስለሚያመለክት ቃሉም ሆነ ቃሉን ተከትለው የሚመጡ ምድብ ተውላጠ ስሞች፣ የግዑዝ ጾታን ያሳያሉ (ለምሳሌ:— ዮሐንስ 4÷24፤ ግሪክ ምድብ ተውላጠ ስሞች ከጾታው ጋር ይጣጣማሉ፤ ነገር ግን አንዳንዴ የዐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ይህን ሕግ በመተላለፍ ከሰዋስው ይልቅ ለነገረ መለኮቱ ትኲረት ሰጥተዋል)፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ፣ ጰራቅሊጦስ (ፓራክሊቶስ παράκλητος) ተብሎ በተጠራባቸው ቦታዎች ላይ፣ የተባዕት ጾታ እንዲሁም ምድብ ተውላጠ ስሞቹ የተባዕት ጾታ ይዘው ገብተዋል (ለምሳሌ ዮሐንስ 14÷26፤ 1ዮሐንስ 2÷1)፡፡

              “አጋንንት” (ዳይሞኒዎን δαιμονίων) የሚለው ቃል፣ የግዑዝ ጾታን አመልካች ነው፡፡ ነገር ግን ርኲሳን መናፍስት ግዑዛን ናቸው ማለት አይደለም (ራእይ 18÷2፤ ማቴዎስ 7÷22፤ ማርቆስ 16÷9:17፤ ሐዋርያት ሥራ 17÷18)፡፡ ስለዚህ ሮሜ 8÷16 ጨምሮ ሌሎችም ቦታዎች መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክቱ ምድብ ተውላጠ ስሞች፣ የግዑዝ ጾታን ማሳየታቸው መንፈስ ቅዱስ ግዑዝ ነው ወይም አካላዊ ህልውና የለውም ወደሚለው ድምዳሜ የሚያደርሱ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ፣ “ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” እና “ከይሖዋ ምስክሮች” የሚቀርበው ትችት፣ ይህን መሠረታዊ የሰዋስው አካሄድ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ ለዚህም ነው በሰባልዮስና በአርዮስ አስተምህሮ ውስጥ ያሉትን ሰዎች፣ የእናት ቋንቋውን ሰዋስው እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ያፈታት ጥበብ (ቢያንስ የመጀመሪያዎቹን ክፍሎች) ተማሩ በማለት የምንወተውተው፤ የምንዋትተው፡፡

፮.“ኢየሱስ ክርስቶስ በቀጥታ፣ ‘እኔ አምላክ ነኝ’ ለምን አላለም?”

              የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን በግልጽና በስፋት የሚያስተምሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ሰዎች ቃል በቃል ኢየሱስ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” ለምን አላለም? ኢየሱስ ይህ ዐይነቱን ንግግር በግልጽ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ወይም “የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነኝ” ቢል ኖሮ፣ አምላክነቱን መቀበልም ሆነ ትምህርተ ሥላሴን ማመን አዳጋች አይሆንም ነበር ይላሉ፡፡ በመሠረቱ በዐዲስ ኪዳን ምንባባት፣ ይህ ዐይነቱ ንግግር ቃል በቃል ተጠቅሶ አለመገኘቱ እሙን ቢሆንም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ የአገላለጽ መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በግልጽና በስፋት ያስተምራል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከሚቀርቡ አጥጋቢ መልሶች መኻል የሚከተሉት አራት ነጥቦች ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገባ ይመስለኛል:—

              አንደኛ፤ ትምህርተ ሥላሴንም ሆነ የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ ሰዎች፣ ኢየሱስ በቀጥታ፣ “እኔ አምላክ ነኝ”፣ “እኔ የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነኝ” ወዘተ እስካላለ ድረስ፣ አምላክነቱን መቀበል ያዳግተናል የሚሉ ከሆነ፣ ከእዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የአመክንዮ አካሄድ በመከተል፣ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል:— “እኔ አምላክ አይደለሁም፣ “እኔ የሥላሴ ሁለተኛ አካል አይደለሁም”፣ ብሎ ስላልተናገረ አምላክነቱንም ሆነ የሥላሴ አካል መሆኑን ሰዎች ሊቀበሉ ይገባል ማለት ይቻላልን? በሁለቱም በኲል ይህ የሙግት አካሄድ ስሕተት ነው፡፡ ከዚህ የምንማረው እውነት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ አምላክነት ወይም ስለ ትምህርተ ሥላሴ የሚያስተምሩት ትምህርት፣ የእኛን የዐረፍተ ነገር አካሄድ ወይም የትንታኔ ዘዬ በተከተለ መልኩ እንዳልሆነ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በክርስቶስ አምላክነት ላይ እንወያይ የነበረ አንድ “የይሖዋ ምስክር”፣ “እኔ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ” ብሎ ስላልተናገረ አምላክ አይደለም አለኝ፡፡ እኔም “ከዚህ ንግግርህ የተረዳሁት፣ አንድ ትምህርት ትክክል ነው ብለህ የምታምነው፣ ትምህርቱ ቃል በቃል አንተ በምትፈልገው መልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ሲገኝ ብቻ ነው ማለት ነው?” ስል ጥያቄ አቀረብሁለት፡፡ እርሱም በሙሉ ልብ ቈፍጠን ብሎ፣ “እንዴታ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኒ እንደ መሆኔ መጠን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ያልነገረኝን ነገር አላምንም” አለ፡፡ እኔም፣ “እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢየሱስ ሊቀ መልአክ ሚካኤል ነው’ ወይም ‘ኢየሱስ አምላክ ለሥራ ሲነሣሣ በመጀመሪያ የፈጠረው ፍጡር ነው’ የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሳየኝ” አልሁት፤ እርሱም ጥቂት ካሰበ በኋላ፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል፣ ‘ኢየሱስ ሚካኤል ነው’ ባይልም፣ ይህ ዐይነቱ ዐሳብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ” አለኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል፣ “ኢየሱስ ሊቀ መልአክ ሚካኤል ነው” ወይም “ኢየሱስ አምላክ ለሥራ ሲነሣሣ በመጀመሪያ የፈጠረው ፍጡር ነው” በማይልበት ሁኔታ፣ “ይህ ዐይነት ዐሳብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ” በሚል፣ “ኢየሱስ ሊቀ መልአክ ሚካኤል ነው”፣ ብለህ የምታምን ከሆነ፣ “ቃል በቃል ካልተጠቀሰ አላምንም” የሚለው አቋምህ ከዚህ ዐሳብ ጋር እንዴት ታስታርቀዋለህ አልሁት፡፡

              በተመሳሳይ መንገድ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” ተከታዮች፣ “የኢየሱስ ሥጋ ከሰማይ የመጣ ነው”፣ “ኢየሱስ የአብ ሥጋ ነው”፣ “አብ የኢየሱስ ነፍስ ነው”፣ “ኢየሱስና አብ አንድ አካል ናቸው” ወዘተ የሚል አቋም አላቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ቃል በቃል እንደዚያ አይልም፡፡ ልብ ልንልው የሚገባን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ዐሳብ ቃል በቃል እኛ በምንፈልገው መልክ አልተናገረውም (አላቀረበውም) ማለት፣ ከዚህ ተቃራኒው ዐሳብ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ “መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ለምን እንዲህ አላለም?” የሚለውን ዐስተሳሰብ ማስወገድ አለብን፤ ምክንዮአዊ ዐስተሳሰብ አይደለምና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሊል የፈለገውን ነገር በራሱ መንገድ እንዲል መፍቀድ አለብን፡፡ ባይሆን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አማኒ፣ “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህና እንዲያ ሲል ምን ማለቱ ነው?” የሚለውን ጒዳይ መጠየቅና መመርመር፣ የሚለውንም ማመን ይጠበቅብናል፡፡

              “የኦንሊ ጂሰሰ” ጸሓፊዎች ኢየሱስ አምላክ ነው ይላሉ፡፡ በአንጻሩ በአብ ላይ የተለጠፈ ሥጋ ነው ይላሉ፡፡ እንግዲያው ኢየሱስ የአብ የሥጋ ክፍል ነው ወይስ እርሱ ራሱ አምላክ ነው የሚለው ጒዳይ በትክክል መወሰን አለበት፡፡      

              ሁለተኛ፤ ይህን ሙግት በተመለከተ ልብ ልንለው የሚገባን ሌላም ነጥብ አለ፡፡ የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደ ሆነ በግልጽ የሚያስተምሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት የተለየ ትንታኔ ይሰጧቸዋል፡፡ ለምሳሌ:— “የይሖዋ ምስክሮች” ዮሐንስ 1÷1፤ 1÷18፤ 20÷28 ላይ ኢየሱስ በግልጽ፣ “አምላክ” እንደ ተባለ የሚቀበሉ ቢሆንም[5]፣ “አምላክ መባሉ አምላክ መሆኑን የሚያስተምር ሳይሆን፣ የአምላክ እንደ ራሴ (ወኪል) መሆኑን የሚያሳይ ነው” የሚል ትንታኔ ያቀርቡለታል፡፡ አብና ወልድ እየተነጋገሩ እንዲሁም ሰዎች እየሰሟቸው የኦንሊ ጂሰስ ቀሳውስት አንድ አካል ናቸው፡፡ አንዱ አካል ራሱን እያናገረ ነው ይሉናል፡፡ ከዚህ የምንማረው እውነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀጥታ/ቃል በቃል፣ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ”፣ “እኔ የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነኝ” ቢል እንኳ፣ ለዚህ አነጋገሩ የተለየ ትንታኔ በመስጠት፣ “‘ኢየሱስ፣ እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ’ ማለቱ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ለማለት ተፈልጎ ሳይሆን ወይም የሥላሴ ሁለተኛ አካል መሆኑን ለማስተማር ሳይሆን፣ በውክልና ደረጃ አምላክ ተብሎ መሰየሙን ለማስረዳት ነው” የሚል ወይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ትንታኔ ይቀርብለት እንደ ነበር መገመት አዳጋች አይሆንም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል፣ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ”፤ “እኔ የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነኝ” ቢልም ንግግሩ የትርጓሜ አማራጭ አይበጅለትም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ከዚህ የምንማረው ጒዳይ አንድ ነገር እኛ በምንፈልገው መልኩ በቀጥታ መጠቀሱም ሆነ አለመጠቀሱ፣ በርእሰ ጒዳዩ ላይ ያለውን ክርክር የሚያስወግድ አይሆንም[6]፡፡

              ሦስተኛው ነጥብ በወንጌላት የምንማረው ትምህርት የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ቀዳማይ ተልእኮ አብን መግለጥ፣ አብን ማክበር እንዲሁም ሰዎችን ከአብ ጋር መስታረቅ ነው (ለምሳሌ:— የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል፡፡ ማቴዎስ 11÷27፤ ዮሐንስ 14÷6፤ 17÷4)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም የኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳማይ ተልእኮ ራሱን እንደ ባርያ ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔርን ማስከበር እንጂ፣ ራሱን ከፍ ማድረግ አይደለም (ፊልጵስዩስ 2÷6-7 ጳውሎ ይህን ንግግር የተናገረው ክርስቲያኖች እርስ በርስ መከባበር እንዳለባቸው ባስተማረበት ዐውድ ነው)፡፡ ይህ ማለት ግን “ኦንሊ ጂሰሶች” እንደሚሉት በአብ ላይ የተለጠፈ ሥጋ ነው ማለት አይደለም፡፡  ኢየሱስ ክርስቶስ በቀጥታ አምላክ ነኝ ቢል ኖሮ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ አይሁድ ጒዳዩን እንደ ትልቅ ዕብደት ይቈጥሩት ነበር፡፡ ስለዚህ ማንነቱን አለዝቦ ደቀ መዛሙርት በሂደት የክርስቶስን ግብር፣ ሕይወትና ትምህርት በመመልከት ወደዚህ ድምዳሜ እንዲደርሱ እንደ ፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

              አራተኛው ነጥብ ቅዱሳት መጻሕፍት “ኦንሊ ጂሰሶች” እንደሚሉት የአብ ሥጋ አይደለም፡፡ ወይም “የይሖዋ ምስክሮች” እንደሚሉት፣ ሊቀ መልአክ ሚካኤል አይደለም፡፡ ኢየሱስ ራሱን ሁሉን ቻይ አምላክ አድርጎ ያቀረበባቸው በርካታ የዐዲስ ኪዳን ምንባባት አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን እንመልከት—

ሀ. ኢየሱስ አምላካዊ ክብር አለው

ኢየሱስ ሰዎች አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ እርሱንም እንዲያከብሩ አስተምሮአል (ዮሐንስ 5÷23)፡፡ ሃይማኖታዊ ስግደትን በሚያመለክትበት ዐውድ ውስጥ፣ ኢየሱስ አምላካዊ ስግደት ተቀብሎአል (ማቴዎስ 14÷33፤ 28÷17)፡፡ አበረታትቶአል (ማቴዎስ 9÷28፤ ዮሐንስ 14÷1)፡፡ ኢየሱስ ሰዎች ከሥጋ ዘመዶቻቸው ይልቅ እርሱን መውደድ እንዳለባቸው አስተምሮአል (ማቴዎስ 10÷37፤ ሉቃስ 14÷26፤ ዮሐንስ 14÷15:21፤ 15÷10)፡፡

ለ. ኢየሱስ አምላካዊ ባሕርይ አለው

ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ስለሆነ እርሱን ማየት ማለት አባቱን እንደ ማየት እንደ ሆነ ተናግሮአል (ዮሐንስ 14÷7-10)፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ እንደሚገኝ (አኀዜ/መላኤ ኲሉ) እንደ ሆነ ተናግሮአል (ማቴዎስ 18÷20፤ እንዲሁም የሚከተለውን ክፍል ይመለከቷል ማቴዎስ 28÷20)፡፡ ኢየሱስ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት እንደ ነበር ተናግሮአል፡፡ ይህ ደግሞ ጅማሮ የሌለው፣ ዘላለማዊ የሆነ አምላክ እንደ ሆነ የሚያስተምር ነው (ዮሐንስ 8÷58-59፤ 17÷5)፡፡ በብሉይ ኪዳን ያህዌ “እኔ እኔ ነኝ” እንዳለው ሁሉ ኢየሱስም “እኔ እኔ ነኝ” ብሎአል (ዮሐንስ 4÷26፤ 6÷20፤ 8÷24:28:58፤ 13÷18-19፤ 18÷5-8፤ ከሚከተሉት ክፍሎች ጋር ያነጻጽሩ ዘዳግም 32÷39፤ ኢሳይያስ 41÷4፤ 43÷2:5:10-11:25፤ 46÷4፤ 52÷6)፡፡

ሐ. ኢየሱስ አምላካዊ ግብር አለው

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተፈጥሮ ሕግጋት ሁሉ በላይ እንደ ሆነ ተናግሮአል፡፡ ይህ ደግሞ በብሉያት አብ የተፈጥሮ ሕግጋት ጌታ የሆነበትን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው (ለምሳሌ የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል ማቴዎስ 8÷23-27፤ 14÷13-33፤ ከሚከተሉት ክፍሎች ጋር ያነጻጽሯል መዝሙር 77÷16-20፤ 104÷4-9፤ 107÷23-30)፡፡ ልክ እንደ አብ ሥልጣናዊ ቃል ይናገራል፡፡ እንደ ነቢያት “የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ሳይሆን፣ “እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ” የሚለውን ንግግር ብሉያት ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር በማነጻጸር ተናግሮአል (ለምሳሌ:— ማቴዎስ 5÷18:26፤ ማርቆስ 3÷28፤ ሉቃስ 4÷24፤ ዮሐንስ 1÷51)፡፡ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር እንደሚል አስተምሮአል (ማቴዎስ 9÷1-8፤ ማርቆስ 2÷1-12፤ ሉቃስ 5÷17-26)፡፡ ለሙታን ሕይወት እንደሚሰጥ ተናግሮአል (ዮሐንስ 5÷21-26)፡፡ በመጨረሻም በሰዎች ዕጣ ፈንታ ላይ ሁሉ ይፈርዳል (ማቴዎስ 16÷27፤ 25÷31-46፤ ዮሐንስ 5÷22-23)፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከሰማይ የመላክ ሥልጣን እንዳለው ተናግሮአል (ዮሐንስ 15÷26፤ 16÷7-14)፡፡

መ. ኢየሱስ አምላካዊ መንበር አለው

ኢየሱስ በጽንፈ ዓለሙ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው (ማቴዎስ 28÷18)፡፡ ስለዚህም በአምላክ ሉዓላዊ ዙፋን ላይ መቀመጥ ይችላል (ማቴዎስ 25÷31፤ ማርቆስ 12÷36፤ ሉቃስ 20÷42-43)፡፡ በሁሉ ላይ የበላይ ባለ ሥልጣን ነው (ማቴዎስ 11÷25-27፤ ሉቃስ 10÷21-22፤  ዮሐንስ 3÷35፤ 13÷3፤ 16÷15)፡፡ ከዚህም የተነሣ የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ምግባሩና ንግግሩ ራሱን ከአምላክ ጋር የሚያስተካክል ነው በሚል የከሰሱት (ማቴዎስ 9÷3፤ ማርቆስ 2÷7፤ 14÷61-64፤ ዮሐንስ 5÷17-18፤ 8÷58-59፤ 10÷27-33፤ 19÷7)፡፡ ኢየሱስ ራሱን እንኳ የማስነሣት ችሎታ እንዳለው አስተምሮአል (ዮሐንስ 2÷19-22፤ 10÷17-18)፡፡

ሠ. ኢየሱስ አምላካዊ ስም አለው

ቶማስ፣ ኢየሱስን  “ጌታዬና አምላኬ” (ዮሐንስ 20÷28) ማለቱ፣ ኢየሱስ አንተ የትንሣኤ ጌታ መሆኔን ስላየህ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ምስጉኖች ናቸው ሲል የሰጠው ምላሽ፣ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን አምላኬና ጌታዬ ብለው እንዲያምኑት የሚያሳስብ ነው (ኢየሱስን፣ “አምላክ” የሚሉ የሚከተሉትን ክፍሎች ይመለከቷል ዮሐንስ 1÷1:18፤ ሮሜ 9÷5፤ 1ዮሐንስ 5÷20-21፤ ዕብራውያን 1÷8፤ ሐዋርያት ሥራ 20÷28፤ ቲቶ 2÷13፤ 2ጴጥሮስ 1÷1)፡፡

              ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ፣ የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ፣ ስግደትና አምልኮ የሚገባው፣ ሁሉን የሚችል፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ፣ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምር ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ቶማስ፣ “አምላኬና ጌታዬ” ብዬ ማመኔ መጽሐፍ ቅዱስን የተከተለ አምልኮ የማይሆንበት ምክንያቱ ምንድን ነው?

ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ፣ ኢየሱስ ሊቀ መላእክት ሚካኤል የሚሉት፣  “የይሖዋ ምስክሮችም” ሆኑ ኢየሱስ በአብ ላይ የተለጠፈ ሥጋ ነው የሚሉት፣ “ኦንሊ ጂሰሶች” ትልቅ ስሕተት ውስጥ ናቸው፡፡

፯.“መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ህልውና ካለው፣ ሰላምታ ውስጥ ለምን አልተካተተም?”

              በሐዋርያው ጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ፣ ሐዋርያው በሰላምታው ውስጥ አብና ወልድን ሲጠቅስ መንፈስ ቅዱስን አልጠቀሰም፣ “ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ሮሜ 1÷7)፡፡ አብና ወልድ የተለያዩ አካላት እንደ ሆኑ ሁሉ፣ መንፈስ ቅዱስም የራሱ ማንነት ያለው አካል ቢሆን ኖሮ፣ በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ ሊጠቀስ ይገባ ነበር፡፡ ኢየሱስ፣ “ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም” (ማቴዎስ 11÷27) በሚለው ንግግሩ ውስጥ፣ መንፈስ ቅዱስን አላካተተም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ ህልውና ያለው አምላክ ቢሆን ኖሮ አብና ወልድን እንደሚያውቅ፣ አብና ወልድም መንፈስ ቅዱስን እንደሚያውቁ መጠቀስ ነበረበት፡፡ ኢየሱስ፣ “ነገር ግን ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም” (ማርቆስ 13÷32) በሚለው ንግግሩ ውስጥ፣ “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በስተቀር” የሚለውን ንግግር መናገር ነበረበት፡፡ የዐዲስ ኪዳን ቅዱሳን በራእያቸው ውስጥ አብና ወልድን እንጂ፣ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተመለከቱ አንዳችም ጊዜ አልተጠቀሰም (ሐዋርያት ሥራ 7÷55-56)፡፡

              ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ ቀዳማይ መሪነት እንደ ተጻፉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል (1ጴጥሮስ 1፥21)፡፡ እንዲሁም የሥላሴ አካላት አንዱ የሌላውን ክብር እንደሚሻና መንፈስ ቅዱስም የአብንና የወልድን ክብር እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል፣ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡ እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል” (ዮሐንስ 16÷13-14)፡፡ ከእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች የምንማረው ቍም ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ ከሆነ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ አብና ወልድን ማክበር እንጂ፣ ራሱን ከፍ ማድረግ ዐላማው ካልሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ቀዳማይ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት አብና ወልድን ማክበር ቀዳማይ ዐላማቸው ቢሆን ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ ከላይ ቤተሰቤን ፎቶ ስለማንሣት የተናገርሁትን ምሳሌ ልብ ይሏል፡፡ 

              ካልተጠቀሰ የለም የሚለውን የሙግት አካሄድ፣ የሥነ አመክንዮ ምሁራን፣ “argument from silence”[7] በማለት የሚጠሩት ስሑት ሙግት ነው፡፡ ይህ ሙግት፣ “መኖሩ ካልተጠቀሰ የለም ማለት ነው” በሚለው ልክፍት የተለከፈ ነው፡፡ ጸሓፊው ወይም ተናጋሪው ይጠቀስ የተባለውን አካል ወይም ርእሰ ጒዳይ ያለ መጥቀሱ ብዙ አማራጭ ምክንያቶች ሊቀርቡለት ይችላል፡፡ ለምሳሌ:— (1) ጸሓፊው ከሚጽፍበት ዐላማ አንጻር መጥቀስ የሚፈልገውን ብቻ መጥቀሱ “ያልጠቀሰው ነገር ሁሉ የለም” ወደሚለው ድምዳሜ መሄድ የለበትም፡፡ (2) ጸሓፊውም ሆነ ተናጋሪው አንድን ነገር የሚነግሩን በጒዳዩ ላይ ካላቸው መረዳት አንጻር ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ (3) ጸሓፊው ወይም ተናጋሪው ጒዳዩን ቀዳማይ ተደራስያኑ ወይም የንግግሩ አድማጮች ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ስለዚህም ጒዳዩን መጥቀሴ አስፈላጊ አይደለም ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ጒዳዩ ያለመጠቀሱ ይህንና ይህን መሰል በርካታ አማራጭ ዐሳቦች በሚቀርቡለት ሁኔታ “ያለመጠቀሱ ያለመኖሩን የሚያሳይ ነው” ማለት ስሕተት ነው፡፡

              ይህ ዐይነቱ የሙግት አካሄድ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ሆነ፣ ነገረ መለኮትን በምናጠናባቸው ጊዜያት አብዝተው የሚያጋጥሙን ችግሮች ናቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ድንግል ስለመፀነሷ አንዳችም ጊዜ አልተናገረም፤ ይህ ማለት ድንግል መፀነሷን አያምንም ነበር ወይም አያውቅም ነበር ማለት አይደለም፡፡ ዮሐንስ ወንጌል 20÷1 መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ስፍራ እንደሄደች ሲገልጽ፣ ማርቆስ 16÷1 ደግሞ፣ “መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ” ዐብረው እንደ ሄዱ ገልጾአል፡፡ ማቴዎስ 28÷1 ደግሞ፣ “መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛዪቱ ማርያም” ወደ መቃብር እንደ ሄዱ ገልጾአል፡፡ ዮሐንስ ያልነገረንን ጒዳይ ማርቆስና (የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ) ማቴዎስ (ሁለተኛዪቱ ማርያም) መንገራቸው ክፍሎቹ ተደጋጋፊ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ዮሐንስ መግደላዊት ማርያምን ብቻ መጥቀሱ፣ ሌሎቹ ሰዎች የሉም ማለቱ አይደለም፡፡ ዮሐንስ በመልእክቱ ውስጥ ያልነገረንን ነገር ሌሎቹ የወንጌል ጸሓፊዎች ነግረውናል፡፡ ዮሐንስ ያለመናገሩ ጒዳዩን አያውቀውም ወይም ጒዳዩ የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን የነበረው ስመ ጥሩ አይሁዳዊ የታሪክ ጸሓፊ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን (Josephus) በጽሑፎቹ ውስጥ ሁሉ አንድም ጊዜ እንኳን ናዝሬትን አልጠቀሰም፡፡ ይህ ማለት ናዝሬት እርሱ በነበረበት ዘመን አልነበረችም ማለት አይደለም፡፡

              በርካታ የዐዲስ ኪዳን ምንባባት አብና ወልድን የጠቀሱትን ያህል፣ ከብዛት አንጻር መንፈስ ቅዱስን ጠቅሰው ያለመገኘታቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ የሚባል አካል የለም ማለት አይደለም፡፡

              ሐዋርያው ጳውሎስ በሰላምታው ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ባይጠቅስም ሐዋርያው ጴጥሮስ በሰላምታው ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ከአብና ከወልድ ጋር አያይዞ ጠቅሶአል፣ “እግዚአብሔር አብ  አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ” (1ጴጥሮስ 1÷2)፡፡ ይህ ጳውሎስ በሰላምታ ውስጥ ያልጠቀሰውን ነገር ጴጥሮስ ጠቅሶ መገኘቱ፣ ጳውሎስ ያለመጥቀሱ ሌላ ትንታኔ የሚቀርብለት እንጂ፣ ያለመኖሩን የሚያሳይ ነው ብሎ ድምዳሜ መስጠት ስሕተት ነው፡፡ ለምን አልተጠቀሰም ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ የሆነ መልስ ስላልሰጠን፣ መልስ ናቸው የምንላቸው ሁሉ ከግምት የሚያልፉ አይሆንም፡፡ ማወቅ ያለብን መሠረታዊው ነጥብ ግን ያለመጠቀስ ላለመኖሩ ማስረጃ አይደለም፡፡

              አንዳንድ ምሁራን መንፈስ ቅዱስ ለምን አልተጠቀሰም ለሚለው ጒዳይ፣ “የአብና ወልድን ሰላምታ በአማኙ ልብ ውስጥ የሚያፈሰው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ እንዲሁም አማኞች በውስጣቸው በሚሠራው ሥራ መንፈስ ቅዱስን ስለሚያውቁት ነው” የሚል አስተያየት አላቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ጳውሎስ በሰላምታው ውስጥ አብና ወልድን ብቻ መጥቀሱ፣ ሐዋርያው በመልእክቶቹ ውስጥ ሊያንሸራሽራቸው የሚገቡ ዐሳቦችን ለማስተላለፍ አብና ወልድን ብቻ መጥቀሱ በቂ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ አስተያየቶች ምን ያህል አጥጋቢ ናቸው የሚለው ጒዳይ ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም፣ በርግጠኝነት የምንረዳው ጒዳይ፣ “ያለመጠቀስ ያለመኖርን የሚያመለክት እንዳልሆነ” ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጳውሎስ ሰላምታ የመንፈስ ቅዱስን ያለመኖር የሚያስተምር አይደለም፡፡

              “ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር አብና ስለ ራሱ ባስተማረባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማስተማር ነበረበት” የሚል አስተያየት ስላላቸው፣ አንባብያን ሁለት ጒዳዮችን ልብ እንዲሉ ያስፈልጋል:—

  • ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለ መንፈስ ቅዱስ በግልጽ መረዳት የሚችሉት በበዓለ ኀምሳ ቀን ወደ ሕይወታቸው መጥቶ በውስጣቸው መኖር በሚጀምርበት ጊዜ ነው የሚል አስተሳሰብ እንደ ነበረው ከወንጌላቱ ትምህርት መረዳት ይቻላል፡፡ ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ በስፋት የተናገረው ታልፎ በሚሰጥበት ሌሊት ነው (ዮሐንስ 14÷16)፡፡ በዚሁ ዐውድ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርት እርሱ የሚለውን ነገር ሁሉ በግልጽ መረዳት የሚችሉት፣ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ አብሮአቸው መኖር ሲጀምር እንደ ሆነ ገልጾአል (ዮሐንስ 14÷25-26፤ 16÷13-14)፡፡ ይህ ጒዳይ ስለ መንፈስ ቅዱስ መረዳት የሚቻለው እርሱ ሲመጣና ማንነቱን ለሐዋርያቱ ግልጥልጥ አድርጎ ሲናገራቸው ብቻ እንደ ሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ወልድን የሚያውቀው አብ ብቻ ነው” (ማቴዎስ 11÷27) ለምን አለ የሚለው ጒዳይ መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ በፊት መንፈስ ቅዱስን የማያውቁ ከሆነ፣ “ወልድን የሚያውቁት አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው” የሚል ንግግር በዚህ ዐውድ ውስጥ ሊያስገባ ይችላልን? ልክ እንደዚሁ ሁሉ፣ “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም” (ማርቆስ 13÷32) በሚለው ቦታ መንፈስ ቅዱስን ቢያካትት ኖሮ አድማጩን ከማደናገር ውጪ ንግግሩ በአድማጮቹ ዘንድ አንዳችም እርባና ሊኖረው አይችልም፡፡
  • “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም” (ማርቆስ 13÷32) በሚለው ምንባብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ነገሩን ግልጽ የሚያደርገው ከሆነ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ የአንድ ድርጅት አስተዳዳሪ የሆኑ ሰው፣ ለድርጅቱ ምክትል አስተዳዳሪ፣ “በፊታችን ባሉት ሳምንታት ሥራዬን ለመልቀቅ ወስኛለሁ፤ ይህን ምስጢር ማንም ሰው አያውቅም፤ አንተም ለማንም እንዳትናገር” ቢሉ፣ “ይህን ምስጢር ማንም ሰው አያውቅም” የሚለው አነጋገራቸው የመሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንጂ፣ የግለሰቡን ሚስት እንዲሁም ቤተሰብ ስለ ጒዳዩ አንዳችም ዕውቀት የላቸውም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ መስማት ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ያልሰሙትን ሰዎች እንጂ፣ መስማት ካለባቸው ሰዎች መኻል የሰሙትን ሰዎች የሚያካትት አይደለም፡፡ ግለሰቡ “ባለቤቴ፣ ልጄና በአሜሪካ አገር ያለው ታላቅ ወንድሜ በስተቀር” ወዘተ ማለት አያስፈልጋቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ስላልሆኑ፣ የመሥሪያ ቤቱ ዐውድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ በማቴዎስ 11÷27 እና በማርቆስ 13÷32 ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ መጥቀስ አንዳችም ጠቀሜታ የለውም፡፡

“በራእይ እግዚአብሔርን የተመለከቱ ሰዎች፣ ኢየሱስንና አብን እንጂ፣ መንፈስ ቅዱስን አልተመለከቱም፤ ይህም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የተለየ አካል እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው” የሚለውን ስሑት የሙግት አካሄድ የተከተለ ነው፡፡ ዮሐንስ በራእዩ መጀመሪያ የተመለከተው ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እንደ ሆነ ተጠቅሶአል (ራእይ 1÷13-18)፡፡

የሥላሴ ተቃዋሚዎች መንፈስ ቅዱስ ስላልተጠቀሰ የለም የሚሉ ከሆነ፣ አብም አልተጠቀሰምና የለም ማለት ነውን? መጽሐፉ አቡቀለምሲሳዊ እንደ መሆኑ መጠን ትእምርታዊ ገለጻዎች ይበዙበታል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ በግ ተመስሎ የታየ ሲሆን (ራእይ 5÷6)፣ አብ ደግሞ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ንጉሥ ሆኖ ቀርቧል (ራእይ 4÷2: 9:10 ወዘተ)፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በትእምርታዊ ገለጻ፣ “በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት” (ራእይ 1÷4) እንዲሁም “ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት” (ራእይ 3÷1፤ 4÷5፤ 5÷6) ተብሎ ቀርቧል፡፡ “ሰባት መናፍስት” የሚለውን ሐረግ ቃል በቃል በመተርጐም፣ ሰባት መናፍስት አሉ ማለት ስሕተት እንደ ሆነው ሁሉ፣ ኢየሱስንም ቃል በቃል አራት እግር ያለው በግ የሚባለው እንሰሳ ነው ማለት ስሕተት ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ሰባት ቍጥር ፍጽምናን ሙሉዕነትን የሚያመለክት እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡ ይህም የመንፈስ ልዕልናን አመልካች ነው፡፡ ኢየሱስ በበግ መመሰሉ ለሰው ልጆች ኀጢአት የከፈለውን የትኪ ሞት የሚያመለክት ነው፡፡ “ካልተጠቀሰ የለም” የሚለውን ስሑት የሥነ አመክንዮ አካሄድ ካስወገድን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምሩን እጅግ በርካታ ትምህርቶች አሉ፡፡

፰. “የሥላሴ አስተምህሮ ለድነት ወሳኝ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያብራራው ነበር”

              “የሥላሴ አስተምህሮ የድነት ቅድመ ሁኔታ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮውን ግልጽ በሆነና በማያሻማ መንገድ ያቀርበው ነበር” የሚለውን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች አስተምህሮው ግልጽ የሚሆነው በምን መልኩ ሲቀርብ ነው ተብለው ሲጠየቁ፣ አብዛኞቹ የሚያቀርቧቸው አማራጮች መኻል የሚከተሉት ይገኙበታል፣ “እግዚአብሔር ሥላሴ ነው”፣ “እግዚአብሔር በባሕርይ አንድ፣ በአካል ደግሞ ሦስት ነው”፣ “አብ አምላክ እንደሆነ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስም አምላክ ናቸው”፡፡ በዚህ መልክ በማያሻማ መልኩ ስላልቀረበ ትምህርተ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው ማለት አይቻልም ባዮች ናቸው፡፡

              በመሠረቱ ድነት በነገረ መለኮት ትምህርት በምናገኘው ውጤት የሚወሰን ጒዳይ አይደለም፡፡ ሃምሳ ከመቶ ያገኙ ሰዎች ዘጠና ከመቶ ካገኙ ሰዎች ይልቅ ድነታቸው አደጋ ላይ ነው፤ ወይም ሠላሳ ከመቶ ያገኙ ሰዎች ድነት አላገኙም ማለት በፍጹም አይቻልም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የነገረ መለኮት ፈተና መውሰድ፣ በዚያም የማለፊያ ነጥብ ማግኘት ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡ ማዳን የእግዚአብሔር ድርሻ፣ የሚያድንም እምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኝ ነው (ሮሜ 3÷21-26፤ ኤፌሶን 2÷8-10፤ ቲቶ 3÷5-8)፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የሚያድን እምነት ዘወትር ርቱዕ አስተምህሮን የተከተለ ነው፡፡ በክርስትና የድነት አስተምህሮ ውስጥ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የድነት ሥራ የማያምኑ ሰዎች ድነት ማግኘት አይችሉም የሚለው ትምህርት፣ ድነት ትክክለኛ አስተምህሮን በቅድመ ሁኔታ ውስጥ ያካተተ ጒዳይ ስለሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዐበይት በሚባሉ ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች ላይ የተሳሳተ አቋም ያላቸው ሰዎች ከድነት እንደሚጐድሉ ቃለ እግዚአብሔር በግልጽ ያስተምራል (ሮሜ 16÷17-18)፡፡ እንዲሁም በደቂቃን (በንዑሳን) ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ላይ የተሳሳተ ምልከታ ያላቸው ሰዎች የበሰለ የክርስቲያናዊ ሕይወት ሊኖሩ አይችሉም (ሐዋርያት ሥራ 18÷25-26)፡፡

              መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረገ መልኩ፣ ክርስቲያኖች ስለ ትምህርተ ሥላሴ ማወቅ ያለባቸው መሠረተ እምነት የቱ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሥላሴ”፣ “ሦስት አካላት አንድ አምላክ”፣ ወዘተ የሚሉትን ቃላት አይጠቀምም፡፡ እነዚህ የነገረ መለኮት ቃላት እንጂ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አይደሉም፡፡ አንድ ሰው እነዚህንም ቃላት መጠቀም አልፈልግም ካለ ያለመጠቀም ሙሉ መብት አለው፡፡ ነገረ መለኮታውያን እነዚህን ቃላት የቀመሩት አስተምህሮአቸውን በግልጽ ለማብራራት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ቃላት ያለመቀበል ይቻላል፤ ነገር ግን እነዚህ ቃላት የወከሉትን ፅንሰ ዐሳብ ክዶ የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ የደቀ መዝሙር ሕይወትም ራስን ለሥላሴ ማለትም ለአብ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በማስገዛት የሚጀምር ሕይወት ነውና (ማቴዎስ 28÷19)፡፡ አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም የሚል እምነት ካለው፣ ከክርስቶስ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ማድረግ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደ ሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁ” (ዮሐንስ 8÷24) ያለው፡፡

              ይህ ክፍል የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ማወቅ የድነት ቅድመ ሁኔታ እንደ ሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮ ድነት የሚያገኙ ክርስቲያኖች አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንደ ሆነ ማመን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟሉ ክርስቲያኖች አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው የሚለው ትምህርት በሦስት አማልክት ማመን እንዳልሆነ ወይም አንዱ አምላክ ራሱን በሦስት ገጽ (መልክ) የገለጸ አምላክ እንዳልሆነ ቢያውቁም፣ መጽሐፍ ቅዱስንና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በማጣቀስ አስተምህሮውን የማብራራት ዐቅም ላይኖራቸው ይችላል፡፡  

              እነዚህ ክርስቲያኖች፣ አስተምህሮውን ለአእምሮ ግቡዕ በሆነ መልኩ አላብራሩም ማለት፣ አስተምህሮውን አያምኑም ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት በትክክል የተረዱ ሰዎች፣ አስተምህሮውን ለአእምሮ ግቡዕ በሆነ መልኩ ለማብራራት የቤተ ክርስቲያን ታሪክንና በተወሰነ ደረጃ የሥነ አመክንዮን አካሄድ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይህን አስተምህሮ ለማብራራት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያደረጉትን ጥረት ማወቅ፣ ከእነዚህ አባቶች መኻል አስተምህሮውን ጥሩ በሆነ መልኩ ያብራሩትን ሰዎች አካሄድ በትክክል ማወቅ፣ አስተምህሮውን በትክክል ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል፡፡

              አብዛኞቹ ምናልባትም ሁሉም መናፍቃዊ ትምህርቶች በአስተምህሮተ ሥላሴ ላይ የተዛባ አተያይ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው የነገረ መለኮት ምሁራን፣ “ትምህርተ ሥላሴ በመናፍቃንና በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆመ የመለያ ሰንደቅ ነው” የሚሉት፡፡ በአጠቃላይ እንደ ሥላሴ ያሉ ዐበይት ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችን መካድ፣ የዘላለም ዕድል ፈንታችንን ሊወስን አለያም ክርስቲያናዊ ብስለታችንን ክፉኛ ሊያጨናግፍ ይችላል፡፡


[1] እነዚህን ሥሉሳውያን ምንባባት (Triadic Texts) ከላይ በሠንጠረዥ አቅርበናል፡፡ ሮሜ 5÷5-6፤ ይሁዳ 20-21፤ 2ተሰሎንቄ 2÷13-14፤ ሮሜ 15÷30፤ ዕብራውያን 2÷3-4፤ ሮሜ 8÷14-17፤ 1ተሰሎንቄ 1÷3-6፤ 2ቆሮንቶስ 13÷14፤ ማቴዎስ 28÷19፤ ሐዋርያት ሥራ 10÷44-48፤ 2÷38-39፤ 1ጴጥሮስ 4÷14፤ 1ዮሐንስ 3÷23-24፤ 1ቆሮንቶስ 6÷11፤ ኤፌሶን 1÷3-13፤ ሐዋርያት ሥራ 15÷8-11፤ ዕብራውያን 10÷29-31፤ ሮሜ 5÷5-6፤ ኤፌሶን 2÷19-22፤ 3÷16-17፤ 2ቆሮንቶስ 1÷21-22፤ ገላትያ 4÷4-6፤ ሐዋርያት ሥራ 2÷38-39፤ 10÷44-48፤ 15÷8-11፤ 20÷27-28፤ 28÷25-31፤ ሮሜ 1÷1-4፤ 5÷5-6፤ 8÷14-17፤ 8÷26-30፤ 15÷16፤ 15÷30፤ 1ቆሮንቶስ 2÷2-5፤ 6÷11፤ 12÷46፤ 12÷11-12:18፤ 2ቆሮንቶስ 1÷21-22፤ 13÷14፤ ኤፌሶን 1÷3- 13፤ 2÷18፤ 2÷19-22፤ 3÷16-17፤ 4÷4-6፤ 4÷3-32፤ 5÷18-20፤ 1ተሰሎንቄ 1÷3 -6፤ 2ተሰሎንቄ 2÷13-14፤ ቲቶ 3÷4-6፤ ዕብራውያን 2÷3-4፤ 9÷14፤ 10÷29-31፤ 1ጴጥሮስ 1÷2፤ 3÷18፤ 4÷14፤ 1ዮሐንስ 3÷23-24፤ 4÷13-14፤ ይሁዳ 20-21፡፡ 

[2] Presupposition የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል እንዲወክል የታሰበ ቃል ነው፡፡

[3] Insight on the Scriptures, “Entry for “SPIRIT.’” Volume 2, (Watchtower Bible and Tract Society of New York, Inc.  1989), 1019. 

[4] በቅዱሳት መጻሕፍት፣ ርኲሳን መናፍስት መንፈስ ተብለዋል፡፡ ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስን አካላዊ ህልውና የሚክዱ ሰዎችም እንኳ፣ እነዚህ መንፈሳውያን ፍጥረታት አካላዊ ህልውና እንዳላቸው ያምናሉ፡፡

[5] በቅርቡ ከአስተምህሮአቸው ጋር እንዲጣጣም በማሰብ፣ በአማርኛ ቋንቋ ተርጒመው ለንባብ ያቀረቡት የሐዲስ ኪዳን ቅጅ፣ በእነዚህ ክፍሎች ኢየሱስ አምላክ እንደ ተባለ ይህም ኢየሱስ ለአብ ያለውን ውክልና እንደሚያሳይ ይገልጻል፡፡

[6]  በአንድ ወቅት አብና ወልድ የተለያዩ አካላት ናቸው በሚለው ጒዳይ ላይ ሰዋስዋዊ ሙግት አቀረብሁ፡፡ ሙግቴ ከሞላ ጐደል የሚከተለውን ይመስላል:— ዮሐንስ 1÷1 ላይ፣ “ጋር” ወይም “ዘንድ” ተብሎ በዐማርኛ ቅጆች ላይ የተተረጐመው የግሪክ ቃል (“ፕሮስ” “πρὸς”)፣ በእንግሊዝኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጆች ላይ የተተረጐመው “with” ተብሎ ነው፡፡ በዐዲስ ኪዳን ግሪክ ሰዋስው፣ “ፕሮስ” (πρὸς) የሚለው ቃል በተሳቢ ሙያ (objective case) በሚቀደምበት ጊዜ መስተጋብርን (ግንኙነትን) ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ ወልድ በአብ ውስጥ ያለ ንግረተ ቃል ሳይሆን ወይም በአብ ላይ የተለጠፈ ሥጋ ሳይሆን፣ ከአብ ጋር ዐብሮ የሚኖር ማንነት ያለው አካል መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህ የትምህርት ፕሮግራም አዘውትሮ ወደ ጉባኤው ይመጣ የነበረ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” አባል፣ “ዮሐንስ 1÷1 ላይ አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ለመግለጽ ቢፈልግ ኖሮ፣ በዚህ ክፍል ‘ፕሮስ’ ‘πρὸς’ከሚለው የግሪክ ቃል ይልቅ ‘ፓራ’ (παρά) የሚለው መስተዋድድ ጥቅም ላይ ይውል ነበር” የሚል ሙግት አቀረበ፡፡ ሙግትህ መሆን ያለበት፣ “ፕሮስ” “πρὸς” ከሚለው ቃል ይልቅ፣ “ፓራ” “παρά” የሚለው ቃል በቦታው ላይ ተጠቅሶ ቢገኝ ይሻለኛል ሳይሆን፣ ተጠቅሶ የተገኘው ቃል (“ፕሮስ” “πρὸς”) በተሳቢ ሙያ ሲቀደም ግንኙነትን ያሳያል ወይስ አያሳይም የሚለው ጒዳይ ነው ለምርመራ መቅረብ ያለበት፡፡ ምክንያቱም “ከዚህ ቃል ይልቅ ይህ ቃል ቢጠቀስ ይሻለኛል” አለያ ግን ማስረጃውን አልቀበልም ማለት፣ “መጽሐፍ ቅዱስ እኔ በፈለግሁበት መንገድ ካልተጻፈ፣ ልቀበለው እቸገራለሁ” እንደ ማለት ነው፡፡

[7] argumentum ex silentio.

Share the Post:

Related Posts