ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ አበው

ሰባልዮሳውያን ነበሩ ወይስ ሥላሴአውያን?

ቅድ ጉባኤ ኒቂያ አበው

ሰባልዮሳውያን ነበሩ ወይስ ሥላሴአውያን?

ከትካችና ተቃራኒ ዐጸፋ

የዐባሪው ትልም

              ይህ ክፍል ከኒቂያ በፊትም ሆነ፣ ከኒቂያ በኋላ የነበሩ ዕውቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ሥላሴአዊ አስተምህሮ እንደ ነበራቸው ማሳየት፣ እነዚህ አባቶች ሰባልዮሳዊ ዐስተሳሰብ ነበራቸው የሚለውን የዘመኑን፣ “የኦንሊ ጂሰሰ” ጸሓፊዎች ክጃሎት መና ማስቀረት፣ የምዕራፉ ቀዳማይ ትልም (ዐላማ) ነው፡፡

ሀ. የታሪክ ሽሚያው ለምን አስፈለገ?

              በምድረ አሜሪካ የሚገኘው፣ “የተባበሩት ጴንጤቈስጣውያን ዓለም ዐቀፍ ቤተ ክርስቲያን”[1] የበላይ ጠባቂ እንዲሁም የቤተ እምነቱ አስተምህሮ ቊጥር አንድ ተሟጋች ዴቪድ ኬ. በርናርድ፣ “ዘ ዋንነስ ኦፍ ጎድ” እንዲሁም “ዋንነስ ኤንድ ትሪኒቲ” በሚል ርእስ በጻፏቸው ተከታታይ መጻሕፍት፣ ትምህርተ ሥላሴ በቃለ እግዚአብሔርም ሆነ በሥነ አመክንዮ አንዳችም መሠረት የሌለውም ከማለት ባሻገር፣ ትምህርተ ሥላሴን በጥሩ መንገድ ተንትነዋል የሚባሉትን፣ ከጉባኤ ኒቂያ በፊትም ሆነ በኋላ የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሁሉ፣ ሰባልዮሳዊ እምነትና አስተምህሮ እንዳላቸው ለማሳመን ብዙ ሲደክሙ ታይቶአል፡፡

              እንደ ዴቪድ ኬ. በርናርድ ሁሉ፣ “የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር” በመባል የሚታወቀው፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ድርጅት፣ ከኒቂያ በፊት የነበሩ አባቶች ሁሉ አርዮሳዊ እምነትና ዐስተሳሰብ ነበራቸው ባይ ነው፡፡ የሚገርመው ግን እነዚህ መናፍቃውያን ድርጅቶች ይህን ለማድረግ የተጠቀሙበት ዋነኛ መንገድ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚተረጒሙበት ሥልት ጋር አንድ ዐይነት ነው፡፡ አንድ የተወሰነ ክፍል እንዲህና እንዲያ ይላል የሚሉት፣ የክፍሉን ዐውደ ምንባብ በተከተለ ምንገድ አይደለም፡፡ አንድ ቃል ከወዲህ አንድ ቃል ከወዲያ፣ አንድ ሐረግ ከወዲህ አንድ ሐረግ ከወዲያ እየገጣጠሙ፣ የሚሹትን አድምቆ እንዲናገርላቸው ይጠመዝዙታል[2]፡፡

              ይህ ዐይነቱ ቈርጦ ቀጥል አሠራር የዚህን ዘመን ትውልድ ለማታለል ፋይዳው እንብዛም ነው፡፡ ከየትኛውም የታሪክ ጊዜ ይልቅ ይህ እኛ ያለንበት ዘመን፣ ትልልቅ የዕውቀት መድብሎችን (encyclopedia) እንዲሁም መጻሕፍትን በእጅ ስልካችን ጭምር የምናገኝበት፣ አስገራሚ የታሪክ ወቅት ነውና፡፡ ስለዚህ እውነታውን በትክክል መመርመር የሚፈልጉ ሰዎች፣ ከወዲህ ከወዲያ የተቀነጣጠቡትን ቃላትና ሐረጎች፣ ከዐውዳቸው አንጻር በማንበብ፣ እውነታውን አመራምሮ ማግኘት ይችላል፡፡ ይህ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ገብቶ መማር የሚፈልግ ወይም በተለየ ሙያ ጥልቅ ዕውቀት የሚሻ ጒዳይ አይደለም፡፡ ፍላጎትና ትጋት ብቻ ነገሩን አመራምሮ እውነታውን ገንዘብ ማድረግ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ኀልዮአዊ ሂኬተኝነትን[3] ካስወገድን፣ እውነታውን ማወቅ አስቸጋሪ አይደለም፡፡  

              ታሪክ የእኔን አስተምህሮ ይበልጥ ይደግፋል የሚለው ጒዳይ፣ ትልቅ ቊም ነገር ሆኖ ለምን ቀረበ?” የሚለውን ብርቱ ጥያቄ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ ከኒቂያ አባቶች በፊት የነበሩ፣ “ሐዋርያዊ አባቶች”[4] በቀጥታ የተማሩት ከጌታ ሐዋርያት እግር ሥር ነው ቢያንስ (አብዛኞቹ)፡፡ ከሐዋርያት አባቶች ሥር በቀጥታ የተማሩት ደግሞ፣ ቅድመ ኒቂያ አባቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ግለሰቦች ትምህርት በቀጥታ የሚጣቀሰው ከሐዋርያቱ አስተምህሮ ጋር ነው፡፡ የእነዚህ አባቶች ትምህርት ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ የጌታ ሐዋርያት ትምህርታቸው ምንድን ነበር የሚለውን ጒዳይ እንደሚመልስ መናፍቃን ገብቶአቸዋል፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርታቸው ምንድን ነበር የሚለው ጒዳይ ዋነኛ አርእስት ሆኖ የቀረበው በዚህ አግባብ ነው፡፡ ታሪክ በእኛ አንጻር ነው የተሰለፈው የሚለው ጒዳይ አጨቃጫቂ ሆኖ የቀረበው፣ በዚህ ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡ 

              ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ አምላክ ራሱን ያለምስክር የማይተው ከሆነ እንዲሁም በየዘመናቱ አምላክ የራሱ ሰዎች ካሉት፣ እነዚህ የአምላክ ሰዎች የትኞቹ ናቸው፤ መሠረተ እምነታቸውስ ምንድን ነው የሚለው ጒዳይ እጅግ ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡ ዘመነኞቹ አርዮሳውያንም ሆኑ ዘመነኞቹ ሰባልዮሳውያን  (“የይሖዋ ምስክሮች” እና “የኦንሊ ጂሰስ” ተከታዮች) ቢያንስ ታሪክ ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት አያውቃቸውም፡፡ ከአምስተኛው እስከ ዐሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መኖራቸውን የሚገልጽ፣ ተኣማኒ የሆነ አንድም የታሪክ ሰነድ የለም፡፡ እነዚህ መናፍቃን ይህን አፍጦ አግጦ የመጣ እውነት መቀበል በበዙ ያስቸግራቸዋል፡፡ ቢያንስ በታሪክ ሽሚያው ውስጥ ትርፍራፊ ቢተርፍልን፣ እርሱን ይዘን እንጮኻለን የሚለውን አካሄድ እየተከተሉ ያለ ይመስላል፡፡ ጨለማን ተገን ሊያደርጉ በሚፈልጉት አቅጣጫ፣ የብርሃን ጅረት መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ታሪክ በጭራሽ አያውቃቸውም፡፡ እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን ቀመር በ1776 ህልውናዋን ባገኘችው ዐዲሲቱ አገር አሜሪካ፣ የተቀፈቀፉ (የተጀመሩ) መናፍቃዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መናፍቃን ጨምሮ የኑፋቄዎች ሁሉ መገኛ፣ አሜሪካ ነች ቢባል፣ ግነትም እብለትም የሚሆን ይመስላችኋል?   

              “የይሖዋ ምስክሮችም” ሆኑ፣ “ኦንሊ ጂሰሶች”፣ ትምህርተ ሥላሴ የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት አይደለም በሚለው ይስማሙ እንጂ፣ ታሪክ ማንን ይደግፋል በሚለው ጒዳይ ላይ በእነርሱም መኻል ትልቅ ልዩነትና ጠብ አለ፡፡ “የይሖዋ ምስክሮች”፣ ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አርዮሳውያን ነበሩ ሲሉ፣ “ኦንሊ ጂሰሶቹ” ደግሞ፣ እነዚህ አባቶች ሰባልዮሳውያን ናቸው ይላሉ፡፡ ሥላሴአውያን ግን በጉባኤ ኒቂያ የተገኙት አባቶች፣ ከጌታ ሐዋርያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እምነት በቀጥታ የተቀበሉ፣ በበኲረ ጽሑፋቱ ቋንቋዎች ላይ እጅግ አስደናቂ ዕውቀት የነበራቸው፣ በቃልም ሆነ በምግባር አንቱ የተባሉ አባቶች ናቸው የሚል ጽኑ አቋም አለን፡፡ “ውጉዝ ከመአርዮስ ወውጉዝ ከመሰባልዮስ” የሚለውም አቋማቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው የሚል አቋም አለን፡፡ ከኒቂያ በኋላም ሆነ፣ ከኒቂያ በፊት የነበሩትን የታሪክ ድርሳናት እንዲሁም የእነዚህን አባቶች ጽሑፍ በተለያዩ ቋንቋዎች ተርጒመንና ጠርዘን ያቀረብነው፣ እኛው ሥላሴአውያን መሆናችን ይታወቅ[5]፡፡ አንድም መናፍቃዊ ድርጅት በዚህ ዐይነቱ ሥራ ውስጥ ተካፋይ ሆኖ አልታየም፤ ሊያደርገውም አይችልም፡፡ ራሱን በራሱ ዐንቈ መግደል ማን ይፈልጋል?   

              የታሪክ ሽሚያው ያስፈለገበት ሦስተኛ ምክንያት፣ “የሥላሴ ትምህርት መሠረቱን የጣለው ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ነው” የሚለው አሉባልታ በሰው ልብ ለማሳደር ስለሚሹ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ትኲረት፣ “የኦንሊ ጂሰስ” ኑፋቄ ስለሆነ፣ የአርዮሳውያኑን ጒዳይ አንመለከትም፡፡ ለኦንሊ ጂሰሶቹ መልስ የምንሰጠው በሁለት አቅጣጫ ነው፡፡ ይኸውም:— (1) የድርጅቱ ዕውቅ መምህራን ከአበው ጽሑፍ በቀጥታ ጠቅሰናቸውል የሚሏቸውን ማስረጃዎች ከዐውዳቸው አንጻር መመርመር፣ (2) በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተኣማኒና ነጻ መረጃ ናቸው የሚባሉትን ድርሳናት በቀጥታ በመጥቀስ፣ የታሪክን ውልቃት በታሪክ መዛግብት ወጌሻነት ማከም ነው፡፡

ለ. ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ አበው ሰባልዮሳዊ እምነት ነበራቸውን?

ዴቪድ ኬ በርናርድና ሰባልዮሳዊ ድርጅታቸው፣ ትምህርተ ሥላሴ ከአረማውያን ሃይማኖትና ፍልስፍና የተቀዳ ባዕድ ትምህርት ነው የሚል አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን፣ ጥንታውያኑ የቤተ ክርስቲያን አበው ሰባልዮሳዊ አቋም ነበራቸው ለማለት የሚያቀርቡት ሙግት ይህን ይመስላል:—

  • “በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ አንድም [ክርስቲያን] ጸሓፊ ሥላሴያዊ የሆነውን አስተምህሮ በትክክል አላስተማረም፤ እንዲያውም አንዱ መለኮታዊ አካል ለሌላው እንደሚገዛ በግልጽ በመጻፍ የሥላሴን አስተምህሮ ክደዋል”[6]፡፡
  • “[የሮሙ] ቀለሜንጦስ [በ100 ዓ.ም ላይ በጻፈው ጽሑፍ][7]… አብን ፈጣሪያችን፣ አዳኛችንና ጌታችን አድርጎ አቅርቦታል፡፡ ይህም የኢየሱስ የማዕረግ ስም ነው”[8]፡፡
  • “የአግናጢዮስ ጽሑፎች (110 ዓ.ም-115 ዓ.ም) ኢየሱስን ከአንዱ አምላክ ጋር ያመሳስሉታል፤ ከዚህም የተነሣ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የአግናጢዮስ አስተምህሮ እንደ ሞዳልስቲክ ነው እንዲሉ አድርጓቸዋል . . . አግናጢዮስ ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደ ሆነ ገልጾአል . . . አግናጢዮስ አምላክ ሲል፣ አብን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ስለሆነ . . . ይህ ኢየሱስ ትስብእት የሆነ እግዚአብሔር አብ ነው፣ የሚለውን ዐስተሳሰቡን ይፋ የሚያደርግ ነው”[9]፡፡
  • “አግናጢዮስ ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው ሲል፣ በግልጽ ተናግሮአል [በማግኔዢያንስ 15 እንዲህ ይላል፣ ‘የማይነጣጠለው መንፈስ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ’] ”[10]፡፡
  • “ሔርማስ [እረኛው በሚለው ጽሑፉ 140 ዓ.ም እስከ 45 ዓ.ም] መንፈስ ቅዱስን በግጻዌ መለኮት ውስጥ ራሱን የቻለ አካል አድርጎ አይመለከተውም፤ ራሱን ለዓለም እንደ ገለጠ ልጅ እንጂ፣ ‘ቅዱስና ዘላለማዊ (pre-existent) የሆነው መንፈስ ቅዱስ፣ ፍጡራንን ሁሉ የፈጠረ፣ እንደ ፈቃዱ እግዚአብሔር በሥጋ ውስጥ እንዲኖር ያደረገ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ የሚያድርበት ሥጋ ለዚህ መንፈስ በከበረ መልኩ ይገዛል’ (Sim. 5:6) . . . ‘መንፈስ ቅዱስን ልገልጥላችሁ እወዳለሁ . . . ይህም መንፈስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው’ (Sim. 9:1)”[11]፡፡
  • “በዮስጦስ የመጀመሪያው አፖሎጂ (c. 150) ላይ፣ በግጻዌ መለኮት ውስጥ ብዝኃነት እንዳለ አስተምሮአል፡፡ በዚህ መሠረት [በመጀመሪያው አፖሎጂ 6 እና 13 ላይ] አብ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ግን ልክ እንደ መላእክት በሁለተኛ ደረጃ ያሉ አማልክት ናቸው . . . ዮስጦስ ወልድን ከቃል ጋር የሚያመሳስለው ሲሆን፣ ቃልን ደግሞ ከአብ የተለየ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ወልድ አብ ነው የሚሉ ከአብ ጋር አንዳችም ትውውቅ የላቸውም፤ የዓለማት ፈጣሪ የሆነው አብ ልጅ እንዳለው አያውቁም ማለት ነው፤ ይህም የመጀመሪያ ልጅ የእግዚአብሔር ቃል እንዲሁም እግዚአብሔር ነው”[12]፡፡
  • “ምንም እንኳ ዮስጦስ መንፈስ ቅዱስ ከሚመለኩ አካላት መኻል ሦስተኛው አካል አድርጎ ቢያቀርበውም፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተለየ አካል እንደ ሆነ በግልጽ አላስታወቀም፤ እንዲሁም በሦስቱ አካላት ዘንድ ያለውን ግንኙነት አልገለጸም፡፡ በርግጥ በበርካታ ቦታዎች ላይ መንፈስን ከቃል ጋር አንድ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው አፖሎጂ ላይ እንዲህ ሲል ጽፎአል፣ ‘ስሕተት ነው . . . መንፈስንና የእግዚአብሔርን ኀይል የእግዚአብሔር በኲር ከሆነው ከቃሉ የተለየ ማድረግ’”[13]፡፡
  • “[የዮስጦስ ደቀ መዝሙር] ታቲያን በመጀመሪያ ቃል በእግዚአብሔር ውስጥ እንደ ነበር ያምናል፤ ይህ እምነቱም ዲያተስሳሮን [የወንጌላት ስምሙነት] የዮሐንስ 1÷1‘እግዚአብሔርም ቃል ነበረ’ ብሎ እንዲተረጒም አድርጎታል፡፡ ይህም አብዛኞቹ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አማንያን ክፍሉን በሚተረጒሙበት መልክ የተተረጐመ ነው፡፡ የዐላፊውን ጊዜ ዘላለም በተመለከተ፣ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አማንያን ክፍሉን በሚተረጒሙበት መልክ የተተረጐመ ነው፡፡ የዐላፊውን ጊዜ ዘላለም በተመለከተ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዐይነት አመለካከት አለው፡፡ ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን የሚለየውም ምድር ከመፈጠሯ በፊት በነበረ በአንድ ወቅት፣ ከእግዚአብሔር በመውጣት ከእግዚአብሔር የተለየ አካል ሆኖአል የሚለው እምነቱ ነው”[14]፡፡
  • “የዐላፊውን ጊዜ ዘላለም በተመለከተ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዐይነት አመለካከት አለው፡፡ ከሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን የሚለየውም ምድር ከመፈጠሯ በፊት በነበረ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር በመውጣት ከእግዚአብሔር የተለየ አካል ሆኖአል የሚለው እምነቱ ነው”[15]፡፡

ቅድመ ኒቂያ ጉባኤ አበው ሰባልዮሳዊ ዐስተሳሰብ እንደ ሌላቸው የሚያስረግጡ በርካታ ምንባባትን ከራሳቸው ጽሑፎች ላይ በቀጥታ በመጥቀስ፣ “የኦንሊ ጂሰስን” ኑፋቄ ማጋለጥ የሚቻል ቢሆንም፣ እስካሁን ከዴቪድ ኬ. በርናርድ በቀጥታ የጠቀስናቸው ክፍሎች ራሳቸው፣ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ሰባልዮሳዊ አመለካከት ነበራቸው ወደሚለው ድምዳሜ የሚያደርሱ አይደሉም፡፡ 

       እነዚህ ክርስቲያን አባቶች፣ “አንዱ መለኮታዊ አካል ለሌላው ይገዛል” የሚለው አነጋገራቸው፣ የሰባልዮስንም ሆነ ዘመነኛውን “የኦንሊ ጂሰስ” አስተምህሮ የሚደግፍ አይደለም፤ እንዲያውም የሚጣረስ እንጂ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አበው በግልጽ እንዳስተማሩት፣ የሥላሴ አማንያንም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ዐይነት ባሕርይ እንዳላቸው፣ በአንጻሩ በሥላሴ አካላት መካከል ፈቃደኝነትን በተከተለ መልኩ አንዱ አካል ለሌላው አካል እንደሚገዛ አስተምረዋል፤ እያስተማሩም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሥላሴያዊ እንጂ ሰባልዮሳዊ ዐስተሳሰብ ሊሆን አይችልም፡፡ በሥራ ክፍፍል ዝቅ ማለት (functional subordination)፣ በባሕርይ ማነስን (ontological subordination) አመልካች አይደለም፡፡ “መገዛት” የሚለው ቃል አንድን አካል ሊያሳይ አይችልም፤ ሁለትና ከሁለት በላይ አካላትን እንጂ፡፡   

       የሮሙ ቀለሜንጦስ አብ ብቻ ወይም ወልድ ብቻ ፈጣሪ፣ አዳኝና ጌታ ነው እስካላለ ድረስ፣ እነዚህ የባሕርይ ስሞች፣ አብን ወይም ወልድን ማሳየታቸው አብና ወልድ አንድ አካል ናቸው ወደሚለው ድምዳሜ የሚወስደን አይደለም (“አበበ መምህር ነው”፡፡ “ዓለሙ መምህር ነው” ስለዚህ  “አበበና ዓለሙ አንድ አካል ናቸው” ማለት ስሕተት ነው፡፡ የባሕርይ (የግብር) አንድነት፣ የአካል (የአኃዝ) አንድነትን አመልካች አይደለምና፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች የመምህርነትን ግብር መከወናቸው፣ አንድ አካል ናቸው እንድንል አያደርገንም)፡፡

       አግናጢዮስ ኢየሱስ፣ “በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው” ማለቱ፣ አብ ወልድ ነው የሚል ሰባልዮሳዊ ትምህርት የለውም፡፡ የሥላሴ አማንያንም ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡ ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑ፣ ፍጹም አምላክ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ፣ ኢየሱስ አብ መሆኑን የሚያስተምር አይደለም፡፡

       አግናጢዮስ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ነው አላለም፡፡ ዴቪድ ኬ በርናርድ በማግኔዢያንስ 15 ላይ መንፈስ ማለቱ መንፈስ ቅዱስ ማለቱ ነው የሚለው ትንታኔያቸው ስሕተት ነው፡፡ የመስኩ ሊቃውንት አግናጢዮስ በዚህ ዐውድ፣ መንፈስ የሚለውን ቃል የተጠቀመው፣ “አመለካከት” ወይም “አእምሮ” የሚለውን ቃል በሚወክል መልኩ ብቻ ነው[16]፡፡

       ሊቃውንት፣ ሔርማስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው አስተያየት ግልጽ አይደለም የሚል ዐሳብ ያላቸው ቢሆንም እንኳ፣ ሔርማስ ትምህርቱ፣ “ከኦንሊ ጂሰስ” ኑፋቄ ጋር አንድ ዐይነት ነው ያለ አንድም የነገረ መለኮት ወይም የታሪክ ምሁር የለም፡፡ ከድርጅቱ መምህራን በስተቀር፡፡ “በኢየሱስ ሥጋ ውስጥ የሚያድረው ዘላለማዊ የሆነው መንፈስ፣ ከኢየሱስ ጋር በጋራ የሚሠራ ነው” (Similitude 5:6) የሚለው የሔርማስ አነጋገር፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፤ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ፡፡

የዮስጦስ ሰማዕት ስለ ሥላሴ የጠራ ትምህርት ነበረው የማይባል ቢሆንም፣ አስተምህሮው ግን ከ“ኦንሊ ጂሰስ” ኑፋቄ ጋር አንድ ዐይነት አይደለም፡፡ በርናርድ፣ “በዮስጦስ የመጀመሪያው አፖሎጂ (c. 150) ላይ፣ በግጻዌ መለኮት ውስጥ ብዝኃነት እንዳለ አስተምሮአል” የሚለው ንግግራቸው፣ ዮስጦስ ሰባልዮሳዊ አመለካከት እንዳልነበረው የሚያሳይ ነው፡፡ ዮስጦስ ሰማዕት፣ “ወልድ የእግዚአብሔር የበኲር ቃል እንዲሁም እግዚአብሔር ነው” (Dialogue with Trypho, 11) ማለቱ፣ የወልድን አምላክነት እንጂ ወልድ ራሱ፣ “አባቴ” ብሎ የሚጠራው አብ ነው ማለት አይደለም፡፡ በርናርድ ራሳቸው፣ ዮስጦስ ሰማዕት፣ “ወልድ የእግዚአብሔር የበኲር ቃል እንዲሁም እግዚአብሔር ነው” (Dialogue with Trypho, 11) ማለቱ የወልድን አምላክነት እንጂ፣ ወልድ ራሱ፣ “አባቴ” ብሎ የሚጠራው አብ ነው ማለት አይደለም፡፡ በርናርድ ራሳቸው:—

  • “ዮስጦስ ወልድን ከቃል ጋር የሚያመሳስለው ሲሆን፣ ቃልን ደግሞ ከአብ የተለየ አድርጎ ያቀርቦታል፡፡ ወልድ አብ ነው የሚሉ ከአብ ጋር አንዳችም ትውውቅ የላቸውም፤ የዓለማት ፈጣሪ የሆነው አብ ልጅ እንዳለው አያውቁም ማለት ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያ ልጅ የእግዚአብሔር ቃል እንዲሁም እግዚአብሔር ነው”፡፡

የሚለውን የዮስጦስን ንግግር ጠቅሰው፣ አብና ወልድ አንድ አካል ናቸው ወደሚለው ድምዳሜ እንዴት ሊደርሱ ቻሉ? ይህ እርሳቸው የጠቀሱት የዮስጦስ ንግግር፣ አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን እንጂ፣ አንድ አካል መሆናቸውን በጭራሽ የሚያመለክት አይደለም፡፡ 

ዮስጦስ ሰማዕት፣ “ለእግዚአብሔር ብቻ ልንሰግድ ይገባል” (የመጀመሪያ አፖሎጂ 16) እንዲሁም “ለእግዚአብሔር ብቻ ስግደታችንን እናቀርባለን” (የመጀመሪያ አፖሎጂ 17) መንፈስ ቅዱስ ሊመለክ የሚገባው አምላክ ነው (የመጀመሪያ አፖሎጂ 6) ሲል፣ መንፈስ ቅዱስ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ አምላክ ነው ማለቱ ሳይሆን፣ ልክ እንደ አብና እንደ ወልድ፣ ስግደት የሚገባው አምላክ መሆኑን ለማመልከት ነው (የመጀመሪያ አፖሎጂ 6)፡፡ 

       ዮስጦስ ሰማዕት፣ አምልኮ ለመቀበል፣ “የነቢያት መንፈስ” ከአብና ከወልድ ቀጥሎ፣ “ሦስተኛ” ነው (የመጀመሪያ አፖሎጂ 13) የሚለው አነጋገሩ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ወይም አብና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በርግጥ በበርካታ ቦታዎች ላይ መንፈስን ከቃል ጋር አንድ ማድረጉ እሙን ነው፡፡ በርናርድ ዮስጦስ ሰማዕት፣ “በመጀመሪያው አፖሎጂው ላይ እንዲህ ጽፎአል፣ ‘መንፈስንና የእግዚአብሔርን ኀይል የእግዚአብሔር በኲር ከሆነው ከቃሉ የተለየ ማድረግ . . .ስሕተት ነው’” የሚለው አነጋገራቸው፣ መንፈስንና መንፈስ ቅዱስን እርስ በርሱ የሚያምታታ ነው፡፡ ዮስጦስ በዚህ ክፍል መንፈስ ሲል፣ ኑባሬንና (ዮሐንስ 4÷24 “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” በሚለው ትርጒም) ኀይልን ለማሳየት እንጂ፣ መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት አይደለም፡፡

       በርናርድ ከታቲያን ጠቅሰው የጻፉት ጽሑፍ በግልጽ የሚያሳየው፣ ታቲያን ሥላሴያዊ አመለካከት እንዳልነበረው በአንጻሩ “የኦንሊ ጂሰስ” መሠረተ እምነት እንደሌለው ነው፡፡ ታቲን ኢየሱስ፣ “ምድር ከመፈጠሯ በፊት በነበረ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር በመውጣት ከእግዚአብሔር የተለየ አካል ሆኖአል የሚለው እምነቱ” ቢሾፕ ተክሌ በቅርቡ ሰማያዊ ሥጋ በሚል ከጀመሩት ትምህርት ጋር የሚመሳሰል ከሆነ እንጂ ከነባሩ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” (UPCI) አስተምህሮ ጋር የሚዛመድ አይደለም፡፡ ነባሩ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” ትምህርት፣ ቃል ሥጋ የሆነው በዘመነ ዐዲስ እንጂ፣ “ምድር ከመፈጠሯ በፊት” አይደለምና፡፡

       በተጨማሪም ታቲያን በግልጽ ኢየሱስ፣ “ምድር ከመፈጠሯ በፊት በነበረ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር በመውጣት ከእግዚአብሔር የተለየ አካል ሆኖአል” ማለቱ፣ ግለሰቡ ሰባልዮሳዊ አቋም በጭራሽ እንዳልነበረው የሚያሳይ ነው[17]፡፡

       በርናርድ ታቲያን በዮሐንስ 1÷1 ላይ የሰጠውን ዐሳብ በተሳሳተ መልኩ ነው የተረዱት፡፡ ይኸውም:— (1) “ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ዐብሮ ነበር” የሚለው የዮሐንስ 1÷1 ሁለተኛ ዐረፍተ ነገር፣ ወልድና አብ አንድ መሆናቸውን (እንደ በርናርድ አነጋገር፣ “ቃል በእግዚአብሔር ውስጥ እንደ ነበር”) ሳይሆን፣ አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን የሚያስተምር ነው፡፡ (2) በርናርድ የዮሐንስ 1÷1 ሦስተኛው ዐረፍተ ነገር መተርጐም ያለበት፣ “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” ተብሎ ሳይሆን፣ “እግዚአብሔርም ቃል ነበር” ተብሎ ነው የሚለው ትንታኔአቸው፣ ከግሪክ ሰዋስው አንጻር ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ይህን ጒዳይ በነገረ መለኮት በተብራራበት ቦታ ላይ ሰፊ ቦታ የሰጠነው ቢሆንም፣ የሙግቱ አካሄድ የሚከተለውን ይመስላል:— ይህ የበርናርድ አቋም፣ “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ባለቤት ሙያ (subjective case) “ቃል” ደግሞ ተሳቢ አንቀጽ ማለትም ባለቤት ሙያ (predicate nominative) ነው የሚለውን ጒዳይ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ 1÷1 “እግዚአብሔር” ተሳቢ ሙያ፣ “ቃል” ደግሞ ባለቤት ሙያ ነው[18]፡፡ የታቲያንን የግሪክ ቅጅ የተረጐሙ ሊቃውንት፣ ይህን የታቲያንን ዐሳብ የተረጐሙት በዚሁ መልክ ነው[19]፡፡ “እግዚአብሔርም ቃል ነበረ” የሚለው ትክክለኛ ትርጒም ነው ቢባል እንኳ፣ ቃል አብ ነው የሚል ትርጒም ሊኖረው አይችልም፤ ምክንያቱም ቃልና እግዚአብሔር ዐብረው ስለነበሩ እንዲሁም በሁለተኛው ዐረፍተ ነገር ላይ ያለው እግዚአብሔር (θεὸς ቴዎስ) ውስን መስተኣምር (τὸν) ያለው ሲሆን፣ በሦስተኛው ዐረፍተ ነገር ላይ ያለው እግዚአብሔር (θεὸς)  ግን ውስን መስተኣምር የሌለው መሆኑ፣ በግሪክ ሰዋስው የመጀመሪያው ቴዎስና ሁለተኛው ቴዎስ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ሐ. ውጉዝ ከመሰባልዮስ!

ዴቪድ ኬ በርናርድን ጨምሮ በርካታ፣ “የኦንሊ ጂሰስ” ጸሓፍያን[20] ቅድመ ኒቂያ ጉባኤ አበው ሰባልዮሳውያን ናቸው የሚል ትምህርት እያስተማሩ ቢገኝም፣ እውነታው ግን እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሰባልዮሳውያን ሳይሆኑ፣ “ውጉዝ ከመአርዮስ ወውጉዝ ከመሰባልዮስ” ካሉት ሥላሴያውያን አበው ቅንጣት የተለዩ አለመሆናቸውን፣ የራሳቸውን ጽሑፎች በቀጥታ በመጥቀስ እውነታውን እንመልከት[21]፡፡ በዚህ ስፍራ በእማኝነት የምንጠቅሳቸው አበው ዋና ዋና የሚባሉ ሐዋርያዊ አባቶችን ነው[22]፡፡ 

“የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ጸሓፍትም ሆኑ ሥላሴያውያን አንድ እግዚአብሔር ብቻ አለ[23]፣ አብ እግዚአብሔር ነው[24]፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው[25] በሚለው ነጥብ ላይ አንድ ዐይነት እምነት ቢኖራቸውም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት ናቸው ወይስ አይደሉም በሚለው ነጥብ ላይ ግን ይለያያሉ፡፡ ስለዚህ እኛ ትኲረት የምናደርገው፣ ከዚህ ቀጥለን የምንጠቅሳቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን በግልጽ ያስተማሩትን አበው ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ ደግሞ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አበው ሥላሴያውያን እንጂ ሰባልዮሳውያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡

              አግናጢዮስ ዘአንጾኪያ (ከ35 ዓ.ም እስከ 107 ዓ.ም የኖረ) አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን እንዲህ ሲል ጽፎአል:—

  • “ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ከአብ ጋር ዐብሮ የነበረ እንዲሁም በመጨረሻ የሚገለጥ …እርሱ፣ ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ከአብ የተወለደ፤ አምላክ ቃል የሆነ፣ አንድያ ልጅ የሆነ፣ ዘላለም ሕያው ሆኖ የሚኖር”[26]፡፡
  • “ልዑል በሆነው አብ እንዲሁም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት”[27]፡፡
  • “ዓለማት ከመፈጠራቸው በፊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ እንዲሁም በዘመኑ መጨረሻ ላይ የተገለጠ” ያለ አባቱ ፈቃድ “አንዳች ነገር የማያደርግ”፡፡ ከአንዱ ከአብ ዘንድ የመጣ”[28]፡፡ ሐዋርያት “ለክርስቶስና ለአብ ታዛዦች ናቸው”[29]፡፡

ጶሊካርጶስ (ከ130 ዓ.ም እስከ 150 ዓ.ም የኖረ) ደግሞ እንዲህ ይላል:—

  • “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዲሁም ዘላለማዊው ሊቀ ካህን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ፣ በእምነትና በእውነት ያጽናችሁ”[30]፡፡
  • “ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፣ የተወደደውና የተባረከው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእርሱ በኲል አንተን ማወቅ ችለናል…አመሰግንሃለሁ ምክንያቱም ለዚህ ሰዓትና ለዚህ ቀን ስላበቃኸኝ፤ ይኸውም የክርስቶስን ጽዋ ከጠጡት ከአንተ ሰማዕታት ጋር በመቈጠሬ፣ ለአካልና ለነፍስ በሚሆን ለዘላለም ሕይወት ትንሣኤ…ስለ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፡፡ እባርክሃለሁ፤ አከብርህማለሁ፤ ዘላለማዊና ሰማያዊ በሆነው በልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አሁን እንዲሁም በሚመጣው ዘመን ሁሉ ክብር ለአንተ ይሁን፤ አሜን”[31]፡፡ በርናባስ (በ70 ዓ.ም) ማነው በሚለው ጒዳይ ላይ ሊቃውንት የተለያየ አስተያየት አላቸው፡፡ ነገር ግን የበርናባስ ደብዳቤ በመባል የሚታወቀው ሰነድ እጅግ ጥንታዊ እንደ ሆነ፣ እንዲያውም ሐዋርያቱ በነበሩበት ዘመን እንኳ፣ ግልጋሎት ላይ ይውል እንደ ነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን በዚህ መልክ ይገልጸዋል:—
  • “ጌታ ለእኛ ነፍስ ሲል ሥቃይን ታገሠ፤ የዓለም ሁሉ ጌታ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር በእርሱ በኲል ዓለማትን ከመፍጠሩ በፊት ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር አለ”[32]፡፡

ሔርማስ (በግምት ወደ 57 ዓ.ም ገደማ) ሊቃውንት በሮሜ 16÷14 ላይ የምናገኘው ሰው ነው የሚል አስተያየት አላቸው (ጥንታውያን የሆኑ ዐማርኛ ጽሑፎች ሄሮሜን ይሉታል)፡፡ የሔርማስ ምጋቤ (The Shepherd of Hermas) በመባል የሚታወቀው ሰነድ አብና ወልድ የተለያየ ማንነት እንዳላቸው የገለጸው በዚህ መልክ ነው:—

  • “የእግዚአብሔር ልጅ ከፍጥረት ሁሉ በፊት ነው፤ ከዚህ የተነሣም በፍጥረት ውስጥ የአባቱ አማካሪ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እርሱ ጥንታዊ ነው”[33]፡፡

እስካሁን የተመለከትነው ጉባኤ ኒቂያ ከመካሄዱ ሁለት መቶ ዓመት በፊት የነበሩትን እንዲሁም ከክርስቶስ ሐዋርያት እግር ሥር በቀጥታ እንደ ተማሩ የሚነገርላቸውን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ነው፡፡ “ሊበሏት የፈለጓትን ቈቅ ጅግራ ነሽ ይሏታል” ካልሆነ በቀር፣ ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ አበው ሰባልዮሳውያን ናቸው ብሎ መከራከር አንዳችም የታሪክ ድጋፍ ሊገኝለት አይችልም፡፡

ከላይ በስፋት ለመመርመር እንደ ሞከርነው፣ ሐዋርያት በቅዱሳት መጻሕፍት አብና ወልድ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን እንደ ገለጹልን ሁሉ፣ እነዚህም አባቶች አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ በመረጃ ዘመን፣ እነዚህን ሥላሴአውያን አበው፣ ሰባልዮሳውያን ናቸው ብሎ ማስተማር፣ የእውነት ሎሌ አያሰኝም፡፡


[1] United Pentecostal Church International–(UPCI).

[2] “የመጠበቂያ ግንብ” የሚባለው፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ድርጅት በዚህ ረገድ መረጃዎችን እንዴት እያጠናበረ እንደሚያቀርብ በግልጽ ለመታዘብ፣ እባክዎን ይህን ድረ ገጽ ይመለከቷል:—     

https://www.bible.ca/trinity/trinity-jw-deceptions.htm

[3] “ኀልዮአዊ ሃኬተኝነት” ኀልየ ማለት ዐሰበ፣ መረመረ፣ ማለት ነው፡፡ ሀኬት ማለት ስንፍና፣ ቸልታ፣ ንዝህላልነት፣ ተንኰል፣ ክፋት፣ ማለት ነው፡፡ በተገናኝ በእንግሊዝኛ፣ “intellectual laziness” የሚለውን ይወክላል፡፡

[4] ከጌታ ሐዋርያት እግር ሥር የተማሩት “ሐዋርያዊ አባቶች” (Apostolic Fathers) የሚባሉ ሲሆን፣ ከሐዋርያዊ አባቶች ሥር የተማሩቱ ደግሞ፣ “ቅድመ ኒቂያ አበው”  ወይም “የቤተ ክርስቲያን አባቶች” (Ante-Nicene Fathers or Church Fathers) በመባል ይታወቃሉ፡፡ “ሐዋርያዊ አባቶች” ከሚባሉት ውስጥ ዋነኞቹ:— የሮሙ ቀለሜንጦስ፣ የአንጾኪያው አግናጢዮስ፣ የሰምሬኔሱ ጶሊቃርጶስ (ፖሊካርፕ)፣ የሂራፖሊሱ ፓፒያስ ይገኙበታል፡፡ “ቅድመ ኒቂያ አባው” ከሚባሉት መኻል ዋነኞቹ:— ዮስጦስ ሰማዕት፣ የሊዮኑ ሔሬኒዎስ፣ ጠርጡሊያኖስ፣ አርጌንስ፣ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ፣ የእስክንድርያው አርጌንስ፣ የሮሙ ሂፖሊተስ፣ የቅርጣግናው ሰፒርያኖስ፣ የአንጾኪያው ቴውፍሎስ፣ የአቴናው አትናጎረስ ናቸው፡፡ በዚህ መጽሐፍ የእነዚህን አባቶች ስም አጠራር የተከተልነው እንግሊዝኛውን ሳይሆን፣ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ጽሑፎችን ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥንት አባቶችን፣ ለዚህ አገርኛ ስያሜ ከልብ እናመሰግናለን፡፡  

[5] እኔ ነገረ መለኮት የተማርሁበት ካልቪን ዩኒቨርሲቲ፣ ሐዋርያዊ አባቶችንም ሆነ፣ ቅድመ ኒቂያና ድኅረ ኒቂያ አባቶችን ጽሑፎች በ14 ቅጽ ተከታታይ መጻሕፍት አዘጋጅቶ አቅርቦአል፡፡ ይህን ሰነድ በሚከተለው ድረ ገጽ በቀጥታ ማንበብ ይቻላል:— https://www.ccel.org/fathers?utm እንዲሁም Philip Chaff and Henry Wace አርታዒ የሆኑበትን 14 ቅጽ መጻሕፍት ይመለከቷል፡፡ በዚህ ረገድ ካቶሊካውያንም ሆኑ ኦርቶዶክሳውያን እጅግ አስደናቂ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ለምሳሌ:— የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህን አባቶች ጽሑፍ፣ በዐማርኛና በግእዝ ተርጒማ አቅርባለች፡፡ እነዚህ አባቶች ሥላሴአውያን መሆናቸውን ሰው ሁሉ በተለይም ክርስቲያኑ ማኅበረስብ በውል ሊያውቀው፣ የመናፍቃኑን ማደናገር ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡        

[6]   David K. Bernard, Oneness and Trinity A.D. 100-300: The Doctrine of God in Ancient Christian Writings (Hazelwood, Mo.: Word Aflame Press, 1991), 24.

[7] ዴቪድ በርናርድ ለቀለሜንጦስም ሆነ ለሌሎቹ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የተጠቀመው ጊዜ፣ አብዛኞቹ የታሪክና የነገረ መለኮት ሊቃውንት ለእነዚህ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አበው ከተጠቀሙበት ጊዜ ቢያንስ የሠላሳ ዓመት ልዩነት አለው፡፡ “ይህቺ ጠጋ ጠጋ ዕቃ ለማንሣት ነው” ይላል ነቄ የአገሬ ሰው፡፡ ሊቃውንት የሮሙ ቀለሜንጦስ ጽሑፉን የጻፈው ቢበዛ 70 ዓ.ም ላይ ካነሰ ደግሞ 68 ዓ.ም ላይ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ ለምሳሌ የሚከተለውን መጽሐፍ ይመለከቷል:— John A. T. Robinson, Redating the New Testament (Philadelphia: Westminster, 1976), 352-53.

[8] ዝኒ ከማሁ፤ 33፡፡

[9]  ዝኒ ከማሁ፤ 33-34፡፡

[10] ዝኒ ከማሁ፤

[11]  ዝኒ ከማሁ፤

[12]  ዝኒ ከማሁ፡፡

[13]   ዝኒ ከማሁ 68-69፡፡

[14]  ዝኒ ከማሁ፤ 79-80፡፡

[15]  ዝኒ ከማሁ፡፡

[16] E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches  (Reprint, Grand Rapids: Zondervan 1998), 40 ከJ. B. Lightfoot and J. R. Harmer, trans., The Apostolic Fathers: Revised Greek Texts with Introductions and English Translations (Reprint, Grand Rapids: Baker, 1984), 146; J. B. Lightfoot, ed. and trans., The Apostolic Fathers: Clement, Ignatius, and Polycarp, Revised Texts with introductions, Notes, Dissertations, and translations, 5 vols. (Reprint, Peabody, Mass.: Hendrickson, 1989), 2:2:140. ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡

[17] ታቲያን ኢየሱስ፣ “ምድር ከመፈጠሯ በፊት እንኳ ከአብ የተለየ ማንነት ነበረው” የሚል አቋሙን ከሚከተሉት መጻሕፍት ላይ ይመልከቱ:— የታቲያንን Pros Hellenonas (ለግሪካውያን የተደረገ ንግግር)፣ 5, in J.P. Mign’, ed., Patralogiae Graecae, 6:818-15 ከሚከተለው መጽሐፍ ጽሑፍ ጋር ያወዳድሩ:— J.E. Ryland translation in Alexander Robers and James Donaldson, eds., The Ante-Nicene Fathers: Translations of the Writings of the Fathers down to A. D. 325, 10 vols. (Reprint, Grand Rapids: Eerdmans, 1975), 2:67.

[18] ዮሐንስ 1÷1 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ይመለከቷል፡፡  

[19] E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 42 k D. Plooij, A Primitive Text of the Diatessaron: The Liege Manuscript of a Mediaeval Dutch Translation, A Preliminary Study (Leyden: A. W. Sijthoff’s Uitgeversmaatschappij, 1923), introductory note by J. Rendel Harris, 3. ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡

[20]  ለምሳሌ:— William B. Chalfant, Ancient Champions of Oneness: A History of the True Church of Jesus Christ (Junction City, Kans.: 1979).

[21]  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ “ሃይማኖተ አበው” በሚል ርእስ ያዘጋጀችው መጽሐፍ፣ ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ አበውን ጨምሮ ጥንታውያን አበው በሥላሴ ትምህርት ላይ ያላቸውን አስተያየት የያዘ ነው፡፡ አንባብያን ይህን መጽሐፍ በጥሞና እንድታነብቡት እናበረታታለን፡፡ ብዙ ጠቃሚ ትምህርት አለውና፡፡

[22]  “ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አበው” የምንለው በቀጥታ በጌታ ሐዋርያት ሥር የተማሩትን “ሐዋርያዊ አባቶችን” ሲሆን፣ “ደኅርት የቤተ ክርስቲያን አባቶች” የምንለው ደግሞ በሐዋርያዊ አባቶች እግር ሥር የተማሩትን ነው፡፡  

[23] ለምሳሌ:— የዘሮሙ ቀለሜንጠስ፤ ቆሮንቶስ 58፤ ማግኔዢያንስ 8፤ ሔርማስ The Shepherd, Mandate 1, in Lightfoot and Harmer, The Apostolic Fathers, 82, 144, 422. E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 48 ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡

[24] ለምሳሌ:— የዘሮሙ ቀለሜንጠስ፤ ቆሮንቶስ 62፤ አግናጢዮስ ኤፌሶን inscription; (English), 39 (Greek), 137 (English), 105 (Greek), 181 (English), 173 (Latin). E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 48 ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡

[25]  ለምሳሌ:— Lightfoot and Harmer, The Apostolic Fathers, ቀለሜንጦስ ዘሮም፤ ቆሮንቶስ 16 (English, p. 63, and Greek, p. 12); አግናጢዮስ ኤፌሶን inscription (English, 137, and Greek, 105), 1:1 (English, 137, and Greek, 105), 7:2 (English, 139, and Greek, 107), 18:2 (English 141, and Greek, 110),ሮሜ   inscription (English, 152, and Greek, 122), ጶሊቃርጶስ 3:2 (English, 160, and Greek, 132), 8:2 (English, 162, and Greek, 134). E. Calvin Beisner Jesus OnlyChurches, 49 ጠቅሶ እንደ ጻፈው፡፡ 

[26]  ከድርሳኑ ቃል በቃል የተጠቀሰውን እነሆ:— “Jesus Christ, who was with the Father before the beginning of time, and in the end was revealed. . . . He, being begotten by the Father before the beginning of time, was God the Word, the only-begotten Son, and remains the same for ever” (emphasis added; Letter to the Magnesians, 6).

[27]  ይህ የአግናጢዮስ ሙግት በሻርፐስ ሕግ ቍጥር 1 እና ቍጥር 2 የሚገዛ ስላልሆነ፣ አብና ወልድ አንድ አካል ናቸው ማለት ስሕተት ነው፡፡ E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 49.

[28]   Lightfoot and Harmer, The Apostolic Fathers, 144-45 (English), 113-14 (Greek). E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 50.

[29] የግሪኩን ቅጅ ከLightfoot and Harmer, The Apostolic Fathers, ላይ ይመለከቷል፡፡ (Magnesians, 23:2; Magnesians, inscription; 1:2; 13:1, Ephesians, 21:2; Trallians 1:1; Philadelphians, inscription; 1:1; 3:2; Polycarp, inscription; and Smyrnaeans, inscription). E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 49.

[30] Philippians 12:2. አብን አምላክ እንዳለው ሁሉ፣ ሊቀ ካህኑን ኢየሱስ  አምላክ ይለዋል፡፡ 

[31] “O Lord God Almighty, the Father of thy beloved and blessed Son Jesus Christ, by whom we have received the knowledge of Thee . . . I give Thee thanks that Thou hast counted me, worthy of this day and this hour, that I should have a part in the number of Thy martyrs, in the cup of thy Christ, to the resurrection of eternal life, both of soul and body, through the in corruption [imparted] by the Holy Ghost. . . . Wherefore also I praise Thee for all things, I bless Thee, I glorify Thee, along with the everlasting and heavenly Jesus Christ, Thy beloved Son, with whom, to Thee, and the Holy Spirit, be glory both now and to all coming ages. Amen (emphasis added; Martyrdom of Polycarp, 14)”. E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 50.

[32]  Lightfoot and Harmer, The Apostolic Fathers, 273 (English), 247-48 (Greek) (Epistle of Barnabas, 5:5, 9). E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 50.

[33] “The Son of God is older than all his creation, so that he became the Father’s adviser in his creation. Therefore, also he is ancient” (The Shepherd, Ninth Similitude, 12). E. Calvin Beisner “Jesus Only” Churches, 50.

Share the Post:

Related Posts