ዕቅበተ እምነት ዘክርስትና

የዚህ ምዕራፍ ቀዳማይ ዐላማ ሦስት ነው፡፡ ይኸውም:—

  • የምሥራቹን ወንጌል በማብሠር (ማለትም በወንጌል ሥርጭትና ደቀ መዛሙርት በማፍራት) ሂደት ውስጥ፣ የሥነ ጽሑፍ ሚና ትልቅ መሆኑን በጒልኅ ማሳየት፣
  • በሥነ ጽሑፍ ረገድ በቤተ ክርስቲያን የሚታየውን  ክፍተት፣ ለማነጻጸሪያ ከተመረጠ ናሙና ጋር ማገናዘብ (ማነጻጸር) የክፍተቱን ጥልቀትና ስፋት በውል ማስተዋል፣ 
  • ለማገናዘቢያነት የተመረጠው ናሙና ጠንከራ ጐኖች ናቸው የሚባሉትን ተሞክሮዎችና አሠራሮች፣ ቤተ ክርስቲያን ልትጠቀምባቸው እንዴት እንደምትችል፣  ጠቋሚ ዐሳቦችን ፈንጠቅ ማድረግ ነው፡፡   

፪.የሥነ ጽሑፍ ኀያል ክንድ

ከአሜሪካን መሥራች አባቶች መኻል አንዱ የሆኑት ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ሃያ ስድስት ወታደሮች ስጡኝ ዓለምን በቊጥጥሬ ሥር አደርጋለሁ”[1] ይሉ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ግለሰቡ ሃያ ስድስት ወታደር የሚሏቸው፣ በወታደራዊ ሳይንስ የሠለጠኑ፣ በጦር ዐውድማ የተፈተኑ፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቁ፣ በሾተል ፍልስፍና የመጠቁ፣ የኮማንዶ አባላትን አይደለም፡፡ በእንግሊዝኛ የፊደል ገበታ ላይ የተሰተሩትን፣ ሃያ ስድስት የእንግሊዝኛ ሆህያት እንጂ፡፡

የግእዝ ቋንቋ ሊቃውንት፣ ሰዎች “ነባብያን ወንቊኀን” ናቸው ሲሉ፣ የኀልዩ የነቢብና የገቢር (የዐስተሳሰብ፣ የንግግር እንዲሁም የምግባር) ባለሀብት መሆናቸውን፣ የሥነ ጽሑፍ ባለቤት መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ርግጥ ነው፣ የሥነ ጽሑፍን ኀያል ጒልበት፣ ሥነ ጽሑፍ ራሱ፣ ነግሮ ዘክሮ እንደ ማይጨርሰው እናውቃለን፡፡ ዕውቀት ከአንድ አእምሮ ወደ ሌላው አእምሮ የምናስተላልፍበት (የምናንቈረቊርበት) ሁነኛ ቦይ፣ ሥነ ጽሑፍ ነው፡፡ 

ኮሚኒስቶች የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ርእዮተ ዓለማቸውን በዓለም ላይ እንዲናኝ ያደረጉት፣ በሰላ ብዕራቸው፣ በቀስቃሽ ጽሑፋቸው እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ፣ በዘመነ ደርግ በዐማርኛ ቋንቋ ተተርጒመው ለንባብ የቀረቡትን፣ የካርል ማርክስ፣ “ዳስ ካፒታል” እና “ኮሚኒስት ማኒፌስቶ” መጻሕፍት እንዲሁም ርእዮተ ዓለሙን የሚተነትነውን፣ “የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት” በዚህ ረገድ ጒልኅ አብነት አድርጎ ማቅረብ ይቻላል፡፡  በ“ቀዝቃዛው ጦርነት” ወቅት፣ በርካታ አገሮች ከኮሚኒስቷ ራሻ (መስኮብ) ተርታ መሰለፍ የቻሉት፣ የርእዮተ ዓለሙ መሪዎች ፍልስፍናቸውን ለአእምሮ ግቡዕ በሆነ ሁኔታ በመተንተን፣ በሥነ ጽሑፍ ከሽነው ወደየሰዉ ልብ ማድረስ በመቻላቸው ነበር፡፡

በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣው የፕሮቴስታንቱ የተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ እንደ ምትሐት ሊታይ የሚችል ነውጥ ማስከተል የቻለው፣ ንቅናቄው ትምህርትን ማዕከል እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ መር የመሆኑ ሐቅ ነው፡፡ የማኅበረሰብን አኗኗርና ለውጥ ይከታተሉ የነበሩ የዘመኑ ደራስያን፣ “የፕሮቴስታንትን ተሐድሶ በማይጠፋ እሳት በነዳጅ ያንቀለቀለው፣ የኅትመት መሣሪያ ፈጣሪው ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ከንቅናቄው ቀደም ብሎ ዮሐንስ ጉተንበርግ፣ የማተሚያ መሣሪያ ባይፈጥር ኖሮ፣ የሉተርና የመርሕያነ ተሐድሶዎች ጥረት፣ ከመንደር ጫጫታ ዘለግ ያለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም ነበር፡፡

አትነቀስም አትገሠሥም በተባለችው ካቶሊካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የተኰለኰሉት አውሮፖውያኑ ነገሥታት፣ በዐይን ብሌን የሚመስሉትን ካቶሊካዊ እምነታቸውን ከጥቃት የመከላከል ዐቅም ያጡት፣ ከእነርሱ ጒልበት የሚበረታ ኀይል፣ ሞገድ እንዳጀበው ደራሽ ውሃ ድንገት ከተፍ በማለት፣ በርዳ ተራዳ የቈመውን ነገር ግን ሐዳስያኑ በሰላ ሒስ የሞሸለቁትን ተረት፣ ታዛ አልባ በማድረጋቸው ነበር፡፡ አስደናቂው ነገር፣ እንደ ስሟ ሁሉ በነገረ መለኮቷም፣ “ዓለም ዐቀፋዊት ነኝ” ብላ ትኵራራ የነበረችው ካቶሊካዊቷ ቤተ ክርስቲያን፣ በመራሕያነ ተሐድሶዎቹ የዕድሜ ዘመን እንኳ፣ ሊጠገን በማይችል ደረጃ በግማሽ መሰንጠቋ፣ የትምህርትንና የሥነ ጽሑፍን ብርቱ ጒልበት በውል የሚያሳይ ጥሩ ማገናዘቢያ ነው፡፡      

ከዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ፣ ከአውሮፓ እንዲሁም ከሰሜን አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሚስዮናውያን፣ ወንጌልን ለመስበክ በሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ስብከተ ወንጌልንና የቀለም ትምህርትን እንደ ነበልባልና እንደ ብርሃን አያይዘውት ተጒዘዋል፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ፊደል በመቊጠር በዘመናዊው ትምህርት መሟሸት የጀመሩት፣ ሚስዮናውያኑ ባቋቋሟቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ የቀለም ተቀብዖ አላቸው ያሏቸውንም የበለጠ ትምህርት ያገኙ ዘንድ፣ ከአገር ውጪ ሄደው እንዲማሩ ሁኔታዎችን ያመቻቹ ነበር፡፡ በዚህ አግባብ ነበር አንድ ሰው፣ “ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ” በሚል፣ በሚስያናውያኑ ትምህርት ቤት ይሤም የነበረው፡፡

እንዲያውም ይህ አካሄድ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከዚህም የገዘፈ ታሪክ ይዞ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ “ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ፊደል ቀርጻ” ትምህርትንና ሥልጣኔን፣ አሐዱ ብላ እንዳስጀመረች ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መጀመሪያ ከተተረጐሙባቸው ጥንታውያን ቋንቋዎች መኻል፣ ግእዝና ዐማርኛ በቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለትምህርትና ለምርምር የነበራትን ልብ አመልካች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ክርስትና ትምህርት ወዳድ የክርስቶስም ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ መር መሆናን አመልካች ነው፡፡        

በዓለማችን የሚገኙት አንጋፋና ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች በዋነኛነት የተቋቋሙት፣ ነገረ መለኮትን ለመተንተንና ለማስተንተን እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የትምህርት ማዕከል የነበሩት ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት እንደ ነበሩ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና እንደ ቅዱስ ቃሉም መኖር፣ የክርስትና ሕይወት መነሻና መዳረሻ ነው፡፡ ይህ ክርስትና ለምርምርና ለጥናት እጅግ ለም መሬት መሆኑ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ይህን በውል በመገንዘብ፣ የማንነቷ አካል ማድረጓ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍን ለአምስት መሠረታውያን ዐላማዎች ስትጠቀምበት ኖሯለች፡፡ ይኸውም:— (1) መሠረተ እምነቷን ከጥቃት ለመጠበቅ፣ (2) ተጻራሪ ዐስተሳሰቦችን ለማምከን፣ (3) ወንጌልን ለማሠራጨት፣ (4) አባሎችዋን በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርትና በክርስቲያናዊው ንጽርኦተ ዓለም ለማነጽ እንዲሁም፣ (5) አምልኮተ እግዚአብሔር ለማካሄድ፡፡

፫. አዚም ያደረገብን ማነው?

በርግጥ ይህ እውነት ከሆነ ንባብ ጠል፣ ሥነ ጽሑፍ ጠል፣ ትምህርት ጠል…የሆነ ማኅበረሰብ ከየት በቀለ? የዚህ ችግር ዋነኛ መናሻ ምንድን ነው?  ችግሩን በስፋት ማስተንተን ትልልቅ ጥራዝ ያላቸው መጻሕፍት ጭብጥ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ችግሩም ዕልባቱም ፈርጀ ብዙ ተኣማኒ ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ምክንያቶች መኻል፣ አንዱን በእኛ ግምት ዋነኛ የመሰለንን አንዱን ብቻ፣ በወፍ በረር እንቃኘው፡፡ ይህ ክርስትና የተመሠረተበትን መሠረት ያፈረሰ፣ የተያዘበትን መልኅቅ የቈረጠ ትልቅ ችግር ነው፡፡    

ይኸውም በኢትዮጵያ ውስጥ የተነሣው የአባይ ነባዮችና የመናፍቃን እንቅስቃሴ ነው፡፡ በተለይ የአባይ ነባዮች እንቅስቃሴ፣ ክርስቲያኖች ቃለ እግዚአብሔርንና ምርምርን የጒዞ መስመራቸው እንዳያደርጉ እጅግ ትልቅ እክል ፈጥሮአል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው የሚለውን የአስተንትኖት ጥያቄ እንመልከት፡፡  

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ትልቅ ትዕግሥት፣ ብዙ ትግል ይፈልጋል፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መኻል ተዘውትረው የሚጠቀሱትን ሦስት መሠረታውያን ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:—

  • መጽሐፉ ጥንታዊ መሆኑ አንብቦ የመረዳቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በእኛና በመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳማይ ተደራስያን መኻል፣ የብዙ ሺሕ ዓመት ርቀት አለ፡፡ ብሉያት ከሦስት ሺሕ ዓመት በፊት የተጻፉ ሲሆን፣ ሐዲሳት ደግሞ ከሁለት ሺሕ ዓመት በፊት እንደ ተጻፉ ይታመናል፡፡ ይህ ደግሞ በእኛና በቀዳማይ ተደራስያኑ መኻል ያለውን ንጽሮተ ዓለም፣ በከፍተኛ ደረጃ አለያይቶታል፡፡ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የፍልስፍና ወዘተ ምጥቀት የዘመኑን ሰው አመለካከት፣ ከጥንታውያኑ ሰዎች አተያይ በከፍተኛ መጠን አራርቆታል፡፡
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሓፍያንና በመልእክቱ ቀዳማይ ተደራስያን መካከል ከፍተኛ የሆነ የባህል ልዩነት አለ፡፡ ይህም ተግባቦቱ እንዲደነቃቀፍ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በኋላ እንኳ፣ ስመ ጥር የሚባሉ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሊቃውንት፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎች ትክክለኛ ትርጒማቸው ምን እንደ ሆነ እንደማያውቁ መግለጻቸው የዘመናት ርቀቱ፣ የመልእክቱን ትክክለኛ ትርጒም በውል እንዳንረዳ ማድረጉን የሚያሳይ ነው (በሁሉም ባይሆን በተወሰኑ ምንባባት ላይ)፡፡   
  • መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ቋንቋ እኛ ከምናውቀው ቋንቋ፣ ዘይቤአዊ አገላለጽ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ዘውግ ወዘተ በብዙ የተለየ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ትረካዎች ይደራጁበት የነበረው ምክንያት ከዛሬው ዘመን በብዙ የሚለይበት ጠበቀይ አለው፡፡  

እነዚህና እነዚህን መሰል ሁኔታዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በትክክል ለመረዳት፣ ረጅም ጊዜ የሚፈጅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገውታል፡፡ የማስተማር ዕድል ባገኘሁባቸው ቦታዎች፣ “ሁሉን ቻዩ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር፣ ዐሳቡን ለሰብአውያን ለማስተላለፍ፣ ይህ ዐይነቱን አድካሚ መንገድ ለምን እንደ መረጠ” የሚል ጥያቄ ሰዎች ይጠይቁኛል፡፡ መልሴ፣ “አላውቅም!” ነው፡፡ አምላክ ይህን መንገድ ለምን እንደ መረጠ በእውነት አላውቅም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ይኸውም አምላክ ቅዱሱን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ነድቶ እንካችሁ እንዳለን ሁሉ፣ ይህን አድካሚ ጐዳና እንዳያታክተን፣ የመረዳት ክፍተቱን እንዲሞሉልን ትልልቅ ሊቃውንትንና አስተማሪዎችን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶአል፡፡ እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለረጅም ዓመት በማጥናት፣ ክፍተቱ እንዲሞላ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ እንኳ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መረዳት ትልቅ ጥረት መፈለጉ እብለት የሌለበት ሐቅ ነው፡፡

ሥነ አፈታትን ማወቅ፣ የእናት ቋንቋውን ሰዋስዋዊ ዐወቃቀር ማወቅ፣ ነገረ መለኮትን ማወቅ፣ ፍልስፍናን ማወቅ፣ አመክንዮን ማወቅ ወዘተ፡፡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተው፣ እጅግ ለረጅም ዓመት የሚማሩበትም ምክንያት ይኸው ነው፡፡  ስለዚህ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ የአምላክን ምክር ለመረዳት፣ ከእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ጋር መፋጠጡ የግድ ሆኗል፡፡  

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያስፈለገበት ዐቢይ ዐላማ፣ አምላክ በግልም ሆነ በጋራ የሚናገረንን ነገር በግልጽ ለመረዳት ነው፡፡ የትንቢትም ዋነኛ ዐላማ ይኸው ነው፡፡ ስለዚህ የአባይ ነባዮቹ አቀራረብ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመረዳት የምንታገለውን በርካታ ትግል ሙሉ አስወጋጅ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በተወሰኑ አጋጣሚዎች እግዚአብሔር ነቢያትን በማስነሣት፣ በአንዳንድ ጒዳዮች ላይ ለቤተ ክርስቲያን ምሪትን እንደሚሰጥ አገር ያወቀው ፀሓይ የሞቀው ነው፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው፣ ይህ በብሉያትም በሐዲሳትም የነበረ ዛሬም ያለ ቋሚ አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን አምላክ የየዕለቱን ትምህርትና ምክር የሚሰጠን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ እንጂ፣ በነቢያት በኲል አልነበረም፡፡

ዛሬ በዙሪያችን እንደ እንጒዳይ የፈሉት አባይ ነባዮች፣ ቢያስፈልግ በቀን ዐሥር ጊዜ፣ በእያንዳንዱ ርእሰ ጒዳይ ላይ አምላክ ሊናገረን የሚፈልገውን ነገር እናቅርብላችሁ እያሉን ነው፡፡ እንግዲያው አምላክ በትንቢትና በነባዮች በዚህን ያህል ቅርበትና በዚህን ያህል መጠን የሚናገር ከሆነ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናት፣ በተለይ ደግሞ ከዚህ እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ ጋር መታገል ለምን ያስፈልጋል?

ወገን የማንበብ ፍላጎታችንን ያሰለለው የቅዱሳት መጻሕፍት ፍቅራችንን የሰለበው ይህ ነው! ይህ ነው መጽሐፍ ቅዱሳችንን ያስረጀብን! ይህ ነው ንባብ ጠል፣ ሥነ ጽሑፍ ጠል፣ ትምህርት ጠል…ማኅበረሰብ እንድንሆን ያደረገን! ለቅዱሳት መጻሕፍት ባይተዋሮች ያደረገን! በስምህና በአድራሻ ተክ ይልልሃል የሚባል መልእክት ካለ፣ ቆሮንቶስ፣ ማቴዎስ፣ ራእይ ዮሐንስ ወዘተ ማለት፣ እኮ ለምን ያስፈልጋል? በቀጥታ፣ “አምላክ አንቺን እንዲህ ይልሻል!” የሚለው “መገለጥ” ብዥታ የሌለበት ብቻ ሳይሆን፣ በተፈለገው ርእሰ ጒዳይ ላይ፣ በተፈለገበት ጊዜና መጠን የሚገኝ፣ “ምሪተ አምላክ” ሆኖአል፡፡

እጅግ ጥንታውያን ከሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ከመፋጠጥ፣ ይህ የተሻለ አካሄድ አይደለምን? እንደ ጪስ አፍኖ የያዘን፣ ዕድገታችንንና ብስለታችንን የሰለበብን፣ የአባይ ነባያት እንደ እንጒዳይ የመፍላታቸው ክሥተት ነው፡፡    

አንድ ወዳጄን፣ “ጌታ በዚህ መጠን በነባዮች የሚናገር ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊነቱ እምኑ ላይ ነው?” አልሁት፡፡ እርሱም በኲራት፣ “ሁል ጊዜ  አንድ ዐይነት ወጥ ብቻ እንዴት ትበላለህ? ይሰለቻል እኮ!…መገለጥና ትንቢት ጥቊሩ መጽሐፍ እንዳይሰለቸን አምላክ የሰጠን ተለዋጭ ወጥ፣ ያውም የዶሮ ወጥ ነው” አለኝ፡፡ “‘በጥቊሩ መጽሐፍና’ ‘በዶሮው ወጡ’ መኻል ትክክለኛ ዳኝነት በማድረግ፣ ሚዛናዊ ክርስትናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምንመሠርተው እንዴት ነው?” የሚለው፣ እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ነው (በርግጥ ጒዳዩ፣ “የዶሮ ወጥ ነው” በሚለው ብንስማማ እንኳ ማለቴ ነው)፡፡ ለዚህ ሁነኛ ጥያቄ ሁነኛ መልስ ሳናበጅ፣ የዘመናት በሽታችን መፍትሔ ያገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍትና ወደ ምርምር ፊታችንን እንመልሳለን ማለት፣ እጅግ ሲበዛ  ቀልድ ነው፤ ቀቢፀ ተስፋ[2] ነው፤ ከንቱ ተምኔት ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያና የቀረበ እጅግ ወሳኝ ፈተና፣ ድል ከተነሣ ደግሞ እጅግ ትልቅ ድል ነው፡፡  

ቀጥለን የማንበብ ባህላችን ምንኛ እንደ ተንኰታኰተ በግልጽ ሊያሳይ የሚችል ናሙና መርጠን ራሳችንን እንታዘብ፡፡ ይህ ናሙናዊ ጥናት፣ ቤተ ክርስቲያን በምን ያህል መጠን ተዥረብርባ እንደ ወደቀች በጒልኅ ያሳያል፡፡

ለናሙናዊ ጥናቱ የተመረጠው፣ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር በመባል የሚታወቀው፣ “የይሖዋ ምስክሮችን” ድርጅት ነው[3]፡፡ የእነርሱ ትጋት ለእኛ ሥጋት፣ የእነርሱ ጥረት ለእኛ ኀፍረት፣ የእነርሱ ከፍታ ለእኛ ዝቅታ እንዴት ሊሆን እንደ ቻለ እንመልከት፡፡  

፬. ንጽጽራዊ መታዘቢያ

ከዚህ በመቀጠል የሥነ ጽሑፍን ኀያል ጒልበት በትክክል ከተረዱ የሃይማኖት ክፍሎች መኻል፣ በቀዳሚነት እየተጠቀሰ የሚገኘውን፣ የሃይማኖት ንቅናቄ ማገናዘቢያ አድርጎ በማቅረብ፣ ከጥንካሬው ልምድ ለመቅሰም ሙከራ እናደርጋለን፡፡

“ከመናፍቃን ልምድ የምንቀስመው እንዴት ነው?” የሚል ግርምት የተቀላቀለበት ጥያቄ ሊቀርብ ይችል ይሆናል፡፡ “እንዴት ተደርጎ ነው እኛ፣ ከዘመኑ አርዮሳውያን፣ ልምድ ለመቅሰም የምንከጅለው?” ሊባል ይችላል፡፡ “ከይሖዋ ምስክሮች” ክርስቲያናዊ ትምህርት እንደማንማር እሙን ነው፡፡ እነርሱን በመናፍቃን ጐራ የዳረጋቸው፣ እኛን በርቱዕ ሃይማኖት ዕቅፍ የከተተን፣ እነርሱ መሠረታውያኑን የክርስትና ትምህርት መካዳቸው፣ እኛ ደግሞ ጤናማውን ወንጌል መቀበላችን ነው፡፡ ስለዚህ በእኛና በእነርሱ መኻል ያለው ልዩነት፣ የአስተምህሮ ልዩነት ነው፡፡ ወንጌል ዘላለማዊ፣ እውነትም ነባራዊ እስከ ሆነ ድረስ፣ ይህ ልዩነት በፍጹም ሊታረቅ አይችልም፤ እስከ ወደያኛው ጸንቶ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ከኑፋቄአቸው አንዳችም ትምህርት የምናገኝበት አግባብ የለም፡፡ በወንጌል ተጫምተን በመቈም ኑፋቄውን ከማፍረስ፣ ሰዎችን ከማስመለጥ በቀር፣ ሌላ አማራጭ አይኖረንም፡፡

አቀራረብን (አሠራርን) በተመለከተ ግን፣ ከመናፍቃን ብዙ ትምህርት እንደምናገኝ መታወቅ አለበት፡፡ እንዲያውም ትልቅ ትምህርት የሚገኘው ከመናፍቃን ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ መናፍቃን በአንድ ወቅት በእኛ ጒያ ውስጥ ተሸሽገው የኖሩ ሰዎች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህም የእኛን ጥንካሬና ድካም በትክክል እንዲያውቁ ዕድል ሰጥቶአቸዋል፡፡ ስለዚህ የእነርሱን ግብር (ድርጊት) መመልከት፣ የእኛን ድካም ለመታዘብ ትልቅ ዕድል ይሰጠናል፡፡ “ብልኅ ሰው ከሌላው ሰው ውድቀትና ጥንካሬ ብዙ ትምህርት ይቀስማል” የሚባለው አባባል፣ ይህን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ግርግዳ ላይ የሚለጠፍ አንድ ጽሑፍ፣ “እህ ብለው ከሰሟቸው፣ እንኳን ከጤነኞች ከዕብዶችም ቊም ነገር አይጠፋም” ይላል፡፡ ፈረንጆች፣ “የማይሠራ ሰዓት፣ በቀን ሁለት ጊዜ ትክክል ነው” እንደሚሉት ዐይነት ነው፡፡ ስለዚህ በነባቤ ቃል ደረጃ እጅግ የበዛና የከፋ ስሕተት ያለባቸው መሆኑ፣ የአሠራር ጥንካሬ የላቸውም ወደሚለው ድምዳሜ የሚወስደን አይደለም፤ እንደዚያ ማሰብ ስሕተት አደገኛም ነው፡፡   

መናፍቃን ሰዎችን በቀላሉ መማረክ ከቻሉባቸው ምክንያቶች መኻል አንዱና ዋነኛው፣ የቤተ ክርስቲያንን የአሠራር ድካም ዐጒልተው ማናገራቸው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ድካም አስተውሎ፣ በጒዳዩ ሲብከነከን የቈየ ሰው፣ በሽንገለቸው በቀላሉ ይታለላል፤ በስምከታቸው ይወሰዳል፡፡ ከበስተ ኋላ ያለውን ትምህርታቸውን በመደበቅ፣ “እኛ ከቤተ ክርስቲያን የወጣነው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ብለን ነው፡፡ ችግሩ ቢፈታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ልንመለስ እንችላለን” ስለሚሉ፣ “ተሐድሶን” ታሳቢ ባደረገ መንፈስ፣ ሰዎች በቀላሉ ይከተሏቸዋል፡፡

ስለዚህ፣ “የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር” በመባል በሕግ የሚታወቀውን፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ድርጅት፣ ሥነ ጽሑፍን እንዴት እየተጠቀመ ነው የሚለውን ጒዳይ፣ የጒዞ መስመር አድርገን የጽሑፍን ኀያል ክንድ እንመለከታለን፤  በዚህ ረገድ ያለብንን ድካም (ውድቀት) እንመረምራለን፡፡

ይህ ሲባል ግን ድርጅቱ ሥን ጽሑፉን ፕሮፖጋንዳ አድርጎ እየተጠቀመበት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ከድርጅቱ የምንማረው ጥሩ ነገር ቢኖርም ሥነ ጽሑፍን የፕሮፖጋንዳ ሰለማ ማድረጉን ደግሞ በጽኑ ልንኰንን ይገባል፡፡

፭. የጊነስ መጽሐፍ ያደነቀው ሥራ

የዓለም አስደናቂ ክሥተቶች የሚመዘገቡበት የጊነስ መጽሐፍ፣ ከዛሬ 55 ዓመት በፊት፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት” በሚል ርእስ፣ በመጠበቂያ ግንብ ድርጅት የታተመው መጽሐፍ፣ በ115 ቋንቋዎች በመተርጐም፣ 100 ሚሊዮን ቅጅ በመባዛት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ፣ የሁለተኛውን ቦታ እንደ ያዘ ገልጾአል[4]፡፡ ይህ የአንድ ጊዜ ክሥተት ብቻ አይደለም፤ የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት የአዘቦት ወግ እንጂ፡፡ መረጃው እነሆ:—

ከማንኛውም መናፍቃን ይልቅ ሥነ ጽሑፍንና የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀም ላይ የሚገኘው፣ “የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር” በመባል የሚታወቀው፣  “የይሖዋ ምስክሮች” የሃይማኖት ድርጅት ነው፡፡ በቅርቡ[5] የድርጅቱ በድረ ገጹ ላይ ያወጣው ጽሑፍ እንዲህ ይላል: 

“በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ያነባሉ። አሁን አንተ እያደረግክ[ህ] እንዳለኸው ሁሉ በሚሊዮን የሚቆ[ቈ]ጠሩ ሰዎች እነዚህን ጽሑፎች የሚያነቡት[፣] በኤሌክትሮኒክ መሣሪዎች ነው። ይሁንና ምን ያህል ጽሑፎች እንደሚታተሙ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ከ2013 [ዓ.ም] ወዲህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን 700 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ማዘጋጀት የጀመርን ሲሆን፣ ጽሑፎቹ በ239 አገሮች ውስጥ እየተሰ[ሠ]ራጩ ነው”[6]። 

እንደ ጐርጐሮሳውያኑ አቈጣጠር በ2021 ዓ.ም፣ አባላቱ የድርጅቱን ጽሑፍ ለማሠራጨት 1.4 ቢሊዮን ሰዓት[7] በመስክ[8] አሳልፈዋል[9]፡፡ አንድ ዓመት በአማካይ 8,760 ሰዓት ስላለው 1.4 ቢሊዮን ሰዓት፣ 159,817 ዓመታት ማለት ነው፡፡ በድርጅቱ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ሰዎች፣ “የድርጅቱ እያንዳንዱ አባል የድርጅቱ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ነው” የሚሉት፣ ይህና ይህን መሰል መረጃዎችን ምክንያት አድርገው ነው፡፡  

ከ26 ዓመት በፊት ይፋ የሆነ አንድ መረጃ፣ “የይሖዋ ምስክሮች” በዓለም ዙሪያ 33 ታላላቅ ማተሚያ ቤቶች እንዳላቸው ይገልጻል[10]፡፡ “ቤቴል” በመባል የሚታወቀው ትልቁ ማተሚያ ቤታቸው ብቻ፣ በቀን ርዝመቱ 1,000 ማይል (1,609 ኪሎ ሜትር) የሚያህል ወይም 61 ሚልዮን ገጽ ወረቀት ያትማል[11]፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወር 3 ሚሊዮን የዐዲስ ዓለም ትርጒም እያተመ ያወጣል፡፡

ይህን ጒዳይ በተመለከተ፣ እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን ቀመር 2023 ዓ.ም በየድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:—

“ከ1920 በፊት ሁሉም ጽሑፎቻችን የሚታተሙት በንግድ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ነበር። በ1920 [ዓ.ም] ግን በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኝ አንድ አነስተኛ ሕንፃ በመከራየት[፣] አንዳንድ መጽሔቶቻችንንና ቡክሌቶቻችንን ራሳችን ማተም ጀመርን። ከዚህ አነስተኛ ጅምር የተነሳ[ሣ]ው ይህ የኅትመት ሥራ[፣] በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ 15 ማተሚያ ቤቶቻችን ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል”[12]

በ1991 ዓ.ም. በእነዚህ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ 11,000 የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች ነበሩ[13]፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ የወጣቶችን ነጻ ጒልበት በመጠቀም፣ የኅትመት ሥራውን እንደሚያካሂድ በድርጅቱ ድረ ገጹ ላይ የወጣው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:—  

“ማተሚያ ቤቶቻችንን የሚጎ[ጐ]በኙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በዚያ የሚሠሩትን ታታሪ ሠራተኞች ሲመለከቱ ይገረማሉ። ሥራውን የሚያከናውኑት ወንዶችና ሴቶች [በ]ሙሉ ጊዜያቸውንና ጉ[ጒ]ልበታቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ። አብዛኞቹ ወደ ቤቴል (“የአምላክ ቤት” ማለት ነው) በመጡበት ወቅት ስለ ሕ[ኅ]ትመት ሥራ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ቤቴል ውስጥ የተሰጣቸው ሥልጠና በቤቴል ካለው ምቹ የሥራ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ[፣] ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በሰዓት 200,000 ባለ 16 ገጽ መጽሔቶችን የማተም ችሎታ ያለውን እጅግ ፈጣን የሕ[ኅ]ትመት መሣሪያ ሲያንቀሳቅሱ ማየት[፣] የተለመደ ነገር ነው”[14]

እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን ቀመር 2013 ዓ.ም፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ጽሑፎቻቸውን 700 ቋንቋዎች በመተርጐም 239 አገሮች ውስጥ አሠራጭተዋል[15]፡፡

ከድርጅቱ አስተምህሮ ጋር እንዲጣጣም ተደርጐ የተተረጐመው የዐዲስ ዓለም ትርጒም በ2013 ዓ.ም ብቻ፣ በ121 ቋንቋዎች ተተርጒሞ፣ 184 ሚልዮን ቅጅ ተባዝቶ ተሠራጭቷል[16]፡፡ ይህ የድርጅቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም በተመለከተ፣ የድርጅቱ ድረ ገጽ እንዲህ ይላል:—

“ከምናትማቸው ጽሑፎች ሁሉ እጅግ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ለመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሆነ የታወቀ ነው። መጀመሪያ ያተምነው መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ኪንግ ጀምስ ቨርዥን ሲሆን[፣] ታትሞ የወጣው በ1942 ነው። ከ1961 አንስ[ሥ]ቶ የይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች ሙሉውን የቅዱሳን መጻሕፍት []ዲስ ዓለም ትርጉ[] አዘጋጅተው በአንድ ጥራዝ ሲያትሙ ቆ[ቈ]ይተዋል። እስከ 2013 [ዓ.ም] ባለው ጊዜ ውስጥ[፣] ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በ121 ቋንቋዎች[፣] ከ184 ሚሊዮን ቅጂዎች [ቅጆች] በላይ ማተም ችለናል”[17]

ሁለቱ የድርጅቱ ዕውቅ መጽሔቶች ማለትም፣ “መጠበቂያ ግንብ” እና “ንቊ” የኅትመት ብዛታቸው፣ የሥርጭት ስፋታቸው እንዲሁም የሚተረጐሙበት የቋንቋ ብዛት በርግጥ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ለምሳሌ:— 2013 ዓ.ም “መጠበቂያ ግንብ” 210  ቋንቋዎች በመተርጐም፣ 45 ሚልዮን ቅጅ ተባዝቶ ተሠራጭቷል[18]፡፡ “ንቊ” መጽሔት ደግሞ፣ በ99 ቋንቋዎች የተተረጐመ ሲሆን፣ 44 ሚልዮን ቅጅ ታትሞ ተሠራጭቷል[19]፡፡ ሥርጭቱም ሪደርስ ዳጀስት እንዲሁም ቲቪ ጋይድ ከሚባሉት መጽሔቶች ካላቸው ሥርጭት ጋር የሚስተካከል፤ ሽያጩም ከታይምስ፣ ከኒውስ ዊክ፣ ከዩ ኤስ ኒውስና፣ የወርልድ ሪፖርት ጋር የሚወዳደር ነው[20]፡፡

የዐዲስ ዓለም ትርጒም በ1990 ዓ.ም ብቻ በ67 ሚልዮን ቅጂዎች የተባዛ ሲሆን፣ በ14 ቋንቋዎች ተባዝቶ ለንባብ ቀርቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ መጽሐፍ ዐማርኛን ጨምሮ፣ ከ129 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጒሞአል[21]፡፡

ይህ የድርጅቱ መጽሔቶች ልዩ ጠባይ ብቻ አይደለም፡፡ የመጻሕፍትና የመለስተኛ መጻሕፍት (brochure) ነባር ባሕርይ ጭምር እንጂ፡፡ ለምሳሌ:— “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” በሚል ርእስ የታተመውና የድርጅቱን መሠረተ እምነት ለዐዳዲስ ተከታዮች የማስተማሪያ መጽሐፍ (224 ገጽ አለው)፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃው በ2005 ዓ.ም ሲሆን፣ 240 ቋንቋዎች ተተርጐሞ፣ 214 ሚልዮን ቅጅ ተባዝቶ ተሠራጭቷል[22]፡፡

በቅርቡ፣ “አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ባለ 32 ገጽ ጥራዝ መለስተኛ መጽሐፍ 400 ቋንቋዎች ተተርጐሞ፣ በ42 ሚልዮን ቅጅ ተባዝቶ ተሠራጭቷል[23]፡፡

በ2012 ዓ.ም ብቻ በድርጅቱ ማተሚያ ቤቶች የታተሙት መጽሔቶች ብዛታቸው 1.3  ቢሊዮን ሲሆን፣ መጽሐፍ ደግሞ 80 ሚልዮን ነው[24]፡፡

ኅዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም ለንባብ የበቃው፣ “የመጠበቂያ ግንብ” መጽሔት፣ በገጽ 27 ላይ ድርጅቱ አዘጋጅቶ ያሠራጫቸውን የኅትመትና የቪዲዮ ውጤቶች በሚከተለው መልክ ይፋ አድርጓል፡፡

  • 3,168,611 ቪዲዮዎች
  • 6,834,740 መለስተኛ መጻሕፍት
  • 47,490,247 መጻሕፍት
  • 167,854,462 በአንድ ርእሰ ጒዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ብሮሹሮች
  • 440,995,740 በራሪ ከጽሑፎች
  • 1,179,266,348 (1.2 ቢሊዮን የሚጠጋ መጽሔት)    

በኅትመት ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በሥርጭት ብዛት እንዲሁም በሚተረጐሙባቸው ቋንቋዎች ብዛት፣ የድርጅቱ መጽሔቶችና መጻሕፍት በዓለም የቊጥር አንድ ቦታን ይዘዋል፡፡           

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድርጅቱ በብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በዐይነትም እጅግ በርካታ መጻሕፍትን ዐትሞ በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡ የኅትመት ጥራታቸው እጅግ የላቀ እንዲሁም በሙሉ ቀለም የታተሙ በመሆናቸው፣ የማንበብን ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኅትመት ውበታቸው አምሮና ደምቆ መቅረቡ፣ አንባቢው የያዙትም ትምህርት ትክክል ነው የሚለውን፣ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ድርጅቱ ለዘመናት ሲጠቀምበት የኖረው ስልት ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተዘጋጁ ያሉት መጻሕፍት፣ በምን ያህል ቊጥር ተባዝተው እንደ ተሠራጩ በመጻሕፍቱና በመጽሔቶቹ ላይ መግለጽ ትተዋል (ይህን ማወቅ የሚቻለው፣ በዓመቱ የሚወጣው የእንቅስቃሴ ሪፖርት ብቻ ነው ይህን መረጃ የምናገኘው)፡፡

ከዐሥር ዓመት ወዲህ በዐማርኛ ቋንቋ የታተሙት መጻሕፍት ወደ 35 ይደርሳሉ[25]፡፡ ድርጅቱ ዋና ዋና ስለሚላቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች በድረ ገጹ የሚከተለውን ገለጻ አቅርቧል (በቀጥታ ዘለግ አድርገን  እንጥቀስ):—

“ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ የሚያግዙ ሌሎች ጽሑፎችንም እናትማለን። ከ2013 ጀምሮ የታተሙትን ጽሑፎች አኃዝ ተመልከት:—

መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀው ዋነኛ መጽሔታችን[፣] ከ210 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ሲሆን[፣] በዓለማችን ላይ በብዛት በመሰ[ሠ]ራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። አ[ዐ]ሥራ ስድስት ገጾች ያሉት እያንዳንዱ እ[ዕ]ትም ወደ 45,000,000 በሚያህል ቅጂዎች [ቅጆች] ይታተማል[26]

ንቁ! ከመጠበቂያ ግንብ ጋር አ[ዐ]ብሮ የሚታተም መጽሔት ሲሆን[፣] በስፋት በመሰ[ሠ]ራጨት ረገድ [፣] ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል፤ ይህ መጽሔት በ99 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። እንዲሁም እያንዳንዱ እ[ዕ]ትም ወደ 44,000,000 ያህል ቅጂ[ጅ] ይታተማል[27]

ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ፣ ለስላሳ ሽፋን ያለው ሲሆን [፣] አንባቢው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች እንዲገነዘብ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ከ2005 [ዓ.ም] ወዲህ ይህ መጽሐፍ ከ214 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች [ቅጆች]ና ከ240 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ታትሟል[28]

አምላክን ስማ የተባለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር የንባብ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በብሮሹሩ ላይ የሚገኙት ማራኪ ሥዕሎችና አ[ዐ]ጠር ያሉት የሥዕሎቹ መግለጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ቀላል በሆነ መንገድ ያስጨብጣሉ። ብሮሹሩ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ42 ሚሊዮን ቅጂዎች [ቅጆች] በላይ ታትሟል[29]

“ከእነዚህ ጽሑፎች በተጨማሪ የይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ፣ በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲፈቱና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚረዱ የተለያዩ መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችንና ትራክቶችን አ[ዐ]ትመዋል። በ2012 የይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች በራሳቸው ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ከ1.3 ቢሊዮን የሚበልጡ መጽሔቶችን እንዲሁም ከ80 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትንና መጽሐፍ ቅዱሶችን አ[ዐ]ትመዋል[30]

“በ2012 የይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች በራሳቸው ማተሚያ ቤቶች ውስጥ[፣] ከ1.3 ቢሊዮን የሚበልጡ መጽሔቶችን እንዲሁም ከ80 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትንና መጽሐፍ ቅዱሶችን አ[ዐ]ትመዋል”[31]፡፡

ድርጅቱ ስለ ጽሑፎቹ የኅትመት ጥራት እንዲህ ይላል:—

“ይህን የሕ[ኅ]ትመት ሥራ አስደናቂ የሚያደርገው የታተሙት መጽሐፍ ቅዱሶች ብዛት ብቻ አይደለም። የምናዘጋጃቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ለረጅም ጊዜ ያገለግላሉ። ወረቀቶቹ ወደ ቢጫነት እንዲለወጡ ከሚያደርግ አሲድ ነፃ ከመሆናቸውም በላይ[፣] መጽሐፉ በጥሩ መንገድ የተጠረዘ ነው። በዚህም የተነሳ[ሣ] አንባቢዎች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ ቢጠቀሙበት እንኳ  [፣] ለብዙ ጊዜ ማገልገል ይችላል”[32]

፮. መረጃን በዐውደ መረብ የማሠራጨት ተግባር

ድርጅቱ የኅትመት ሥራዎችን በወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በድረ ገጹ ላይ ዕያተመ በማስነበብ፣ በብዙ ስኬት ዐላማውን ከዳር እያደረሰ ይገኛል፡፡ “ወንጌል በኢንተርኔት” በሚል ርእስ ተዘጋጅቶ፣ ድረ ገጹ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:—

“የይሖዋ ምሥክሮች ኢንተርኔት ላይ ሕጋዊ ድረ ገጽ ካወጡ 25 ዓመታት ተቆ[ቈ]ጠሩ። የኅዳር 1997 [ዓ.ም] የመንግሥት አገልግሎታችን ‘ወንጌል በኢንተርኔት’ በሚል ርዕ[እ]ስ… አ[ዐ]ዲስ ድረ ገጽ መውጣቱን አስተዋውቆ ነበር። ርዕ[እ]ሱ እንዲህ የሚል ሐ[ዐ]ሳብ ይዟል:— ‘ማኅበሩ የይሖዋ ምሥ [ስ]ክሮችን እምነትና እንቅስቃሴ የሚመለከቱ አንዳንድ ትክክለኛ መረጃዎችን ኢንተርኔት ውስጥ አስገብቷል። . . . የዌብ ሳይቱ ዓላማ አ[ዐ]ዲስ የሚወጡ ጽሑፎችን ማስተዋወቅ ሳይሆን[፣] ብዙ ሰዎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝ[ይ]ነት መረጃዎችን እንዲያገኙ መርዳት ነው።’[33]

“ከዚያን ጊዜ አንስ[ሥ]ቶ ሰዎች አንዳንድ ትራክቶችን፣ ብሮሹሮችን እንዲሁም መጠበቂያ  ግንብ እና ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕ[እ]ሶችን…ማውረድ ችለዋል። watchtower.org የተባለው ድረ ገጽ ለሕዝብ ክፍት የሆነው ጥር 15, [ቀን፤] 1997 [ዓ.ም] ነው። ከዚያም በ1999 [ዓ.ም] jw-media.org የተባለው ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በዚህ ድረ ገጽ አማካኝ[ይ]ነት[፣] ሕግ ነክ ጉዳዮችንና ሌሎች ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ከይሖዋ ምሥ[ስ]ክሮች ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ክንውኖችን በተመለከተ[፣] ለመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ መስጠት ተችሏል[34]

“‘ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ኢንተርኔት ይጠቀማል። ኢንተርኔት ለብዙዎች በተለይም ለወጣቶች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል. . .የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በሆነባቸው የምድር ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች[፣] ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ያስችላል።’[35]

“ቀደም ሲል ጽሑፎችን ማውረድ የሚቻለው በ411 ቋንቋዎች ብቻ ነበር። ድረ ገጹ በ2012 ተሻሽሎ ከወጣ ከሰባት ዓመት ገደማ በኋላ ግን[፣] ጽሑፎችን በ1,000 ቋንቋዎች ማውረድ ተችሏል፤ ከእነዚህ መካከል 100 የምልክት ቋንቋዎች ይገኙበታል። ይህ ድረ ገጽ በስፋት በመተርጎ[ጐ]ም ረገድ[፣] በዓለማችን የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል።[36]

“ድረ ገጹን ከሚጎ[ጐ]በኙ ሰዎች ጋር በተያያዘ[፣] ከፍተኛው ቁ[ቊ]ጥር የተመዘገበው[፣] የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በተከበረበት ዕለት ማለትም[፣] ሚያዝያ 7, [ቀን፤] 2020 [ዓ.ም] ነበር፤ በዕለቱ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ድረ ገጹን ጎ[ጐ]ብኝተዋል። በ2020 [ዓ.ም] ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ድረ ገጹን የጎ[ጐ]በኙ ሲሆን[፣] በ2019 ግን ድረ ገጹን የጎ[ጐ]በኙት 800 ሚሊዮን ሰዎች ነበሩ። ከጥር 2022 [ዓ.ም] ወዲህ[፣] በየቀኑ በአማካይ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ድረ ገጹን ይጎ[ጐ]በኛሉ።[37]

“ይህ ድረ ገጽ በስብከቱ ሥራ እገዛ ያደርግልናል፣ ከድርጅቱ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ይሰጠናል[፤] እንዲሁም ዓለም አ[ዐ]ቀፉን የወንድማማች ማኅበር አንድ በማድረግ[፣] ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። ይህን ግሩም መሣሪያ ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።”[38]  

፯. አንኳር አንኳር መረጃዎች

“የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር”፣ ሥነ ጽሑፍን የህልውናው አልፋና ዖሜጋ አድርጎ የሚንቀሳቀስ፣ በዚህም ትልቅ ድል ያስመዘገበ የሃይማኖት ተቋም ነው፡፡ ከድርጅቱ ስኬት እንዲሁም ተሞክሮ ቢያንስ የሚከተሉትን ዐሥራ ሁለት አንኳር አንኳር ነጥቦች ማውጣት ይቻላል፡፡ እነዚህን ነጥቦች ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት እናዛምዳለን የሚለው ጒዳይ፣ ብዙ ውይይትና ምክክር ከመፈለጉ ባሻገር፣ እንደየቤተ እምነቱ ዐቅምና ዝግጅት የሚወሰን ነው፡፡ እነሆ ዐበይት ነጥቦች:—  

  • የጽሑፎቹን የኅትመት ብዛት እጅግ ከፍተኛ ማድረጉ፤  

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት፣ በወረቀትም ሆነ በድረ ገጹ ላይ የሚያትማቸው ጽሑፎች ብዛት፣ እጅግ ሲበዛ አስገራሚ ነው፡፡ ከላይ ለመመልከት እንደ ሞከርነው የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት፣ በአንድ ዓመት ብቻ፣ “6,834,740 መለስተኛ መጻሕፍት፣ 47,490,247 መጻሕፍት፣ 167,854,462 በአንድ ርእሰ ጒዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ብሮሹሮች፣ 440,995,740 በራሪ ጽሑፎች፣ 1,179,266,348 (1.2 ቢሊዮን የሚጠጋ መጽሔት እንዲሁም 663,175,189 መጻሕፍት)”[39] ዐትሟል፡፡ ይህ ማለት ቀኑንና ሌሊቱን ጨምሮ በአንዲት ሰከንድ ውስጥ 38 መጽሔቶችና 21 መጻሕፍት ያትማል ማለት ነው፡፡ መጠበቂያ ግንብ ድርጅት ይህን ሁሉ ጽሑፍ ያተመው 2005 ዓ.ም ነው (ጠቅላላው ወደ 1.9 ቢሊዮን መጽሔቶና መጻሕፍት)፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ወይም እንደ ዓለም ባንክ መረጃ በ2005 ዓ.ም፣ የዓለም ሕዝብ ቊጥር 6.5 ቢሊዮን ነበር፡፡ ይህ ማለት ድርጅቱ በአንድ ዓመት ያተመው ጽሑፍ፣ አንድ ሦስተኛ ለሚሆነው የዓለማችን ነዋሪ፣ በነፍስ ወከፍ ሊዳረስ የሚችል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ድርጅቱ በአንድ ዓመት ዐትሞ የሚያሠራጨው ጽሑፍ፣ ከሦስት የዓለማችን ነዋሪዎች መኻል፣ ለአንዱ ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ይህ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ድርጅቱ ሰዎች አስተምህሮውን ባይቀበሉ እንኳ፣ አስተምህሮውን በማስተዋወቅ ይተጋል፡፡ እንዲሁም ተጻራሪዎቼ ናቸው የሚላቸውን አስተምህሮዎች የሚጻረር ጽሑፍ ይበትናል፡፡ ሰዎች የድርጅቱን ትምህርት ባይቀበሉ እንኳ፣ በራሳቸው ሃይማኖት ላይ ጥያቄ እንዲፈጠርባቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ዛሬ ድርጅቱ በዚህ መንገድ የዘራው ዘር፣ ነገ ቀን ቈጥሮ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር፣ ሊበቅል እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ አካሄድ ነው፡፡       

  • የጽሑፎቹን የኅትመት ጥራት እጅግ ከፍተኛ ማድረጉ፤

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት ዓለምን የሚያስደምመው በኅትመት ብዛት ብቻ አይደለም፤ ጥራትም ጭምር እንጂ፡፡ ለኅትመት የሚጠቀምባቸው ወረቀቶች ሙሉ ቀለም ማተም የሚችሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከአሲድ ነጻ መሆናቸው፣ በዕድሜ ብዛት እንዳይወይቡ ወይም ወደ ቢጫነት እንዳይቀየሩ አስችሏል፡፡ የድርጅቱ የኅትመት ውጤቶች አንዳች ብልየት ሳያሳዩ ለረጅም ዘመን የመኖር ዐቅም አላቸውና፡፡ አንድ ሰው የድርጅቱን ጽሑፍ ቤቱ አስገባ ማለት፣ ቀን ቈጥሮ የሚፈነዳ ፈንጂ ቤቱ ውስጥ አጠመደ ማለት ነው፡፡

የመጻሕፍቱና የመጽሔቶቹ የኅትመት ጥራት እንኳን ለሦስተኛው ዓለም አገሮች፣ በሠለጠነውም ዓለም እንደ ትንግርት የሚታዩ ናቸው፡፡ እያንዱ የኅትመት ውጤት፣ በሙሉ ቀለም መታተሙ፣ የወረቀቱ ጥራት የላቀ መሆኑ፣ በየጽሑፉ መኻል ማረፊያ የሚሆኑ ውብ ሥዕሎንና ፎቶ ግራፎችን መነስነስ፣ የድርጅቱ ጽሑፎች ዐይነተኛ ባሕርይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሰዎችን የንባብ ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይሰለቹ እንዲያነቡ ምክንያት ሆኗል[40]፡፡ የኅትመት ውጤቶቹ እጅግ ውብ መሆናቸው አንባቢያን፣ “እንደ ኅትመቱ ጥራት ይዘቱም ቊም ነገር አለው” ብለው እንዲያስቡ አድርጓል፡፡ ሰዎች የኅትመት ጥራቱ (አቀራረቡ) እጅግ ውብ መሆን፣ ጭብጡ (ይዘቱ) እውነተኝ ነው ወደሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡      

  • ጽሑፎቹን በብዛት ማሠራጨቱ፤  

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት፣ዓለምን ጒድ ያስባለው በኅትመት ብዛትና በኅትመት ጥራት ብቻ አይደለም፤ በሥርጭትም ስፋት እንጂ፡፡ ለምሳሌ፣ “ንቊ!”  እና “መጠበቂያ ግንብ” የሚባሉት መጽሔቶች ያላቸው የሥርጭት ስፋት፣ በዓለማችን እጅግ ተወዳጅና ተነባቢ ከሚባሉ ሁለት መጽሔቶች (ሪደርስ ዳጀስትና ቲቪ ጋይድ) በአንድ ተደምረው፣ ከሚገኘው የሥርጭት ስፋት በብዙ ቊጥር በልጦ ተገኝቶአል፡፡ ምንም እንኳ የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት መጽሔቶች ሽያጭ፣ በኢትዮጵያ ብዙ እመርታ ባያሳይም፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ግን ታይምስ፣ ኒውስ ዊክ፣ ዩ ኤስ ኒውስና፣ ወርልድ ሪፖርት ካላቸው ሽያጭ ጋር  የሚወዳደር ሆኖ ተገኝቶአል[41]፡፡

  • ዘመናዊ የኅትመት መሣሪያ መጠቀሙ፤

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት እጅግ ዘመናዊ የሚባሉና የጥራት ደረጃቸው እጅግ የላቁ የኅትመት መሣሪያዎችን በብዛት መጠቀሙ፣ በትንሽ ወጪ፣ በትንሽ ቦታ፣ እጅግ ብዙ ጽሑፎችን ዐትሞ ማውጣት አስችሎታል፡፡ ይህ ደግሞ በጥቂት የሰው ኀይልና ጊዜ፣ ብዙ ሥራ እንዲያከናውን አስችሎታል፡፡   

  • ውቅታዊና አስፈላጊ ርእሰ ጉዳዮችን ማንሣቱ፤  

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት የጽሑፍ ትኲርት አድርጎ የሚያነሣቸው ርእሰ ጒዳዮች፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል፣ የዕውቀት ደረጃና ቦታ ያሉ ሰዎች የሚፈልጓቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ የሕይወት አንገብጋቢ ጥያቄ ናቸው በሚባሉ ርእሰ ጒዳዮች ላይ ትኲረት አድርጐ ይጽፋል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች የኅትመት ውጤቶቹን እንዲፈልጉ አድርጓል፡፡

      ለምሳሌ፣ “ንቊ!” የሚባለው መጽሔት የሚሰናዳው፣ ነገረ መለኮትን ለማስተማር ወይም የድርጅቱን መሠረተ እምነት ለመተንተን አይደለም፡፡ ወቅታዊ ጒዳዮች ላይ ትኲረት በማድረግ፣ ሰዎች ወደ ድርጅቱ ለመሳብ ነው፡፡ የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ የሚዘጋጁ መጻሕፍት እንዳሉ ሁሉ፣ ልጆቼን እንዴት ላሳድግ ለሚሉ ወላጆች የሚጠቅሙ፣ በርካታ ጽሑፎችን እያተመ ያሠራጫል፡፡        

  • በጥቂት ወጪ ብዙ ውጤት ማስመዝገቡ፤

ድርጅቱ በዐሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን እንዲሁም የኮሌጅ ተማሪዎችን በዕረፍት ጊዜያቸው ወደ ማተሚያ ቤቶቹ እንዲመጡ በማድረግ፣ የጒልበት አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ በዚህ መንገድ እጅግ ከፍተኛ ጒልበት፣ በነጻ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች መፎካከር ስለሚወዱ፣ ብዙ ውጤት ያስመዘገቡ ልጆችን የዕውቅና ሰርተፍኬት በመስጠት፣ ጒልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ለዐላማው ይጠቀማል፡፡   

       ድርጅቱ የትርጒምሥራዎቹን ሁሉ የሚያሠራው “የቤቴል ሰዎች” ወይም “ቤቴላውያን” በሚላቸው፣ ራሳቸውን ለዚህ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በሰጡ ሰዎች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለዚህ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ የራሳቸው መኖሪያ ቤት እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት መገልገያ ዕቃ የላቸውም፡፡ የሚኖሩት ኮተቤ በሚገኘው፣ “ቤቴል” ብለው በሚጠሩት ባለ አራት ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ ድርጅቱ ለእነዚህ ሰዎች ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ከመስጠት ያለፈ አንዳችም ክፍያ አይፈጽምም፡፡   

  • አቀራረቡን ሳይንሳዊ ማድረጉ፤

በመጻሕፍቱና በመጽሔቶቹ ኅዳግ ማስታወሻ ላይ፣ ወሳኝ ጥያቄዎችንና አንኳር አንኳር ዐሳቦችን በማስታወስ፣ የንባቡን ወሳኝ መልእክት ያስጨብጣል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች በእያንዳንዱ ገጽ፣ ምን ተማርሁ የሚለውን ጒዳይ እንዲጠይቁ እንዲሁም የአንቀጹን ዐቢይ መልእክት በቀላሉ ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል፡፡

       ከዚህ በተጨማሪ በዕውቀትና በመረዳት ዝቅተኛ ናቸው ለሚላቸው ሰዎች የሚሆን ትምህርት ያዘጋጃል፡፡ ለምሳሌ:— “አምላክን ስማ” የተባለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር፣ “የዐስተሳሰብ ችሎታቸው ደካማ ነው” ለሚባሉ ሰዎች እየተዘጋጀ የሚቀርብ ነው፡፡ በብሮሹሩ ላይ የሚገኙት ማራኪ ሥዕሎችና ዐጫጭር ገለጻዎች፣ ሰዎች መልእክቱን በቀላሉ እንዲይዙ ያስችላል[42]፡፡    

  • ዋነኛውን ጉዳይ ዋነኛ ማድረግ መቻሉ፤

በየትኛውም የዕድሜና የዕውቀት ክልል ያለ የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት አባል፣ መሠረተ እምነቱን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡  እንዲያውም ለእያንዳንዱ መሠረተ እምነት የመከራከሪያ ነጥብ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህ ድርጅቱ ትኲረት ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ትኲረት ሰጥቶ መሥራቱን አመልካች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ መሠረተ እምነቱን ለሌሎች ለማስረዳት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል፡፡ ድርጅቱ ያለውን ጥሪት ሁሉ የሚጠቀመው፣ አባላቱን ለማስተማርና ዐዳዲስ አባላትን ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ ድርጅቱ ዐላማ ይህ ነው፤ ያለውንም ጥሪት እንዲሁም የሰው ኀይልና ዕውቀት የሚጠቀመው ለዚሁ ጒዳይ ነው፡፡  

  • የድርጅቱን ሥራዎች በዐውደ መረብ ተደራሽ ማድረጉ፤

ድርጅቱ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለምን እንደ ጀመረ ሲገልጽ፣ “‘ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ኢንተርኔት ይጠቀማል። ኢንተርኔት ለብዙዎች በተለይም ለወጣቶች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል. . . መልእክት ለመስማት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በሆነባቸው የምድር ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች[፣] ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ያስችላል።’[43] ይህ ወጣቱን ለማግኘት እንዲሁም በተለያየ የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎችን በቀላሉ ለመድረስ፣ ከሚጫወተው ሚና ባሻገር፣ የኅትመት ወጪውን ቀንሶለታል፡፡ መረጃውን ወይም ትምህርቱን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች፣ ጽሑፉን በቀጥታ በኤሌክትሮኒክ አውርደው ይጠቀማሉና፡፡  

  • ጽሑፎቹን በተለያዩ ቋንቋዎች፣ ተነባቢ ማድረግ መቻሉ፤  

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት ጽሑፎቹን በአንድ ሺሕ ቋንቋዎች ተርጒሞ ለንባብ ይቀርባል፡፡ ይህ የቋንቋ ጒዳይ ዋነኛ ጒዳይ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ፣ እጅግ ውጤታማ አሠራር ነው፡፡ ሰው ራሱን በትክክል በሚገልጽበት፣ ዐሳቡን በጥሩ መንገድ አሳክቶ በሚናገርበት፣ የእኔ ነው በሚለው ቋንቋ መማሩና ማስተማሩ፣ እጅግ ውጤታማ አሠራር ነው፡፡

  • አካለ ስንኩላንን ተደራሽ ማድረጉ፤

ድርጅቱ አንድ መቶ በሚሆኑ የምልክት ቋንቋዎች መልእክቱን ተደራሽ እንዳደረገ፣ ይህም በዓለም የአንድኝነት ቦታ እንዳሰጠው ገልጾአል፡፡ ሰዎች መስማትና ማየት አለመቻላቸው፣ መልእክቱን ለመስማት እክል እንዳይፈጥር ማድረግ ችሏል ማለት ነው፡፡ ድርጅቱ ለዐይነ ስውራን ብቻ ሳይሆን፣ መናገር ለማይችሉ እንዲሁም ጆሮአቸው ለማይሰማ ሰዎች ኑፋቄውን ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡       

  • ዐላማውን ከዳር ለማድረስ እያንዳንዱን አባል መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙ፤  

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት እያንዳንዱ አባል፣ “አስፋፊ” በመባል ይጠራል፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ አባል የድርጅቱ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ:— በ2022 ዓ.ም የንቊ አባላት ቊጥር 8,699,048 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በየቀኑ ወጥቶ የሚሰብከው አባል 8,514,983 ነው፡፡ ይህ ማለት መስክ ወጥቶ የድርጅቱን ጽሑፍ ያላሠራጨ እንዲሁም የድርጅቱን ትምህርት ያልሰበከ 184,065 ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት በመስክ ሥራው ላይ ተካፋይ ያልሆነው፣ ሁለት ከመቶ (2.1%) ብቻ ነው፡፡ ይህ የድርጅቱን ሥራ ለማከናወን፣ አባላቱ ዕድሜና ጤና እንኳ እንደማይገድባቸው አመልካች ነው፡፡ በዚህ መንገድ ተገኝተው በውሃ ጥምቀት ድርጅቱን የተቀላቀሉ ሰዎች 145,552 ናቸው[44]፡፡

                  በዓመቱ ውስጥ ለመስክ ምስክርነት የዋለው ሰዓት 1,501,797,703 ነው፡፡ ይህን ቊጥር ለንቊ አባላት ቊጥር ስናካፍለው፣ እያንዳንዱ አባል በዓመት 176 ሰዓት፣ ለመስክ ምስክርነት አውሏል ማለት ነው (ይህ በወር 14 ሰዓት ነው)፡፡ በእንግሊዝ አገር የሚገኘው የኪንግስ ኮሌጅ፣ በኮሌጁ ውስጥ የሚማሩ የሙሉ ጊዜ ተማሪዎች፣ ለአንድ ሳምንት በክፍል ውስጥ የሚቈዩት ከ12 እስከ 16 ሰዓት እንደ ሆነ ገልጿል[45]፡፡

        በድርጅቱ ላይ ጥናት የሚያደርጉ  ምሁራን፣ “እያንዳንዱ ‘የይሖዋ ምስክር’ የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት የመሠራውን ያህል፣ ለቀጠረው መሥሪያ ቤት ያን ያህል አይሠራም የሚሉት” ይህ ዐይነቱን መረጃ በውል አገናዝበው  ነው፡፡ ይህ የአባላት እንቅስቃሴ ድርጅቱን ከመጥቀሙ አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ አባል በድርጅቱ ውስጥ፣ ሥራ አለኝ፣ ቦታ አለኝ፣ ለድርጅቱ አስፈልጋለሁ የሚል መንፈስ እንዲያድርበት የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ፣ “ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ለአንድ ሰው ሸክሙ ነው” የሚለውን አገርኛ ብሂል፣ በገቢር የተረጐመ ግብር ነው፡፡ ድርጅቱ እያንዳንዱን አባል በዚህ መጠን ማንቀሳቀስ ባይችል ኖሮ፣ ይህን የሚያህል ትልቅ ሥራ፣ መሥራት በፍጹ አይችልም ነበር (በኅትመት፣ በሥርጭት፣ በማስተማር ወዘተ)፡፡   

፱. እኛ ግን

        ሥነ ጽሑፍን በተመለከተ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ የተካሄደ ጥናት ያለ አይመስለኝም፤ ቢያንስ እኔ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ ይፋ የሆኑ የተወሰኑ ጥናቶች፣ ትምህርትና ሥነ ጽሑፍ (ንባብ) ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እየተነነ፣ ከዐውደ ምሕረቱ እየመነነ፣ የባዕድ አገር ሰው እንደ ሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ጥቂት መታዘቢያ ይሆን ዘንድ በቅርቡ የሕንጸት መጽሔት፣ “የምስባኮቻችን ነቀፌታ ለመፈተሽና መፍትሔዎቻቸውን ለማመልከት”  በሚል ርእስ ያካሄደው እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያኑ የዘመን ቀመር ጥቅምት 27 ቀን፤ 2016 ዓ.ም በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን የቀረበ አንድ ጥናት፣ በዚህ ረገድ ያለንን አጠቃላይ ትዝብት የሚያጠናክር ነው[46]፡፡

በየቤተ እምነቱ የሚገኙ 19 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥናቱ መካሄዱ፣ መጠይቁ 40 ጥያቄዎችን መያዙ፣ 207 ሰዎች ለመጠይቁ ምላሽ መስጠታቸው፣ ከዚህም ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ከ24 እስከ 54 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ (62 ከመቶ ወንዶች፣ 37 ከመቶ ሴቶች) መሆናቸው ተገልጾአል፡፡

 መጠይቁ የሚያጠነጥነው በሦስት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታች ላይ ነበር፡፡ ይኸውም:— (1) “የስብከትና የትምህርት አገልግሎት”፣ (2)  “የዝማሬና የአምልኮ አገልግሎት”፣ (3) “የጸሎትና የነጻ መውጣት አገልግሎት”፡፡

“የስብከትና የትምህርት አገልግሎት” ላይ የተደረገው ጥናት፣ 33 በመቶ የሚሆኑ የቤተ ክርስቲያን የሰንበት አምልኮ ተሳታፊዎች፣ የሚቀርበው ስብከተ ወንጌል ጠናማውን የወንጌል ትምህርት የተከተለ ነው በሚለው ጒዳይ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ተገልጾአል፡፡ 21 በመቶ የሚሆኑት፣ ሰባኪው ወይም አስተማሪው የምንባቡ ክፍል በትክክል አልተረጐመውም የሚል አቋም አላቸው፡፡ 22 በመቶ የሚሆኑት፣ በሰንበት አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ላይ ጥያቄ ያላቸው ናቸው፡፡ 55 በመቶ የሚሆኑት በሰንበት አምልኮ ላይ የሚቀርበው ስብከተ ወንጌል፣ ከዕለት ተዕለት ሕይወቴ ጋር አንዳችም ተያያዥነት የለውም የሚሉ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የቤተ ክርስቲያን የሰንበት ታዳሚ፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደስተኛ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምታቀርበው አገልግሎት መንፈሳዊም ሆነ አእምሮአዊ ጥያቄዬ ምላሽ አግኝቶአል ብሎ አያምንም፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የቤተ ክርስቲያን ታዳሚ፣ በቤተ ክርስቲያ አገልግሎት ደስተኛ አይደለም፡፡

“የዝማሬና የአምልኮ አገልግሎት” ረገድ የቀረበውም ጥናት፣ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ 40 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ዝማሬዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተከተሉ አይደሉም ወይም መከተላቸውን ርግጠኞች አይደለንም ብለዋል፡፡ እንዲያውም የአምልኮና የዝማሬ ፕሮግራም ተብሎ መከፈሉ፣ ጊዜን ከማጣበብ ውጪ አንዳችም ፋይዳ እንደሌላው የገለጹ ሰዎች መኖራቸው ተጠቅሶአል፡፡

“የጸሎትና የነጻ መውጣት አገልግሎት” ተብሎ በብዙ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አገልግሎት የሚሳተፉ 29 ከመቶ የሚሆኑ አባላት ብቻ እንደ ሆኑ ተገልጾአል፡፡ ከእነዚህ ሰዎችም መኻል 60 ከመቶ የሚሆኑት፣ በአገልግሎቱ መጽሑፍ ቅዱሳዊነት ላይ ጥያቄ አንዳላቸው፣ እንደማይታነጹ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም አገልግሎቱ የሰዎችን ሰብአዊ ክብር እንደማይጠብቅ የገለጹ አሉ፡፡

ሰዎች መናፍቃንን የሚከተሉት፣ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ፍለጋ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሰዎችን አእምሮአዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስ በመለሰበት መንገድ የማትመልስ ከሆነ፣ በመናፍቃን እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ ትክክለኛው መሠረተ እምነት ማምጣት ያለመቻሏ ብቻ ሳይሆን፣  የቤተ ክርስቲያን አባላት ራሳቸው ለመናፍቃን እንቅስቃሴ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ተጋልጠዋል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ የሰዎችን መንፈሳዊ፣ አእምሮአዊ፣ አካላዊና ማኅበራዊ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ በመለሰበት መንገድ መመለስ በጭራሽ አልቻለችም፡፡

፲. የመፍትሔ ዐሳብ

ከላይ የተቀመጡትን ዐሥራ ሁለት ነጥቦች እያንዳንዱ ሰው በጥልቀት እንዲመረምራቸውና እንዴት ተግባራዊ ይደረጋሉ የሚለውን ጒዳይ እንዲመክርበት በማሳሰብ፣ ርእሰ ጒዳዩን እንቋጭ፡፡ አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚከተሉት ጒዳዮች ተግባራዊ የመሚደረጉበት መንገድ ቢፈልግ መልካም ነው:—

  • ቢያንስ ቤተ እምነቶች የራሳቸው የሆነ የማተሚያ ቤት እንዲኖራቸው ቢደረግ፣
  • አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በጎልማሶች፣ በወጣቶችና በሕፃናት የተደራጀ ሥርዐተ ትምህርት እስከ አፈጻጸሙ ቢኖራቸው፣
  • ዐቅም በፈቀደ ሁሉ፣ ጥራትና በብዛት ሊያትሙ የሚችሉ ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያዎች እያንዳንዱ ቤተ እምነት እንዲያገኝ ጥረት ቢደረግ፣   
  • የቤተ እምነቱን መሠረተ እምነት እያንዳንዱ አባል በጥልቀት እንዲያውቅ እንዲሁም ሌሎች እንዲያውቁት የሚያደርግ ጥረት ቢደረግ፣  
  • መሠረታውያን በሆኑ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ላይ እንዲሁም በወቅታዊ ርእሰ ጒዳዮች ላይ ጽሑፎችን ማዘጋጀት፣
  • የመጻሕፍት ወር፣ የንባብ ሳምንት ወዘተ በማዘጋጀት ሕዝቡ የንባብ ፍላጎቱ እንዲያድግ ማስቻል፣
  • ጥሩ ጥሩ መጻሕፍትን በሰንበት አምልኮና በትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ላይ ማስተዋወቅ፣
  • ጥሩ ጥሩ ጸሓፍያንን ዐቅም በፈቀደው ሁሉ ማበረታታት፣
  • በየወሩ እንዲሁም ዓመታዊ ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ርእሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲቀርቡ በደረግ፣  
  • የቤት ለቤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማጠናከር፣   
  • ለነገረ መለኮት ጥናት እጅግ ጠቃሚ ናቸው የሚባሉ ዋና ዋና መጻሕፍትን በተለያየ ቋንቋ ተርጒሞ ማቅረብ፣
  •  የጽሑፍ ፍላጎቱና ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች፣ የልብ ወለድና የኢልብ ወለድ አጻጻፍ ሥልጠና መስጠት፤ እንዲጽፉም ማበረታታት፡፡
  •  በየአጥቢያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችን መክፈት፡፡ አባላት ገብተው እንዲማሩ ማበረታታት፡፡
  •  የመጻሕፍት ክለብ በማዘጋጀት አባላት በክበብ እንዲታቀፉ ማስቻል፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትንም መሸለም፡፡
  •  በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ የዐቅብተ እምነት ክበቦችን በማቋቋም በደርዛዌ ነገረ መለኮት፣ በሙግት ጥበብ፣ በመናፍቃን አስተምህሮ ላይ ወዘተ ጒዳይ ላይ ፍላጎቱ ያላቸውን ሰዎች ማሠልጠን፡፡
  •  በቤተ እምነት እንዲሁም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መኻል የልምድ ልምዶችንና የተለያዩ አሠራሮችን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣  
  •  የመጻሕፍት ግምገማ፣ የመጽሔት ግምገማ ማዘጋጀት፡፡ በተለያየ ርእስ ላይ ዕውቀት ያላቸውን ነገር ግን የተለያየ አቋም ያላቸውን ሰዎች ማሟገት፡፡ 

፰፩. ማጠቃለያ

ዕውቀትና ሥነ ጽሑፍ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት እንደ ተነነ፣ ከዐውደ ምሕረቱ እንደ በነነ፣ የቀድሞ ጥንካሬአችን እንኳ ከትውስታችን እንደ መነነ፣ ለማንም የተሰወረ አይደለም[47]፡፡ ሥነ ጽሑፍ ታሽቶ ባደገበት ቀዬ ምን ያህል ባይተዋር እንደ ሆነ ለሁሉ የተገለጠ ነው፡፡ 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ እንኳን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ በቤተ እምነት ደረጃ እንኳ፣ እጅግ መለስተኛ የሚባል የማተሚያ ቤት ያለው አንድም ቤተ እምነት አልነበረም (ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያውን በቊርጥ መናገር ባይቻልም)፡፡ ቤተ እምነቶቹ የተወሰኑ የኅትመት ሥራዎቻቸውን የሚያሳትሙት፣ የንግድ ማተሚያ ቤቶችን በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጻሕፍቱን ሽያጭ ከማናር በላይ፣ የኅትመት ጥራቱ እጅግ የተበላሸ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የመጻሕፍቱ አጠራረዝ መስመር ያልተከተለ፣ ስፌቱ በቀላሉ የሚተረተር፣ የወረቀቱ ጥራት እጅግ መናኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ ገጾቹን ከፍቶ ለማንበብ እንኳ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወረቀቱ አሲድ ስላለበት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ቢጫነት የሚቀየር፣ የጥረዝም ሆነ የኮርቻ ስፌቱ፣ በቀላሉ የሚላቀቅ፣ በአጠቃላይ የወረቀትና የኅትመት ጥራቱ በአገራችን ከሰባና ከሰማኒያ መቶ ዓመት በፊት የታተሙትን መጻሕፍት፣ የኅትመት ጥራት ያልተሻለ ነው፡፡ በእነዚህ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ታትመው የሚወጡ አብዛኞቹ መጻሕፍት የኅትመት ጥራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የአርትዖት ሥራቸው እንኳ በወጉ የተሠራላቸው አይደሉም—በነገረ መለኮት ይዘታቸውም ሆነ በሥነ ጽሑፍ ለዛቸው ለማንበብ የሚጋብዙ አይደሉም፡፡ እንደ መጠበቂያ ግንብ በኅብረ ቀለማት የተዋበ፣ በኅትመት ጥራቱ የላቀ፣ የወንጌል ትምህርት ማንበብ በጭራሽ አልታደልንም፡፡ 

አንዳንድ ቤተ እምነቶች፣ እንደ መስቀል ወፍ በዓመት አንዴ ታትሞ የሚወጣ መጽሔት ቢኖራቸውም በሥርጭት፣ በኅትመት ጥራት፣ በጽሑፍ ወቅታዊነት፣ በአርትዖት ሥራ ወዘተ ብዙ ወደ ኋላ የቀሩ ለመሆናቸው፣ ሥራቸው በግልጽ ይመሰክራል፡፡ ኅትመት በሌለበት ንባብ የለም፡፡ ንባብ በሌለበትም ዕውቀት የለም፡፡ ዕውቀት በሌለበት ደግሞ ብፍታ እንጂ እውነተኛ ዕድገት ሊኖር አይችልም፡፡


[1] ከወንድም ምኒልክ አስፋው ያገኘሁት ነው፡፡ 

[2] “ቀበፀ” ማለት ቈረጠ ነው፡፡ ስለዚህ “ቀቢፀ ተስፋ” ማለት ተስፋ መቊረጥ ማለት ነው፡፡

[3] በድርጅቱ አስተምህሮ ላይ ሰፊ ትንታኔና ኂስ መመልከት ከፈለጉ፣ የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ፣ “አርዮሳውያን፤ ‘የይሖዋ ምስክሮች’ አስተምህሮ በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን” የሚለውን መጽሐፍ ይመለከቷል፡፡

[4] ንቊ! (ሚያዝያ 22 ቀን፤ 1982 ዓ.ም)፤ ገጽ 29፡፡

[5] እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን ቀመር፣ 2023 ዓ.ም ላይ የወጣ ዘገባ ነው፡፡ ድርጅቱ የይዘትና የኅትመት ልዕቀቴ ትልቅ ነው ቢልም፣ የዐማርኛ ሰዋስውም ሆነ ለሞክሼ ሆህያት አንዳችም ቊብ እንደሌላው፣ የድርጅቱ ጽሑፎች ገለጥ ገለጥ በማድረግ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሰባራ ቅንፍ ያስቀመጥናቸው፣ ድርጅቱ ያሳሳታቸውን ነገር ግን መሆን የነበረባቸውን ሞክሼ ሆህያትና ትእምርቶች ነው፡፡ የሰዋስውን ስሕተት በዚህ መንገድ ማመላከት  አስቸጋሪ ስለሆነ እንዲሁ ትተነዋል፡፡ ስለዚህ በቀጥታ በተወሰደው ጽሑፍ ላይ፣ ቅንፍ የጨመርነው እኛ ነን፡፡     

[6] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[7] 1,423,039,931 ሰዓት

[8] “የመስክ አገልግሎት” የሚባለው የድርጅቱ አባላት በነቂስ አደባባይ ወጥተው፣ የድርጅቱን ጽሑፎች የሚያሠራጩበት እንዲሁም የድርጅቱን አስተምህሮ የሚሰብኩበት ጊዜ ነው፡፡

[9] https://www.jw.org/en/library/books/2021-service-year-report/2021-grand-totals/

[10] በቅርቡ ከእነርሱ ዘንድ የተገኘ መረጃ፣ የማተሚያ ቤቶቹ ቊጥር 15 ብቻ እንደ ሆኑ ይገልጻል፡፡ ይህ እውነታውን ለመደበቅ ሆነ ተብሎ የተደረገ ማሳሳት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እጅግ ብዙ ሰዎች ድርጅቱን ለቀው እየወጡ ስለሆነ፣ ይህም ድርጅቱ የማሽቈልቈሉን ጐዳና መያያዙን አመላካች ሊሆን ይችላል፡፡  

[11] CRI “Cult Growth Statistics”, Citing the Watchtower (1, Jan.1993): 19b.

[12] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[13] David A. Reed, Jehovah’s Withness Litrature: a Critical Guide to Watchtower Publications (Grand Rapids:Baker, 1993), 9.

[14] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[15] https://www.jw.org/en/jehovahs-witnesses/activities/publishing/global-printing/

[16] ዝኒ ከማሁ፡፡

[17] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[18] ዝኒ ከማሁ፡፡

[19] ዝኒ ከማሁ፡፡

[20] Alan W.Gomes, Unmasking the Cults, 23. 

[21]https://www.jw.org/en/publications/books/2016-yearbook/highlights/new-world-translation-more-languages/ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም ለድርጅቱ ትምህርት ምን ያህል ሎሌ እንዳደረ አርዮሳውያን በሚለው መጽሐፍ ላይ ሰፊ ሐተታ ቀርቧል፡፡ ሞክሼ ሆህያት፣ ሥርዐተ ነጥብ፣ ሙያዊ ቃላት እንዲሁ የዐማርኛ ሰዋስውን በተመለከተ እጅግ በርካታ ችግሮች ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ምናልባ በመጽሐፍ ቅዱስ ደረጃ የሥነ ጽሑፍ ለዘው በዚህ ደረጃ የተሟጠጠ ሥራ የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በዐማርኛ ሥነ ጽሑፍ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ሰዎች ይህን መጽሐፍ እንዲመለከቱት ምክሬ ነው፡፡    

[22]https://www.jw.org/en/jehovahs-witnesses/activities/publishing/watchtower-awake-magazine/

[23] ዝኒ ከማሁ፡፡

[24] ዝኒ ከማሁ፡፡

[25] የቀድሞ ጽሑፎችን ሳይጨምር መረጃው እነሆ:— “ቅዱሳት መጻሕፍትን በየዕለቱ መርምር”፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?”፣ “ምን ጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ሁኑ”፣ “የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምስክሮች” (የ2015 ዕትም)፣ “ወደ ይሖዋ ተመለስ”፣ “ኢየሱስ—መንገድ እውነት፣ ሕይወት”፣ “የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው”፣ “የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ”፣ “የምትወዱት ሰው ሲሞት”፣ “ልጆቻችሁን አስተምሩ”፣ “ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል”፣ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?”፣ “ለይሖዋ ዘምሩ”፣ “በእምነታቸው ምሰሏቸው”፣ “መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል?”፣ “የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ለማድረግ ቊልፉ ምንድን ነው?”፣ “ዓለምን እየተቈጣጠረ ያለው ማን ነው?”፣ “ስለ ወደ ፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል?”፣ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለህ?”፣ “የሞቱ ሰዎች እንደ ገና በሕይወት መኖር ይችላሉ?”፣ “ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ማድረግ አስባችኋል?”፣ “ከአምላክ ፍቅር አትውጡ”፣ “ወደ ይሖዋ ቅረብ”፣ “ከታላቁ አስተማሪ ተማር”፣ “ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምስክርነት መስጠት”፣ “በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም”፣ “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?”፣ “መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?”፣ “አምላክን ስማ”፣ “እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ?”፣ “ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?”፣ “የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፍ”፡፡

[26] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[27] ዝኒ ከማሁ፡፡

[28] ዝኒ ከማሁ፡፡

[29] ዝኒ ከማሁ፡፡

[30] ዝኒ ከማሁ፡፡

[31] ዝኒ ከማሁ፡፡

[32] ዝኒ ከማሁ፡፡

[33] https://www.jw.org/am/ዜና/አካባቢ/ዓለም-አቀፍ/ወንጌል-በኢንተርኔት/

[34] ዝኒ ከማሁ፡፡

[35] ዝኒ ከማሁ፡፡

[36] ዝኒ ከማሁ፡፡

[37] ዝኒ ከማሁ፡፡

[38] ዝኒ ከማሁ፡፡ በመታሰቢያ ቀን የተገኙ ሰዎች፡፡

[39] የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት፤ ኅዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም፤ ገጽ 27፡፡

[40] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[41] Alan W.Gomes, Unmasking the Cults, 23. 

[42] https://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/እንቅስቃሴዎች/ሕትመት/ዓለም-አቀፍ-ሕትመት/

[43] ዝኒ ከማሁ፡፡

[44] ከድረ ገጹ፣ “2022 Service Year Report–Grand Totals” የሚለውን ይመለከቷል፡፡  

[45] https://www.kings.edu/admissions/high_school_vs_college#:~:text=

[46] ሕንጸት መጽሔት ጥናቱን አካሂዶ፣ ጥቅምት 27 ቀን፤ 2016 ዓ.ም በሩሐማ ገዛኸኝ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ለታዳሚዎች የቀረበ ጽሑፍ፡፡ ይህን መረጃ በሕንጸት ዩቲዩብ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡  

[47] እንዲያውም ቅዱሳት መጻሕፍትን ደርዝ ባለው መልክ መተንተን፣ “የአእምሮ ሰው” ወይም፣ “የቃል ሰው” የሚል አሉታዊ ስያሜ የሚያከናንብበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ ከዚህ በተቃራኒው አንጻር የቆሙትን፣ “የጸጋ አገልጋዮች” “መንፈሳውያን ሰዎች” የሚል ትልቅ ክብር    ያጐናጽፋል፡፡

Share the Post:

Related Posts